አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች እስራኤል በጋዛ ከተማ በፈፀመችው ጥቃት ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Al Jazeera
እስራኤል በጋዛ ከተማ አልሺፋ ሆስፒታል አቅራቢያ በፈፀመችው ጥቃት አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች መገደላቸውን መገናኛ ብዙኃኑ አስታወቀ።
ጋዜጠኞቹ አናስ አል ሻሪፍ እና ሞሐመድ ቅሬቅህ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያዎቹ ኢብራሂም ዛሂር፣ ሞሐመድ ኑፋል እና ሞአሚን አሊዋ ሲሆኑ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በሆስፒታሉ ዋና በር ላይ ለጋዜጠኞች ተብሎ በተዘጋጀ ድንኳን ውስጥ ነበሩ ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊትን በአል ሻሪፍ እንዲሁም በጋዛ በሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ "የቅስቀሳ ዘመቻ" ተፈጽሟል በሚል አልጀዚራ አውግዞ ነበር።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የእስራኤል መከላከያ ኃይል አናስ አል ሻሪፍን መግደሉን አረጋግጦ፣ "የሐማስ አሸባሪ ቡድን የሕዋስ መሪ ሆኖ አገልግሏል" ሲል በቴሌግራም ገጹ ላይ ጽፏል።
የእስራኤል መከላከያ ስለተገደሉት ሌሎች ጋዜጠኞች ምንም ያለው ነገር የለም።
የአልጀዚራ ማኔጂንግ ኤዲተር ሞሐመድ ሞዋድ ለቢቢሲ እንደተናገረው አል ሻሪፍ በአካባቢው እንዲዘግብ ፈቃድ ያለው ጋዜጠኛ ሲሆን፣ ዓለም በጋዛ ሰርጥ ምን እየተፈጠረ እንዳለ እንዲያውቅ "ብቸኛው ድምጽ" ነበር ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ወደ ግዛቲቱ ገብተው እንዲዘግቡ አልፈቀደችም።
ስለዚህ ብዙ መገናኛ ብዙኃን መረጃ ለማግኘት በጋዛ ውስጥ ባሉ የአገር ውስጥ ዘጋቢዎችን ይጠቀማሉ።
ሞዋድ አክሎም እስራኤል የፈፀመችውን ጥቃት አስመልክቶ "በድንኳናቸው ውስጥ ሳሉ ዒላማ ተደርገዋል፣ ግጭት በሚካሄድበት አካባቢ ዘገባ እየሠሩ አልነበሩም" ብሏል።
"እውነታው የእስራኤል መንግሥት ማንኛውም መገናኛ ብዙኃን ከጋዛ የሚያቀርበውን የትኛውንም ዘገባ ዝም ለማሰኘት መፈለጉ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ይህ በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከዚህ በፊት አይቼው የማላውቀው ነገር ነው።"
የ28 ዓመቱ አል ሻሪፍ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በኤክስ ገፁ ላይ እስራኤል በጋዛ ከተማ ውስጥ እየፈጸመችው ስላለው ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ ማስጠንቀቂያ ለጥፎ ነበር።
መሞቱ ከተዘገበ በኋላ የታተመው ልጥፍ አስቀድሞ በጓደኛው ተጽፎ የተለጠፈ ይመስላል።
በቢቢሲ ቬሪፋይ የተረጋገጡ ሁለት ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ሰዎች የተገደሉትን ጋዜጠኞች አስከሬን ተሸክመው ሲሄዱ ያሳያሉ።
አንዳንዶች የሞሐመድ ቅሬቅህን ስም እየጮሁ የሚጠሩ ሲሆን፣ አንድ ጋዜጠኛ መሆኑን የሚለይ ልብስ የለበሰ ሰው ደግሞ አንዱ አስከሬን የአነስ አል ሻሪፍ መሆኑን ተናግሯል።
በሐምሌ ወር የአልጀዚራ ሚዲያ ኔትዎርክ የእስራኤል ጦር "ያለማቋረጥ የሚያካሄደውን፤..በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ጋዜጠኞቹ እና ዘጋቢዎቹ ላይ ያነጣጠረ የቅስቀሳ ዘመቻ" በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።
"ኔትወርኩ ይህንን ቅስቀሳ በአካባቢው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ዒላማ ለሚያደርግ ጥቃት አስቀድሞ ምክንያት የመፈለግ አደገኛ ሙከራ እንደሆነ አድረጎ ይቆጥረዋል" ሲል አክሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል መግለጫ አል ሻሪፍን ጋዜጠኛ በመምሰል እንዲሁም "በእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች እና የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሮኬት ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በማድረግ ተጠያቂ ነው" ብሏል።
ከዚህ ቀደም ያለውን ወታደራዊ ግንኙነት የሚያረጋግጥ የወሰዳቸውን "የሽብርተኝነት ሥልጠናዎችን ዝርዝሮች" ያካተተ "የደኅንነት መረጃ" ይፋ ማድረጉን ገልጿል።
"ከጥቃቱ በፊት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እርምጃዎች ተወስደዋል፤ ከእነዚህም መካከል ዒላማውን የሚለይ የጦር መሳሪያ፣የአየር ላይ ክትትል እና ተጨማሪ የደኅንነት መረጃ" ሲል በመግለጫው ላይ ገልጿል።
ለጋዜጠኞች ደኅንነት እንደሚሟገተው ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ መረጃ ከሆነ እስራኤል በመስከረም 2015 ዓ.ም. በጋዛ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ 186 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።















