በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል የቀድሞ ባለሥልጣናት ትራምፕ የጋዛ ጦርነትን እንዲያስቆሙ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል የቀድሞ የደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ 600 የሚሆኑ ጡረታ የወጡ የደኅንነት ባለሥልጣናት ቡድን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የጋዛን ጦርነት በአስቸኳይ እንድታቆም ግፊት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፉ።
"በእኛ ሙያዊ ብያኔ መሠረት ሐማስ ከአሁን በኋላ የእስራኤል ስትራቴጂያዊ ስጋት አይሆንም" ሲሉ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
"አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያምንዎታል፤ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና መንግሥታቸውን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የመምራት አቅምዎትን ይጨምራል፤ ጦርነቱ ይቁም፣ ታጋቾች ይመልሱ፣ ስቃዩ ያቁሙ" ሲሉ ጽፈዋል።
ይህ የተማፅኖ ጥያቄያቸው የመጣው ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር በተዘዋዋሪ የሚያደርጉት የተኩስ አቁም ድርድር በመቋረጡ በጋዛ የሚደረገውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማስፋት ግፊት እያደረጉ መሆኑ በተዘገበበት ወቅት ነው።
ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደች ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ከ60,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ሰኞ እንዳስታወቀው፣ እሁድ ዕለት በጋዛ ቢያንስ 94 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ በእስራኤል ጥቃት የተነሳ ሞተዋል።
ቢያንስ 24 ሰዎች እርዳታ ለመቀበል በሄዱበት ወቅት መገደላቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ዘገባዎች በየቀኑ ማለት በሚያስደፍር መልኩ ቢሰሙም ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ ገብተው እንዳይዘግቡ በእስራኤል በመከልከላቸው ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።
እስራኤል ወደ ጋዛ በሚገቡ የእርዳታ ቁሳቁሶች ላይ በጣለችው ጥብቅ እገዳ የተነሳ ግዛቱ ከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ ቁሰቀቁሶች እጥረት አጋጥሞታል።
ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 93 ሕጻናትን ጨምሮ 180 ሰዎች በምግብ እጥረት መሞታቸውን ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፉ ኤጀንሲዎች በጋዛ "በጣም የከፋው የረሃብ ሁኔታ እየታየ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቀድሞ የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ይፋ የሆነው ሁለት በረሃብ የተጎዱ እስራኤላውያን ታጋቾችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በሐማስ እና በእስላማዊ ጂሃድ ታጣቂዎች ከተለቀቁ በኋላ ነው።
ቪዲዮዎቹ በእስራኤላውያን እና በምዕራባውያን መሪዎች ዘንድ በሰፊው ተወግዘዋል።
ቪዲዮዎቹ ከተለቀቁ በኋላ ኔታንያሁ የሁለቱ ታጋቾችን ቤተሰቦች ያነጋገሩ ሲሆን፣ በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን በሙሉ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት "ያለማቋረጥ እና ያለመታከት እንደሚቀጥል" ተናግረዋል።
ነገር ግን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን አንድ የእስራኤል ባለሥልጣንን ጠቅሰው ኔታንያሁ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እየሠሩ ያሉት "ሐማስን በወታደራዊ ዘመቻ በማሸነፍ ነው" ሲሉ ዘግበዋል።
ፍልስጤማውያን በረሃብ ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጦት እንደሚሞቱ የሚገልጹ ዘገባዎች በዓለም ላይ ድንጋጤን በፈጠሩበት በአሁኑ ወቅት፣ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ማስፋት፣ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩትን የእስራኤል አጋሮች የበለጠ ሊያስቆጣ ይችላል።
የታጋቾችን ቤተሰቦች የሚደግፈው ዋናው ቡድን "ኔታንያሁ እስራኤልን እና ታጋቾቹን ወደ ጥፋት እየመሯቸው ነው" በማለት አዲስ ወታደራዊ ጥቃት የመፈፀሙን ሃሳብ አውግዟል።
ይህ አመለካከት በቀድሞው የሞሳድ ዋና አዛዥ ታሚር ፓርዶ፣ በቀድሞው የሺን ቤት ኃላፊ አሚ አያሎን፣ በእስራኤል የአገር ውስጥ መረጃ አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ባራክ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ሞሼ ያሎን እና ሌሎችም ለትራምፕ በጻፉት ደብዳቤ ላይ በግልጽ ተጠቅሷል።
"መጀመሪያ ላይ ይህ ጦርነት ፍትሃዊ ጦርነት ነበር፤ የመከላከል ጦርነት ነበር። ነገር ግን ሁሉንም ወታደራዊ ዓላማዎች ስናሳካ ይህ ጦርነት ፍትሃዊ ጦርነት መሆኑ አቆመ" ብለዋል አያሎን።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቀድሞዎቹ የእስራኤል ከፍተኛ አመራሮች፣ የአሁኖቹን የእስራኤል የደኅንነት አዛዦች ታጋቾችን በሰላም ማስመለስ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሲወተውቱ ነበር።
"የጋዛ ጦርነትን አቁም! የእስራኤል ትልቁ የቀድሞ መከላከያ ጄነራሎች እና ሞሳድ ቡድን፣ ሺን ቤትን፣ፖሊስ እና ዲፕሎማቲክ ዘብን በመወከል የጋዛ ጦርነትን እንዲቆም እንጠይቃለን። በሊባኖስ አደርጋችሁታል። በጋዛም ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጽፈዋል።
በጋዛ የደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመት እና የፍልስጤማውያን ስቃይ ዓለም አቀፍ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ እስራኤልንም እያደገ ለመጣ ዓለም አቀፍ መገለል አጋልጧታል።
በዓለም ዙሪያ በእስራኤል ዙሪያ የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከዕለት ወደ ዕለት አሉታዊ እየሆነ መጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥታት በእስራኤል ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት እያደረጉም ይገኛሉ።
ነገር ግን ትራምፕ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ምን ዓይነት ጫና እንደሚያደርጉ ግልፅ አይደለም ።
ምንም እንኳ ኔታንያሁ በጋዛ ረሃብ የለም ብለው ቢክዱም፣ ትራምፕ ግን ባለፈው ሳምንት በጋዛ "እውነተኛ ረሃብ" መኖሩን በይፋ የተናገሩ ቢሆንም አጋራቸውን ግን ያለማቋረጥ ይደግፋሉ።















