የመንግሥታቱ ድርጅት እስራኤል አምስት የአልጄዚራ ጋዜጠኞችን መግደሏን አወገዘ

አስከሬኑን ከብበው የሚያለቅሱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA\Shutterstock

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በጋዛ ስድስት ጋዜጠኞችን የገደለውን የእስራኤል ጥቃት አስከፊ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ሲል አወገዘ።

እሁድ ዕለት እስራኤል በፈፀመችው የአየር ጥቃት አናስ አል ሻሪፍ የተባለውን ዘጋቢ ጨምሮ አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ተገድለዋል።

መገናኛ ብዙኃኑ ፍሪላንስ ጋዜጠኛውን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ባለሙያዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር ሻሪፍን ዒላማ በማድረግ መግደሉን ገልፆ "የሐማስ አሸባሪ ቡድን ህዋስ መሪ በመሆን ያገለግላል" በማለት ወንጅሎታል።

ሻሪፍ ይህንን ውንጀላ ከዚህ ቀደም ያስተባበለ ሲሆን እስራኤልም እዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ አላቀረበችም።

ቢቢሲ ሻሪፍ አሁን በጋዛ ካለው ግጭት በፊት ከሐማስ የመገናኛ ብዙኃን ቡድን ጋር የተወሰኑ ስራዎችን መስራቱን መረዳት ችሏል።

ጋዜጠኛው ከመሞቱ በፊት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በለጠፋቸው ጽሑፎች ሐማስን ተችቶ ነበር።

የሚዲያ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም ኳታርን እና ሌሎች አገራት ጥቃቱን አውግዘዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ቃል አቀባይ የዩኬ መንግሥት ግድያው "በጣም አሳስቦታል" በማለት ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የስታርመር ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እስራኤል ጋዜጠኞች ያለ ስጋት ደህነንነታቸው ተጠብቆ መስራት መቻላቸውን ማረጋገጥ አለባት ብለዋል።

የሻሪፍ የአልጀዚራው ዘጋቢ ሞሀመድ ቅርቂህ እና የካሜራ ባለሙያዎች ኢብራሂም ዛህር፣ ሞሀመድ ኑፋል እና ሞአመን አሊዋ የቀብር ስነ ስርዓት ሰኞ ዕለት ተፈጽሟል።

የአል ሺፋ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች በጥቃቱ የተገደለ ስድስተኛው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አል ኻልዲ እንደሚባል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ሮይተርስ በዘገባው በጥቃቱ ሌላ ሰው መሞቱንም ገልጿል።

የጋዛ ጎዳናዎች ለቀብር በወጡ ሰዎች ተጨናንቀዋል። አናስ አል ሻሪፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በርካታ ተከታዮች ያሉት በጋዛ እጅግ ታዋቂ ጋዜጠኛ ነበር።

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሻሪፍን ግድያ አጥብቆ አውግዟል።

ፎሬይን ፕሬስ አሶሲየሽን በበኩሉ ዒላማ ያደረገው ግድያ በጣም እንዳስቆጣው ተናግሯል። የእስራኤል ጦር የፍልስጤም ጋዜጠኞችን በተደጋጋሚ "ብዙ ጊዜ የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይኖራቸው በታጣቂነት ይፈርጃቸዋል" ሲል ተናግሯል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) በበኩሉ በጥቃቱ በጣም እንደደነገጠ እና እስራኤል በሻሪፍ ላይ ያቀረበችውን ውንጀላ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ተስኖታል ብሏል።

ድርጅቱ አክሎም "እስራኤል ጋዜጠኞችን የተረጋገጠ ማስረጃ ሳታቀርብ በአሸባሪነት የመወንጀል የረዥም ጊዜ የተሰነደ አሰራር አላት" ብሏል።

የእስራኤል ጦር ሻሪፍ የሐማስ አባል መሆኑን የሚያረጋግጡ ሰነዶች በጋዛ ተገኝተዋል ሲል ጠቁሟል።

እነዚህም ሰነዶች "የሰዎች ስም ዝርዝር፣የሽብርተኝነት ስልጠና ኮርስ ዝርዝሮች፣ የስልክ ማውጫዎች እና የደመወዝ ሰነዶችን" ያካተቱ ናቸው ብሏል።

ይፋ የሆነው ብቸኛ ማስረጃ በሰሜናዊው ጋዛ ሰርጥ የሐማስ ወኪሎችን ዝርዝር የሚያሳይ፣ የሐማስ ወኪሎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን እና የታጣቂው ቡድን የምሥራቅ ጃባሊያ ጦር የስልክ ማውጫ ነው የተባለው ክፍል የምስል ቅጂ ነው።

ቢቢሲ እነዚህን ሰነዶች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

እንዲሁም ሻሪፍ አሁን ባለው የጋዛ ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው ወይም የሐማስ ንቁ አባል ስለመሆኑ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላየም።

እስራኤል ለቀሪዎቹ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ግድያ እስካሁን ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልሰጠችም።

ሲፒጄ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 186 ጋዜጠኞች መገደላቸውን ተናግሯል።

ይህም ቡድኑ እአአ በ1992 እንደዚህ ያሉ መረጃዎችን መሰነድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለጋዜጠኞች እጅግ አስከፊው ጊዜ ነው ብሏል።

"እስራኤል ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁሉንም ሰላማዊ ዜጎች ማክበር እና መጠበቅ አለባት" ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት በኤክስ ገፁ ላይ በለጠፈው ጽሑፍ አስታውቋል።

"በጋዛ ለሁሉም ጋዜጠኞች በአፋጣኝ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ክልከላ ያሌለበት እንቅስቃሴ እንዲፈቀድ እንጠይቃለን።"

ባለፈው ወር ቢቢሲ እና ሌሎች ሦስት የዜና ኤጀንሲዎች ሮይተርስ፣ኤፒ እና ኤኤፍፒ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በመግለጽ "ስጋት እንደገባቸው" በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የእስራኤል መንግሥት ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች ወደ ጋዛ ገብተው በነፃነት እንዲዘግቡ አይፈቅድም።

በዚህም የተነሳ ብዙ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎቻቸውን ለማግኘት ጋዛ ውስጥ በሚኖሩ ጋዜጠኞች ላይ ጥገኛ ሆነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አንድ ሕጻንን ጨምሮ አምስት ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይህም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 101 ሕጻናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 222 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲ አርብ ዕለት እንዳስታወቀው ወደ ጋዛ የሚገባው የእርዳታ መጠን "የሰዎችን ግዙፍ ፍላጎቶች ለማሟላት ከሚያስፈልገው ዝቅተኛ ደረጃ በጣም ያነሰ ነው" ብሏል።

ባለፈው ወር በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የዓለም የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች "በአሁኑ ጊዜ በጣም የከፋ የረሃብ ሁኔታ እየታየ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል በጋዛ ረሃብ የለም በማለት የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች የመጣውን እርዳታ ከድንበር ላይ አንስተው አያከፋፍሉም ስትል ትከስሳለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባሉት የድንበር አካባቢዎች እርዳታ ለመውሰድ በሚሞክርበት ወቅት እንቅፋቶችን እና መዘግየቶችን ማጋጠማቸው ቀጥሏል ብሏል።

ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ እስራኤል መጠነ ሠፊ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ 61,430 ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።