እስራኤል ጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች - የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ኮሚሽን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ ውስጥ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች አለ።
በኮሚሽኑ የወጣው አዲስ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ሕግ ከተገለጹት አምስት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች አራቱ እስራኤል ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባችበት መስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
እነዚህም አንድ ቡድን አባላት ላይ ግድያን፣ ከባድ የአካል እና የአእምሮ ጉዳት ማድረስ፣ ቡድኑን ለማጥፋት ሆን ተብሎ የታሰበባቸው ሁኔታዎችን መፍጠር እና እንዳይወልዱ ማድረግ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
ሪፖርቱ በእስራኤል መሪዎች የተደረጉ ንግግሮች እና የእስራኤል ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች አካሄድን የዘር ማጥፋት ድርጊት ዓላማን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አድርጎ አቅርቧቸዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱን "የተዛባ እና ሐሰት" ሲል ሙሉ ለሙሉ አውግዞታል።
ቃል አቀባዩ የኮሚሽኑ ሦስቱን ባለሙያዎች "የሐማስ ተላላኪዎች" ሆነው የሚያገለግሉ እና "በሐማስ ውሸት ላይ ሙሉ በሙሉ መሠረት ያደረጉ፣ በሌሎች የተደገሙ ናቸው" በማለት ክሶቹ ከዚህ በፊት የተጋለጡ ናቸው ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ጦርነት የከፈተችው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎች ከተገደሉ እና 251 ደግሞ ከታገቱ በኋላ ነው።
ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው በዚህ የእስራኤል ዘመቻ ቢያንስ 64,905 ፍልስጤማውያን ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሦስት አባላት ያሉት ገለልተኛው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን የሚመራው ደቡብ አፍሪካዊቷ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ እና የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በነበሩት ናቪ ፒላይ ነው።
አዲሱ የኮሚሽኑ ሪፖርት የእስራኤል ባለሥልጣናት እና ወታደሮች በአውሮፓውያኑ 1948 በተቀመጠው የዘር ማጥፋት ብያኔ ላይ ከተገለጹት አምስት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች መካከል አራቱን በጋዛ ውስጥ ፍልስጤማውያን ላይ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
ለዚህም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የዘር ማጥፋት ማሳያ ያላቸውን የተፈጸሙ ድርጊቶችን በማስረጃነት አቅርቧል።
በዘር ማጥፋት ኮንቬንሽኑ መሠረት የዘር ማጥፋት ድርጊት ሕጋዊ ፍቺውን ለማሟላት፣ ፈጻሚው አካል ከእነዚህ ድርጊቶች አንዱን የፈፀመው ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ እንደሆነ መታወቅ አለበት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮሚሽኑ የእስራኤል መሪዎች የያደረጓቸውን ንግግሮች የተመለከተ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት "የዘር ማጥፋት እንዲፈጸም አነሳስተዋል" ብሏል።
በተጨማሪም የእስራኤል ባለሥልጣናት እና በጋዛ የሚገኙ የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች አካሄድን መሠረት በማድረግ ሊደመደም የሚችለው "የዘር ማጥፋት አላማ ብቸኛው ምክንያት መሆኑን ነው" ይላል።
ኮሚሽኑ፤ የአፈጻጸሙ ሁኔታ ሆን ተብሎ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ፍልስጤማውያን ላይ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም መግደል እና ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ በሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና የትምህርት ቦታዎች ላይ ስልታዊ እና ሰፊ ጥቃቶች መፈጸም እና ጋዛን በመክበብ ነዋሪን ማስራብ ተፈጽሟል ብሏል።
የእስራኤል መንግሥት ግን እርምጃው የሐማስን አቅም በማውደም ላይ እንጂ በጋዛ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ አጥብቆ ይከራከራል። ኃይሎቹም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደሚንቀሳቀሱ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይናገራል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት በከፈተችበት የመጀመሪያ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ "ክፉ ከተማ" ብለው በጠሯት ጋዛ ውስጥ ሐማስ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከባድ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ መናገረችውን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "'ክፉ ከተማ' የሚለውን ሐረግ መጠቀማቸው አጠቃላይ የጋዛ ከተማን እንደ ተጠያቂ እና የበቀል ዒላማ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ያሳያል። እናም ፍልስጤማውያን 'በቶሎ ለቃችሁ ውጡ ምክንያቱም በሁሉም ቦታ የኃይል እርምጃ እንወስዳለን' ብለዋል" ሲሉ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ የእስራኤል የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች ድርጊት "የእስራኤል መንግሥት" ድርጊቶች ናቸው ሲል ገልጿቸዋል፤ ስለዚህም መንግሥቱ "የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል ባለመቻሉ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በማስቻሉ እና የዘር ማጥፋት ወንጀልን ባለመቅጣቱ ኃላፊነቱን ይወስዳል" ብሏል።
እንዲሁም ሁሉም ሌሎች አገራት በዘር ማጥፋት ኮንቬንሽኑ መሠረት "ሁሉንም እርምጃዎች በመውሰድ የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል እና መቅጣት ካልቻሉ" ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል።
በርካታ ዓለም አቀፍ እና የእስራኤል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ገለልተኛ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ባለሙያዎች እንዲሁም ምሑራን እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ሲሉ ከስሰዋል።
በሌላ በኩል የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የእስራኤል ኃይሎች ላይ በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ እየተመለከተ ነው። እስራኤል ጉዳዩን "ፍፁም መሠረተ ቢስ" እንዲሁም "አድሏዊ እና ሐሰተኛ ክሶች" በማለት አጣጥላዋለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters















