ኔታንያሁ ጦርነት ለማቆም እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ እንዲስማሙ የሚጠይቁ በርካታ ሰልፈኞች በእየሩሳሌም ተቃውሞ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከ15,000 በላይ እስራኤላውያን፤ በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቀሪዎቹን ታጋቾች ማስለቀቅ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለመጠየቅ ሰልፍ ወጡ።
በሀማስ የተያዙ ታጋቾች ቤተሰቦች እና ደጋፊዎች እየሩሳሌም በሚገኘው ፓሪስ አደባባይ የተሰባሰቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በቴል አቪቭ ሰልፍ ወጥተዋል።
ጋዛ ውስጥ ከታገቱት 48 እስራኤላውያን መካከል 20 የሚሆኑት በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
እስራኤል፤ የተወሰኑ ታጋቾች እንዲፈቱ ለማድረግ የተዘጋጀውን ስምምነት በተመለከተ እስካሁን በይፋ ምላሽ አልሰጠችም። ከዚህ ቀደም ግን በሚፈረም የማንኛውም ስምምነት ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ የሚያስችል መሆን አለበት የሚል አቋም ስታንጸባርቅ ቆይታለች።
ኔታንያሁ፤ ሀማስ ላይ ሙሉ ድል መጎናጸፍ ታጋቾች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ያደርጋል በሚል አቋማቸው ጸንተዋል።
ሐማስ በመስከረም 26/2017 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት በመፈጸም 251 ታጋቾችን ወደ ጋዛ የወሰደ ሲሆን በጥቃቱም 1,200 ሰዎች ተገድለዋል።
እስራኤል በከፈተችው ዘመቻም ቢያንስ 64,368 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሀማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የተባበሩት መንግሥታት እነዚህን አሃዞች እውነተኛ አድርጎ ቢመለከታቸውም፤ እስራኤል ግን ታጣጥለዋለች።
በጋዛ ላይ የሚካሄደው ወታደራዊ ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቁ የእስራኤላውያን የጎዳና ላይ የተቃውሞ ሰልፎች እና የእስራኤል አጋሮች ዓለም አቀፍ ጥያቄዎች እየጨመሩ መጥተዋል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የሚያመለክቱት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተዘጋጀ መሆኑን ነው። የኔታንያሁ መንግሥት የጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ ለመውረር፣ በመጨረሻም ሀማስን ለማሸነፍ የተጠናከረ ዘመቻ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲለቀቁ እና ጦርነቱ እንዲቆም ቅዳሜ ምሽት ቴል አቪቭ እና ኢየሩሳሌም የተደረጉት ሰልፎች በቅርብ ጊዜያት ከተካሄዱት የበለጠ ሰው የተገኘባቸው ናቸው።
በከተማዋ ከሚገኘው የኔታንያሁ መኖሪያ ቤት አካበቢ የተገኙ ሰልፈኞች ድምፅ ማጉያ በመጠቀም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታገቱ ሁለት ዓመት ገደማ የሆናቸውን እስራኤላውያን ለማስመለስ ከሀማስ ጋር ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፉ መልዕክቶችን በቁጣ ካሰሙት በርካታ የቤተሰብ አባላት መካከል በጋዛ ተይዞ የሚገኘው የእስራኤል ጦር ወታደር ማታን አንግሬስት እናት ይገኙበታል።
"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ማስፈራሪያ አይደለም፤ የሆነ ነገር ቢከሰት ዋጋውን ይከፍላሉ፤ ይህ የእናት ቃል ነው" ሲል ጮኸት መናገራቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
ብዙዎቹ ሰልፈኞች የጦርነቱ መስፋፋት የታገቱት ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል ይናገራሉ። ኔታንያሁ በእየሩሳሌም አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሊሆን ቢችልም የወላጆች እና ደጋፊዎች ጥሪ አዳማጭ አላገኘም።
የሚቀርቡባቸው ትችቶች እየጠነከሩ እንኳ በአቋማቸው የጸኑት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ግን እስካሁን ጦርነቱን የማቆም ምልክት አላሳዩም።
በርካታ የእስራኤል የቀድሞ ወታደራዊ መሪዎች፤ የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በእገታ ላይ ያሉትን ሰዎች ሕይወት ይበልጥ አደጋ ላይ ሳይጥል እና በጋዛ ያለውን ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ሳያባብስ በወታደራዊ አቅሙ የቻለውን ያህል ማከናወን ችሏል በማለት ይከራከራሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA/shutterstock
ይህ አቋም በስራ ላይ ባሉ በርካታ የጦር ጄነራሎች ዘንድም የሚንጸባረቅ እንደሆነ ተዘግቧል። ነገር ግን አሁን ጄነራሎቹ፤ በጦርነቱ የወደመው የፍልስጤም ግዛትን ጨምሮ ጋዛ ከተማን ለመውረር ለሚካሄድ ግዙፍ የመሬት ላይ ወረራ እንዲዘጋጁ በመንግስታቸው እየተጠየቁ ነው።
የኔታኒያሁ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በጋዛ ከተማ የሚገኙ ባለ ብዙ ወለል ህንጻዎች ሲፈነዱ የሚታዩባቸው ቪዲዮዎች በመለጠፍ፤ 'ይህ ገና ጅምር ነው' የሚል ግልጽ መልእክት በማህበራዊ ሚዲያ አስተላልፈዋል።















