የእስራኤላውያን ሠፋሪዎች ፍልስጤማውያንን ከዌስት ባንክ ለማስወጣት የሚያካሂዱት ዘመቻ ተባብሷል

የፎቶው ባለመብት, Oren Rosenfeld/BBC
ሜር ሲምቻ፤ እስራኤል እ.አ.አ ከ1967 ጀምሮ በወረረችው ዌስት ባንክ የሚገኘውን የሄብሮን ደቡባዊ ክፍል ሰፊ መሬት በሂደት እየቀየሩ ያሉት የአይሁድ ሠፋሪዎች ቡድን መሪ ነው።
አገር፣ ሃይማኖት እና ጦርነት ከፖለቲካ እና ከመሬት ባለቤትነት ጋር የማይነጣጠሉ በሆኑባት ምድር የሚኖረው ሲምቻ፤ ተልዕኮ ላይ እንደሆነ ያምናል።
እንደ እርሱ እምነት ተልዕኮው፤ ዌስት ባንክን ከፍልስጤማውያን እጅ አውጥቶ የአይሁዶች ምድር በማድረግ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስፈጸም ነው።
በአሁኑ ወቅት ይህ ተልዕኮው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው የሚል እምነትም አለው።
በአረቦች እና በአይሁዶች፤ በዮርዳኖስ ወንዝ እና በሜድትራንያን ባሕር መካከል ያለውን መሬት መቆጣጠር የተጀመረው፤ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ከአውሮፓ የመጡ ጽዮናውያን ፍልስጤም ውስጥ ማኅበረሰብ ለማቋቋም መሬትን መግዛት ሲጀምሩ ነበር።
ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሀኔታዎችን የቀየሩ ጉልህ ለውጦች ተካሂደዋል።
የቅርቡ ጉልህ ለውጥ የመጣው፤ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በሐማስ የተፈጸመውን አስከፊ ጥቃት እና በእስራኤል የተሰነዘረውን አውዳሚ ምላሽ ተከትሎ ነው።
ባለፉት 22 ወራት የተካሄደው ጦርነት፤ እንደ የ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሁሉ ለዓመታት እና ለትውልዶች የሚተርፍ መዘዝ የሚያስከትል ይመስላል። በየዛኔው ጦርነት እስራኤል ባደረገችው ወረራ ጋዛን ከግብፅ እንዲሁም ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና ዌስት ባንክን ከዮርዳኖስ ነጥቃለች።
በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ያስከተለው ጥፋት እና ግድያ መጠን ግን ዌስት ባንክ ውስጥ በውጥረት እና አመጽ ታጅቦ እየተካሄደ ያለውን መስፋፋት አደብዝዞታል።
ከመስከረም 2023 ጀምሮ እስራኤል በሕጋዊ የደህንነት እርምጃ ስም በዌስት ባንክ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርገው ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የሚኒስትሮች መግለጫዎች፣ እንደ ሲምቻ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአካባቢው መሪዎች እና በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ምስክርነት ላይ የተመሰረቱ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ጫናው የሰፊ አጀንዳ አካል ነው።
አጀንዳውም፤ በተወረሩ ግዛቶች ውስጥ የሚካሄዱትን የአይሁድ ሰፈራዎች በፍጥነት ማስፋፋት እንዲሁም ከእስራኤል ጎን የምትኖር የፍልስጤም ሀገርን የመፍጠር ተስፋን ለማጥፋት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Oren Rosenfeld/BBC
ፍልስጤማውያን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች፤ የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ፍልስጤማውያንን እንዲሁም የራሳቸውን ዜጎች የመጠበቅ ሕጋዊ ግዴታቸውን እየተወጡ አይደሉም ሲሉ ይከስሳሉ።
የፀጥታ ኃይሎቹ ሰፋሪዎች ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ፊታቸውን በማዞር ሳያበቁ እያገዙ መሆኑን ጭምር ያነሳሉ።
ከመስከረም 2016 ጀምሮ አክራሪ ብሔርተኛ የአይሁድ ሠፋሪዎች ዌስት ባንክ ውስጥ የሚፈጽሙት አመጻ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ፣ ኦቻ፤ ሠፋሪዎች በየቀኑ በአማካይ አራት ጥቃቶችን እንደሚያደርሱ ግምቱን አስቀምጧል።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት፤ በ1967 የተያዘውን የፍልስጤም ግዛት ሙሉ በሙሉ መውረር ሕገ ወጥ መሆኑን የሚያስገነዝብ የምክር ሀሳብ ሰጥቷል።
እስራኤል የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት አመለካከት ውድቅ በማድረግ፤ በተወረሩ ግዛቶች ላይ ሰፈራን የሚከለክሉት የጄኔቫ ኮንቬንሽኖች በዚህ ሁኔታ ላይ ተግባራዊ አይሆኑም ብላለች።
የዚህ አመለካከት ግብ በእስራኤል አጋሮች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ክርክር የሚነሳበት ነው።
የአይሁድ ሰፋሪዎች ቡድን መሪው ሲምቻ ግን በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያስረዱ ክሶችን ውድቅ አድርጓል።
የእርሱ ቡድን በያዛቸው ኮረብታዎች ላይ ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩ እና በሸለቆዎች ውስጥ የወይራ ዛፎቻቸውን የሚንከባከቡ አብዛኛዎቹ አረብ አርሶ አደሮች ለቅቀው የመሄዳቸውን ጉዳይ ግን በደስታ አንስቶታል።
በመስከረም 2016 ዓ.ም. የተፈፀመውን የሐማስ ጥቃት እና ያንን የተከትሎ የመጣውን የእስራኤል ምላሽ እንደ እጥፋት ይቆጥረዋል።
"ብዙ ነገር እንደተለወጠ፣ መሬታችን ላይ የሚገኘው ጠላት ተስፋ እንዳጣ አስባለሁ። [ጠላት] እየለቀቀ መሆኑን መገንዘብ ጀምሯል፣ ባለፈው አንድ ዓመት ወይም አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ የተለወጠው ይህ ነው" ይላል።
"ዛሬ በረሃማው መሬት ላይ በእግር መጓዝ ትችላለህ፤ ማንም አአድብቶ መጥቶ ሊገድልህ አይሞክርም። አሁንም በዚህ ምድር ውስጥ መገኘታችንን ለመቃወም የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ፤ ነገር ግን ጠላት ይህንን በዝግታ መገንዘብ ጀምሯል። እዚህ ምንም የወደፊት ተስፋ የላቸውም" በማለት አቋሙን ይገልጻል።
"እውነታው ተለውጧል። ለምንድን ነው ለእነዚያ ፍልስጤማውያን ይህን ያህል ፍላጎት ያላችሁ? ብዬ አንተን እና የዓለም ሕዝብን እጠይቃለሁ። ለምን ስለ እነርሱ ትጨነቃላችሁ? አንድ ትንሽ አገር ብቻ ናቸው"
"ስለ ፍልስጤማውያን ፍላጎት የለኝም። እኔ የማስበው ስለ ሕዝቤ ነው" ሲል ሲምቻ ተናግሯል።
ሲምቻ፤ ፍልስጤማውያን ከኮረብታዎች አቅራቢያ ከነበሩት መንደሮች እና እርሻዎች ለቅቀው የወጡት፤ እግዚአብሔር መሬቱን ለእነሱ ሳይሆን ለአይሁዶች እንዳሰበው ስለተገነዘቡ ነው ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ቡድን ግን ሐምሌ ላይ ከዚህ የተለየ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ "በሰፊው እየተስፋፋ እንደሆነ እየተገለጸ ባለው ማስፈራራት፣ አመፅ፣ የመሬት ወረራ፣ የኑሮ ሁኔታ ውድመት እና በዚህም የተነሳ ማህበረሰቦች በግፍ መፈናቀላቸው በጣም ያሳስበናል። ይህም ድርጊት ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው እየነጠቀ እና የምግብ ዋስትናቸውን እያዳከመ ነው የሚል ስጋት አለን" ብሏል።

"በውንጀላ እየቀረቡ ያሉት የአመፅ ድርጊቶች፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም የመሬት እና ሀብት ክልከላ ስርዓታዊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያሳያሉ" ሲልም ስጋቱን ገልጿል።
ሲምቻ፤ በዌስት ባንክ የአይሁድ ሰፈራዎችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኙ ሌሎች በርካታ ሰዎች ሁሉ በርካታ እቅዶች አሉት።
የሐማስ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት፤ ይኖር የነበረው ወደ ሙት ባህር በሚወስድ የአይሁድ ምድረ በዳ ላይ በሚታይ ኮረብታ ላይ አነስተኛ ቁጥር ካለው ቡድን ጋር ነበር።
ከዚያ ጊዜ ወዲህ የማኅበረሰቡ አባላት ቁጥር ወደ 200 ገደማ መስፋቱን እና በሦስት ኮረብታዎች ላይ እንደሚገኙ ያስረዳል።
ሲምቻ፤ 'ሂልቶፕ ዩዝ' በመባል የሚጠራው እና ፍልስጤማውያን ላይ በሚያደርሰው የአመጽ ማሳደድ የሚታወቀው ጽንፈኛ የሰፈራ እንቅስቃሴ አካል ነበር።
በተወረሩት ግዛቶች ውስጥ የሰፈሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን እንደ ሲምቻ አይደሉም።
በእነዚህ አካባቢዎች የሰፈሩት በርዕዮተ ዓለማዊ እና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ሳይሆን በርካሽ ንብረት ማፍራት ስለሚቻል ነው።
በተወረሩ አዲስ ግዛቶች ውስጥ አይሁዳውያንን የማስፈር ዕቅድ ያለው የእስራኤል ፕሮጀክት የተጀመረው ከ1967ቱ ድል በኋላ በቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።
ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ የመጡት ተከታታይ የእስራኤል መንግሥታት እና አንዳንድ ሀብታም ደጋፊዎቻቸው አሁን ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በዌስት ባንክ የሚገኙ 700,000 የሚሆኑ የእስራኤል አይሁዶች ያሉበት ደረጃ እንዲደርሱ ከፍተኛ ገንዘብ እና ጉልበት አፍስሰዋል።
ከ1991 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት እንኳ አብዛኛው የዌስት ባንክ ክፍል ተለውጧል። በአካባቢዎቹ የተካሄዱት ትልልቅ ሰፈራዎች ትናንሽ ከተሞች መስለዋል።
የእስራኤል መንግሥት፤ በዌስት ባንክ በሚገኙ አይሁዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም በመንገዶቹ ዙሪያ ያለውን መሬት መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ይላል።
በወረራ ጫና ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ብዙውን ጊዜ መሬታቸውን ለመጎብኘት ወታደራዊ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን አንዳንዴም የሚፈቀድላቸው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ፍልስጤማውያን አርሶ አደሮች በቫን መኪናዎች ወይም አህያ ላይ ተጭነው ወደ ዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሲጓዙ መመልከት የተለመደ ነገር ነበር።
አሁን ግን በዌስት ባንክ በተለይም እንደ ምሥራቃዊ 'ሲሆን' ባሉ ሰፈራዎች ፍልስጤማውያን ዓይን ውስጥ አይገቡም።
ጦርነቱ ከጀመረበት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ወዲህ በዌስት ባንክ የሚካሄደው የሰፈራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
ይህንን ተግባር የሚደገፈውም እንደ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ቤን ጋቪር ያሉ በአገሪቱ መንግሥት ካቢኔ ውስጥ የሚገኙ አክራሪዎች እንዲሁም እንደ የሪሊጂየስ ዛዮኒስት ሙቭመንት ፓርቲ መሪ ቤዛሌል ስሞትሪክ ባሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ነው።
ከመስከረሙ ጥቃት ወዲህ የእስራኤል ሠራዊት በወሰደው እርምጃ የተነሳ ፍልስጤማውያን በሰፋሪዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ቀንሷል። በተቃራኒው ደግሞ ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

'ብሬኪንግ ዘ ሳይለንስ' የተባለ ሰፈራዎችን የሚቃወም ድርጅት መስራች የሆነው ይሁዳ ሻውል፤ በሠፋሪዎች እና በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ መምጣቱን ይናገራል።
በጋዛ የተካሄደው ጦርነት፤ የመከላከያ ሠራዊቱ የጀርባ አጥነት የሆኑት ተጠባባቂ ወታደሮች በእስራኤል ታሪክ ከፍተኛ በሆነ መጠን እንዲሰማሩ አድርጓል።
ብዙ እስራኤላዊያን ጦሩን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ሲባልም በዌስት ባንክ የሚገኙ ብርጌዶች ከሠፋሪዎች የተውጣጡ አባላት ያሉት የመከላከያ ክፍሎችን አቋቁመዋል።
ሻውል፤ "አሁን ሠፋሪዎቹ ወታደር ናቸው። በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት ሠፋሪዎቹ ናቸው" ይላል።
ከሦስት እና አራት ዓመታት ገደማ በፊት ከከብት አርቢ ፍልስጤማውያን ማኅበረሰቦች አቅራቢያ በሚገኝ ኮረብታ ላይ ሰፍረው የነበሩ እና ፍልስጤማውያንን ለማስወጣት ድንጋይ ሲወረውሩ እና ድብደባ ሲፈጽሙ የነበሩ ሠፋሪዎች አሁን አካባቢውን የሚቆጣጠሩ ወታደሮች ወይም የጦር መኮንኖች መሆናቸውን ይናገራል።
"ስለዚህ ወደ አንድ ፍልስጤማዊ መጥቶ፣ 'እቃህን ሰብስበህ ለመሄድ 24 ሰዓት አለህ፤ አለበለዚያ እገድልሃለሁ' ቢለው፣ ፍልስጤማዊው ጥበቃ ሊያደርግለት የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል" በማለት ያስረዳል።
ሻውል እስራኤል ሁለት አማራጮች እንዳሏት ያምናል።
አንዱ አማራጭ፤ "ይህ መንግሥት እየተከተለ ያለው የመፈናቀል፣ የበደል፣ የግድያ፣ የፍልስጤማውያንን ሕይወት የማጥፋት አቅጣጫ ነው" የሚለው ሻውል ይህ አካሄድ በመጨረሻም የብዙ ሕዝብ መፈናቀልን እንደሚያስከትል ይከራከራል።
ሁለተኛው አማራጭ፤ "ከእስራኤል ጎን ፍልስጤም የምትገኝበት እና የሁለቱም ሕዝቦች መብት እና ክብር እንዲኖራቸው የሚያደርገው የሁለት አገር አማራጭ ነው። ያሉን ብቸኛ ምርጫዎች ሁለቱ አማራጮች ናቸው። አሁን አንተ እና እኛን የሚመለከት ማንኛውም ሰው የትኛውን እንደሚደግፍ መምረጥ አለበት" ይላል።















