እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በመቀጠል ሁለተኛውን ግዙፍ ሕንጻ አወደመች

በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የወደመው ሱሲ ታወር

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሱሲ ታወር በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የወደመ ሁለተኛው ሕንጻ ነው

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ በመቀጠል ሁለተኛውን ግዙፍ ሕንጻ አወደመ።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምስል ሕንጻው ሲወድም የሚያሳይ ሲሆን "እንቀጥላለን" የሚል የጽሁፍ መልዕክት አስፍረውበታል።

በጋዛ የሚፈጽመውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክሮ የቀጠለው ጦሩ ሱሲ ታወር ሐማስ የሚገለገልበት ነበር ያለ ሲሆን ቡድኑ ግን አስተባብሏል።

ሕንጻው በሚወድምበት ወቅት ምን ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እስካሁን ድረስ ማወቅ አልተቻለም።

ቅዳሜ ዕለት እስራኤል ጥቃቱን ከመፈፀሟ በፊት ሰላማዊ ዜጎች የሰብዓዊነት ቀጠና ስትል በጠራቸው ወደ ከተማዋ ደቡብ አካባቢ እንዲሄዱ የሚያስጠነቀቅቅ በራሪ ወረቀት በትናለች።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋራ ልጥፍ የእስራኤል ጦር በአረብኛ በካን ዮኒስ እና በባሕር ዳርቻው መካከል በሚገኘው የአል ማዋሲ አካባቢ "ቀድመው የሄዱትን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቀላቀሉ" የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

የእስራኤል ጦር በተደጋጋሚ ሠላማዊ ዜጎች ወደዚያ አካባቢ እንዲሄዱ በተደጋጋሚ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ነበር። ወደዚያ አካባቢ ለሚሄዱ ሰዎች ሕክምና፣ ውሃ እና ምግብ እንደሚቀርብም ገልጿል።

ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአል ማዋሲ የሚገኙት የመጠለያ ድንኳኖች በተፈናቃዮች ተጨናንቀዋል፤ ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደለም፤ እንዲሁም በደቡባዊ አቅጣጫ ያሉ ሆስፒታሎች በሕሙማን ተሞልተዋል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማክሰኞ ዕለት በአል ማዋሲ ውሃ ለመቅዳት ሲጠባበቁ የነበሩ አምስት ሕጻናት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የዓይን እማኞች የእስራኤል ድሮኖች ባደረሱት ጥቃት ሕጻናቱ መገደላቸውን ሲናገሩ ጦሩ በበኩሉ "ጉዳዩን እየተመለከትኩት ነው" ብሏል።

ሱሲ ታወር በእስራኤል የቅርብ ጥቃት የወደመ ሁለተኛው ትልቁ ሕንጻ ነው።

አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል ሙሻታሃ ታወር ከፍተኛ ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ ወደ ፍርስራሽነት ሲለወጥ ያሳያል።

የእስራኤል መከላከያ የሰላማዊ ዜጎችን ሞት ለመቀነስ "ለሕዝቡ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠትን" ጨምሮ "ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ መሳሪያዎችን በመጠቀም" ጥንቃቄ ተወስዷል ሲል ገልጿል።

ፍልስጤማውያን ግን የተፈናቀሉ ሰዎች በሙሻታሃ ታወር ተጠልለው እንደነበር የገለፁ ሲሆን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማሃሙድ ባሳል በበኩላቸው እስራኤል "የግዳጅ ማፈናቀል ፖሊሲን ትከተላለች" ሲሉ ወንጅለዋል።

የሳተላይት ምስሎች የእስራኤል ጦር በአካባቢው የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ሕንጻዎች ትቢያ መሆናቸውን እና አካባቢው በፍርስራሽ ክምሮች መሞላቱን ያሳያሉ።

እነዚህ የመኖሪያ እና የንግድ ሕንጻዎች የጋዛ ከተማን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ የያዙ ሲሆን እስራኤል ወረራዋን አቁማ ነጻ የፍልስጤም አገር የመመስራት ተስፋ ሰንቀው ነበር።

በከተማዋ ከአምስት ፎቅ በላይ ሕንጻ መገንባት የተጀመረው እአአ በ1993 የኦስሎ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።

ከዚህ ስምምነት በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከስደት ተመልሰው በጋዛ እና በዌስት ባንክ መኖር ጀምረዋል።

እስራኤል እአአ በ1994 ከአብዛኛው የጋዛ አካባቢ መውጣቷን ተከትሎ ተመላሾች የሚኖሩበትን ስፍራ ለማዘጋጀት ረዣዥም ሕንጻዎች መገንባት አስፈልጎ ነበር።

የፍልስጤም አስተዳደር በግንባታው ዘርፍ ሰዎች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ ሲያበረታታ የነበረ ሲሆን አካባቢውም በሕንጻው ስም መጠራት ጀምሯል።

እስራኤል እና ሐማስ በተዘዋዋሪ ሲያደርጉት የነበረው የተኩስ አቁም ድርድር ያለውጤት መበተኑን ተከትሎ ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ሰርጥን በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት 1 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በጋዛ እንደቀሩ ተናግሮ በሰርጡ ረሃብ መከሰቱን አውጇል።

በጋዛ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ግልጽ የሆነ "ውድመት" ይፈጠራል ሲል አስጠንቅቋል።