የእስራኤል ጦር አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች የጋዛ ከተማን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ

የጋዛ ነዋሪዎች በጋሪ አካባቢያቸውን ለቀው ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ሰፊ የምድር ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ መላው የጋዛ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች።

የጦሩ የአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባይ በጋዛ ትልቁ ከተማ የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አዝዘዋል።

ቃል አባዩ "በከተማዋ ውስጥ መቅረት በጣም አደገኛ ነው።" ብለዋል።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርብ ቀናት በጋዛ ትላልቅ ሕንጻዎችን ያወደመው የአየር ጥቃት "የዋናው ጥቃት እና ከፍተኛ ዘመቻ መጀመሪያ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻው የሐማስ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታን መቆጣጠር እንደሆነም ገልጸዋል።

ሐማስ በበኩሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሰዎች በግዳጅ እንዲፈናቀሉ የሚያደርግ ወንጀል ነው ብሏል።

እስራኤል የጋዛ ከተማን የመውረር እቅዷ ዓለም አቀፍ ትችቶችንም አስከትሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ረሃብ እንደተከሰተ በታወጀበት አካባቢ የሚፈፀመው ጥቃት መባባስ ሰላማዊ ሰዎችን ወደ ባሰ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ ከተማ በበተናቸው በራሪ ወረቀቶች እና በአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባዩ ኮሎኔል አቪቻይ አድሬ በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራው ጽሑፍ ላይ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።

መልዕክቱ " ለሁሉም ነዋሪዎች እና በጋዛ ከተማ ፣ በጥንታዊ ከተማ እና ከባሕሩ በምዕራብ በኩል ከቱፋህ አካባቢ ደግሞ በምሥራቅ በኩሉ ለምትገኙ ሁሉ፡ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሐማስን ለማንበርከክ ቁርጠኛ ነው። በመሆኑም በጋዛ ከተማ በታላቅ ቁርጠኝነት ዘመቻ ያካሂዳል። በመሆኑም ለደኅንነታችሁ ስትሉ በአስቸኳይ ውጡ" ይላል።

በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ሐምሌ ወር ላይ ከሐማስ ጋር በተደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር የተደረሰው ስምምነት ከፈረሰ በኋላ የእስራኤል የጸጥታ ምክር ቤት ሙሉ ጋዛን ለመውረር የቀረበውን እቅድ አጽድቋል።

በዚህም መከላከያ ጦሩ ከሁለት ዓመት በላይ ባካሄደው ጦርነት ሐማስን እንዲያሸንፍና በታጣቂ ቡድኑ አሁንም ተይዘው የሚገኙ እና 48 ታጋቾችን እንዲያስመልስ ተነግሮታል። ከታጋቾቹ መካከል 20 የሚሆኑት በሕይወት እንደሚገኙ ይታመናል።

በቅርብ ሳምንታት እስራኤል በጋዛ ከተማ የምትፈፅመው የአየር እና የምድር ጥቃት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ትናንት ምሽቱንም መከላከያ ጦሩ ሐማስ ጥቃት ለመፈፀም ይጠቀምበታል ያላቸውን ሕንጻዎች በአየር ደብድቧል።

ሰኞ ዕለት ኔታንያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በጋዛ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ 50 የሚሆኑ ትላልቅ ሕንጻዎች መውደማቸውን ተናግረዋል።

" ይህ ሁሉ የመጀመሪያው ነው።ኃይሎቻችን በምድር የሚፈፅሙት የዋናውና ሰፊው ጥቃት መጀመሪያ ነው" ሲሉም የጋዛ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ኔታንያሁ አስጠንቅቀዋል።

ማክሰኞ ዕለትም የባሕር ዳርቻ ከሆነችው ጋዛ ከተማ ነዋሪዎች በእግራቸው፣በጋሪ እና በተሽከርካሪዎች ወደ ከተማዋ ደቡባዊ አቅጣጫ ሲሄዱ ምስሎች አሳይተዋል። ሆኖም የጅምላ ስደትን የሚያሳዩ ምልክቶች የሉም።

ሃና የተባለች የሦስት ልጆች እናት ቤተሰቦቿን ወደየት እንደምትወስድ እንደማታውቅ እና የከፋ ነገር እስከሚመጣ ድረስ እዚያው ይዛቸው እንደምትቆይ ለቢቢሲ ተናግራለች።

" የምሄድበት ቦታ ቢኖረኝ ኖሮ ቤተሰቦቼን እና ልጆቼን ይዤ እስካሁን እወጣ ነበር" ብላለች።

ሃና በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅት እስራኤል በፈፀመችው የቦምብ ጥቃት መኖሪያ ቤቷ የወደመ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቿ ጋር ተፈናቅላ ነው ያለችው።

አሁን ላይ እርሷ እና ቤተሰቦቿ እየተሰማቸው ያለውን ስሜት የሚገልጸው ቃል እንደሌለም ተናግራለች።

ራዛን ሳልሃ የተባለች ተማሪም የሚፈፀመው ጥቃት በመባባሱ ከሁለት ቀን በፊት ጋዛ ከተማን ለቃ መውጣቷን እና ዴር አል ባላህ ከተማ ውስጥ አንድ ክፍል ከ20 ዘመዶቿ ጋር ተጋርታ እየኖረች እንደሆነ ገልጻለች።

" በመኪና ነው 375 ዶላር ከፍለን የወጣነው። ብዙ ሰው ከከተማው አልወጣም። የሚሄዱበት ቦታ ስለሌላቸውና በተመጣጣኝ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት ስለሌለ ከጋዛ ከተማ ያልወጡ ሰዎች አሉ" ስትል ለቢቢሲ በላከችው የድምጽ መልዕክት ተናግራለች።

ራዛን እንደምትለው አለመረጋጋት እና ቤት አልባነት አቅም ያሳጣት ሲሆን ተስፋዋንም አጨልሞታል።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት እና አጋሮቻቸው የእስራኤል የተባባሰ ጥቃት አስከፊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

እሁድ ዕለት ባወጡት ሪፖርትም ከነሐሴ መጀመሪያ አንስቶ ከ97 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን፤ ነገር ግን ከሰሜናዊ ጋዛ ወደ ደቡባዊ ጋዛ መሻገር የቻሉት 50 ሺህ ዎቹ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የእስራኤል መከላከያ እነዚህን ሰዎች አዲስ ወደተለየውና በአል ማዋሲ ወደሚገኘው ሥፍራ እንዲሄዱ ነግሯቸዋል። ሆኖም አካባቢው በተደጋጋሚ በእስራኤል ጥቃት የደረሰበት ሲሆን የተባበሩት መንግሥታትም አሁን ላይ "በጋዛ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥፍራ የለም" ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ዓለም አቀፉ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በጋዛ ረሃብ መከሰቱን ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ካረጋገጡ ወዲህ 121 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የእስራኤል ጦር ከሁለት ዓመት በፊት በጋዛ ላይ የጥቃት ዘመቻ የከፈተው ሐማስ በደቡባዊ የአገሪቷ ክፍል ጥቃት በመሰንዘር 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 64 ሺህ 605 ሰዎች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን የግዛቷ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።