እስራኤል የገደለቻቸው ከ178 በላይ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች

እስራኤል በአልሺፋ ሆስፒታል በጋዜጠኞች ድንኳን ላይ የፈጸመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Bashar Taleb/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በአልሺፋ ሆስፒታል በጋዜጠኞች ድንኳን ላይ የፈጸመችው ጥቃት

እስራኤል በጋዛ ላይ የተቀናጀ ጥቃት ከጀመረች መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ 192 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አስታውቋል። እንደ ተቋሙ ከሆነ ቢያንስ 178 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች በእስራኤል ተገድለዋል።

እስራኤል ሆን ብላ አነጣጥራ በፈጸመችው ጥቃት በቅርቡ ከተገደሉት መካከል ታዋቂው የአልጀዚራ ዘጋቢ አናስ አል ሻሪፍን ጨምሮ አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ይገኙበታል።

ጋዜጠኞቹ በጋዛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል ነው ነሐሴ 4/2017 ዓ.ም. የተገደሉት።

የአልጀዚራዎቹ ዘጋቢዎች ሻሪፍ እና መሐመድ ቄሬህ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያዎቹ ኢብራሂም ዛሄር፣ መሐመድ ኑፋል እና ሙአሚን አሊዋ ጥቃት በተፈጸመባቸው ወቅት በሆስፒታሉ ዋነኛ በር ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ድንኳን ውስጥ እንደነበሩ የመገናኛ ብዙኃኑ አስታውቋል።

ሁለት ዓመት ሊጠጋ በተቃረበው ጦርነት ውስጥ እስራኤል ከገደለቻቸው ጋዜጠኞች መካከል የተወሰኑትን ታሪካቸውን እነሆ፦

አናስ አል ሻሪፍ

አናስ አል ሻሪፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አናስ አል ሻሪፍ

አናስ አል ሻሪፍን ጨምሮ አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የአል ሺፋ ሆስፒታል ሲገደሉ ሌሎች ሁለት ፍልስጤማውያንም ተገድለዋል።

የ28 ዓመቱ አናስ የጋዛን ጦርነት፣ ውድመት፣ በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለውን ሕይወት በአልጀዚራ አማካይንት ካሳወቁ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው።

እስራኤል የአየር ጥቃት በፈጸመችባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በውጊያዎች አካባቢ በቀጥታ በመዘገብ ይታወቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለአልጀዚራ ለሁለት ዓመት የሠራው አናስ የተወለደው በሰሜን የጋዛ ሰርጥ በሕዝብ በተጨናነቀችው ጃባሊያ አካባቢ ነው።

አናስ ባለትዳር እና የአራት ዓመት ሴት ልጅ ሻም እና የአንድ ዓመት ወንድ ልጅ ሳላ አባት ነው።

እስራኤል በግዳጅ ፍልስጤማውያንን ከሰሜናዊ ጋዛ ማፈናቀሏን ተከትሎ ቤተሰቦቹ ተፈናቅለዋል።

የግዳጅ መፈናቀሉን ባለመቀበል አናስ ከሰሜናዊ ጋዛ ሪፖርት የሚያደርግ ሲሆን፣ ከቤተሰቦቹ ጋርም ለረጅም ጊዜ መለያየት የከፈለው መስዋዕትነት ነው።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2023 የቤተሰባቸው መኖሪያ ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት አባቱን ጀማል አል ሻሪፍን አጥቷል።

እስራኤል የገደለችው አናስ ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ጽሁፍ አስቀምጦ ነበር።

መሞቱን ያወቀ የሚመስለው ጋዜጠኛው ከተገደለ በኋላ ያስቀመጠው ጽሁፍ በጓደኛው አማካኝነት ኤክስ ገጹ ላይ ሰፍሯል።

"እነዚህን ቃላት ካነበባችሁ እስራኤል እኔን በመግደል እና ድምጼን በማፈን እንደተሳካላት እወቁ" ይላል።

"በከፍተኛ መከራ ኖሬያለሁ። ስቃይ እና ማጣትን ደጋግሜ አውቃቸዋለሁ። በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ ግን ያለ ምንም ማዛባት እውነቱን ከማስተላለፍ ወደ ኋላ አላልኩም" ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አናስን ዒላማ አድርጎ መግደሉን አረጋግጦ "የሐማስ የሽብር ቡድን" መሪ ሲል ወንጅሎታል። ነገር ግን ይህንን ውንጀላውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም።

ከዚህ ጦርነት በፊት አናስ ለሐማስ ሚዲያ ይሠራ ነበር ሲል አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ቢናገሩም አልጀዚራ ይህንን ውድቅ አድርጎታል።

የቢቢሲ የጋዛ የአረብኛ ፕሮግራም ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማግኘቱን አስታውቋል። ጋዜጠኛው ከመገደሉ በፊት በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈራቸው ጽሁፎቹ ሐማስን የተቸበት አጋጣሚም ነበር።

መሐመድ ቅርቄህ

መሐመድ ቅርቄህ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, መሐመድ ቅርቄህ

ሌላኛው የአልጀዚራ ጋዜጠኛ መሐመድ ቅርቄህ በእስራኤል ጥቃት የተገደለው ከባልደረው አናስ አል ሻሪፍ ጋር ነው።

በጋዛ ሹጃያ በተባለች ስፍራ የተወለደው መሐመድ ዕድሜው 33 ነበር።

በጋዛ ከሚገኘው ኢስላሚክ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና በሚዲያ ሥራ የመጀመሪያ ዲግሪውን በአውሮፓውያኑ 2015 አግኝቷል።

ባለፈው ዓመት የእስራኤል ጦር የአል ሺፋ ሆስፒታልን መውረሩን ተከትሎ መሐመድ የእናቱን አስክሬን አገኘ። ወንድሙም በሹጃያ ሰፈር እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ቆስሎ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

እስራኤል የገደለችው ይህ ጋዜጠኛ ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነበር።

ፋጢማ ሃሳውና

የፎቶ ጋዜጠኛ የሆነችው ፋጢማ ሃሳውና ሚያዝያ 8/2017 ዓ.ም. በእስራኤል ጥቃት የተገደለችው ለ2025 የካንስ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት መመረጧ ከታወጀ ከ24 ሰዓት በኋላ ነበር።

ለሽልማት የተመረጠችበት በእሷ እና በፍልስጤማውያን የዕለት ተዕለት የሕይወት ትግል ላይ የሚያተኩር ዘጋቢ ፊልም ነበር።

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ላይ ባነጣጠረ ጥቃት እሷ እና በርካታ የቤተሰብ አባሎቿን ገድሏል።

የእስራኤል ጦር በሐማስ አባላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው የፈጸምኩት ብሏል።

ታዋቂዋ ፈረንሳያዊት የፊልም ተዋናይት እና የካንስ ፊልም ፌስቲቫል ዳኛ ጁሊየት ቢኖቼ ከፋጢማ ግድያ በኋላ ያላትን አድጋቆት ገልጻ ነበር።

"ፋጢማ ዛሬ ምሽት ከእኛ ጋር መሆን ነበረባት። ጥበብ ዘላለማዊ ነው። ለሕይወታችን እና ለህልማችን ኃያል ምስክር ነው" ስትል ዘክራታለቸ።

አህመድ ማንሱር

በእስራኤል የአየር ጥቃት መጋቢት 29/2017 ዓ.ም. የተገደለው አህመድ ማንሱር 'ፓለስታይን ቱደይ' የተባለ የዜና ወኪል ጋዜጠኛ ነበር።

እስራኤል ዒላማ ስታደርገውም ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ድንኳን ውስጥ ነበር።

በድንኳኑ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሌላኛው ጋዜጠኛ ሄልሚ አልፋቃቂ እና ሦስተኛ ሰው ዩሱፍ አል ካዚንዳር ሲገደሉ፤ ዘጠኝ ጋዜጠኞች ቆስለዋል።

የፍልስጤም የጋዜጠኞች ማኅበር በጋዜጠኞቹ ላይ የተፈጸመውን "አስፈሪ እና አሰቃቂ ጭፍጨፋ" ሲል ነበር ያወገዘው።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱ ያነጣጠረው ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት አብሮ በነበረው የፎቶ ባለሙያ ሐሳን አስሊህ ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል።

በሐማስ ስር ያለው የሚዲያ ቢሮ ዳይሬክተር እስማኤል አል ታዋባታ እስራኤል በአስሊህ ላይ ያቀረበችው ውንጀላ "ሐሰተኛ" ነው ያሉ ሲሆን፣ የፎቶ ባለሙያው ከቡድኑ ጋር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ትስስር እንደሌለው ተናግረዋል።

ፈይሰል አቡ አል ቁምሳን፣ አይማን አል ጃዲ፣ ኢብራሂም አል ሼክ ካሊል፣ ፋዲ ሃሳውና እና ሙሐመድ አል ላዳህ

'አል ቁድስ አል ዩም' ለተሰኘ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሠሩት አምስት ጋዜጠኞች ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ።

በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በሚገኘው ኑሴራት የስደተኞች ካምፕ የነበሩበት መኪናቸው ዒላማ ተደርጎ በተፈጸመባቸው ጥቃት ነው የጋዜጠኞቹ ሕይወት የተቀጠፈው።

የእስራኤል ሚሳዒል አል አውዳ ሆስፒታል ፊት ለፊት ቆማ የነበረችውን ተሽከርካሪ መትቶ ጋዜጠኞቹን መግደሉን እና ተሽከርካሪዋ መውደሟን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ተሽካርካሪዋ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መለያ በግልጽ ተለጥፎባት እንደነበር እና ጋዜጠኞቹ በሆስፒታሉ ውስጥ እና በኑሴይራት የስደተኞች ካምፕ ዘገባ ለመሥራት መገኘታቸውን የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የእስራኤል ጦር ጥቃት መፈጸሙን አምኖ በተሽከርካሪው ውስጥ "የኢስላሚክ ጂሃድ አባላት ነበሩ" ብሏል።

እስማይል አል ጋውል እና ራሚ አል ሪፊ

በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የአልጀዚራ ዘጋቢ የነበረው እስማኤል አል ጋውል ጭንቅላቱ የተቆረጠ አስክሬን ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጋራ።

በጋዛ ከተማ መኪና ውስጥ እያለ ነበር የእስራኤል ጦር ዒላማ ሆኖ የተገደለው።

የካሜራ ባለሙያው ራሚ አል ሪፊ እና በብስክሌት ላይ የነበረ ካሊድ አል ሻዋ የተባለ ልጅ በዚህ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት ተገድለዋል።

የእስራኤል ጦር ጋዜጠኛውን "የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ተዋጊ እና የኑክባ አሸባሪ" ሲል የፈረጀው ሲሆን፣ በታጣቂው ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ነበረው ብሏል።

አልጀዚራ በጋዜጠኛው ላይ የቀረበውን ውንጀላ መሠረተ ቢስ ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ይህ "እስራኤል ለረጅም ጊዜ የምታደርገው የፈጠራ ታሪክ እና አሰቃቂ ወንጀሎቿን ለመሸፈን የምታቀርበው የሐሰት ማስረጃን የሚያሳይ ነው" ብሏል።

ሐምዛ አል ዳህዱህ

ሃምዛ በጋዛ ሰርጥ የአልጀዚራ ቢሮ ሃላፊ ዋኤል አል ዳህዱህ የበኩር ልጅ ነው

የፎቶው ባለመብት, @hamzadah1996 on X

የምስሉ መግለጫ, ሃምዛ በጋዛ ሰርጥ የአልጀዚራ ቢሮ ኃላፊ ዋኤል አል ዳህዱህ የበኩር ልጅ ነው

የአልጀዚራ ጋዜጠኛ እና የካሜራ ባለሙያ ሃምዛ አል ዳህዱህ ራፋህ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ሆነው ከኻን ዩኒስ ወደ ራፋህ በሚጓዙበት ጊዜ ነበር በእስራኤል ድሮን ዒላማ ተደርገው ታኅሣሥ 28/2016 ዓ.ም. የተገደሉት።

ሌላኛው የፍሪላንስ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ቱራያም በዚሁ ጥቃት ተገድሏል።

የእስራኤል ጦር ከጥቃቱ በኋላ "በጋዛ መሠረታቸውን ያደረጉ የአሸባሪ ድርጅቶች አባላት ናቸው" ብሏል።

ሃምዛ በጋዛ ሰርጥ የአልጀዚራ ቢሮ ኃላፊ ዋኤል አል ዳህዱህ የበኩር ልጅ ነው።

ዋኤል አል ዳህዱህ ባለቤቱ፣ ሴት ልጁ፣ ወንድ ልጁ፣ እና የልጅ ልጁ በእስራኤል ጥቃት ጥቅምት ወር ላይ እንደተገደሉ ሲረዳ የቀጥታ ዘገባ እየሠራ ነበር።

ታኅሣሥ ገደማ ዋኤል በእስራኤል ጥቃት ሲቆስል የአልጀዚራው የካሜራ ባለሙያ ሳሜር አቡ ዳቃ ተገደለ።

ሳሜር አቡ ዳቃ

ሳሜር አቡ ዳቃ

የፎቶው ባለመብት, Al Jazeera

የምስሉ መግለጫ, ሳሜር አቡ ዳቃ

የአልጀዚራ የካሜራ ባለሙያ ሳሜር አቡ ዳቃ በእስራኤል የድሮን ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ አልፏል።

ሳሜር በወቅቱ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ በትምህርት ቤት ላይ የፈጸመችውን የአየር ጥቃት እየዘገበ ነበር።

ሳሜር ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በአካባቢው በነበረ የቦምብ ፍንዳታ ምክንያት ሕክምና ማግኘት ባለመቻሉ ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዳለፈ አልጀዚራ አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ በላከው መግለጫ ጋዜጠኛውን ለመርዳት አምቡላንስ ቢላክም "መንገዱ ጉዳት ስለገጠመው በወቅቱ ወደ ስፍራው መድረስ አልቻለም" ብሏል።

እናቱ የልጃቸውን ሞት ተከትሎ "ትናንት ሊሰናበተኝ መጥቶ ነበር። ተርቦ ሞተ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ልጁ ዛይን በበኩሉ "አምላክ ይማርህ አባ፣ ለሁሉም ደግ ሰው ነበርክ። ልጆችህን እንደ ጓደኛ ነበር የምታያቸው። ሁሉም ሰው ይወድሃል። አንተን ማጣችን ልባችንን ሰብሮታል" ሲል ሐዘኑን ገልጿል።

ሮይ ኢዳን

የፎቶው ባለመብት, October 7 Memorial

የምስሉ መግለጫ, ሮይ ኢዳን

ከእነዚህ በተጨማሪ ኢብራሂም ሙሃሬብ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. ተገድሏል።

ከፍልስጤማውያኑ ጋዜጠኞች በተጨማሪ ሮይ ኢዳን የተባለ 'ይኔት' ለተሰኘ የእስራኤል ጋዜጣ ይሠራ የነበረ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መጥፋቱ ተነግሮ ነበር።

ከአስር ቀናት ገደማ በኋላ አስክሬኑ ተገኝቷል።

አንደኛው ልጁ አቪጋሊ ኢዳነ በሐማስ ታግታ የነበረ ሲሆን ኅዳር ወር ላይ ተለቃለች።

ለጋዜጠኞች ደኅንነት እና መብት የሚከራከረው ሲፒጄ ቤተሰቡ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ኢዳን ሥራ ላይ ነበር ብሏል።

የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሪ አዙላይ የጋዜጠኛውን ግድያ አውግዘው "ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ እና ለግድያው ተጠያቂ የሆኑ ለፍትሕ እንዲቀርቡ" ጠይቀዋል።

ያኒቭ ዞሃር የተባለ እስራኤላዊ ጋዜጠኛ 'ሃዮም' ለተሰኘ ጋዜጣ ይሠራ ነበር። ሐማስ ደቡባዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት ከባለቤቱ እና ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር ተገድሏል።