በእስራኤል የተገደለው እውቁ የጋዛ ጋዜጠኛ አናስ አል ሻሪፍ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
እሁድ ዕለት በጋዛ አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
ከእነዚህም መካከል የእስራኤል ዘመቻ በጋላ ላይ ከተጀመረ አንስቶ በዋናነት ስለ ጦርነት ሲዘግብ የነበረው የ28 ዓመቱ ጋዜጠኛ አናስ አል ሻሪፍ ይገኝበታል።
በጥቃቱ የተገደሉ ሌሎቹ አራት ጋዜጠኞች ሞሐመድ ቄርቅህ እና የካሜራ ባለሙያ ኢብራሂም ዛህር፣ ሞሐመድ ኖፋል እና ሞአሚን አሊዋ እንደሆኑ አልጀዚራ አስታውቋል።
በዚህ ጥቃት ሌሎች ሁለት ሰዎችም መገደላቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ገልጿል። የሆስፒታል ምንጮች ሞሐመድ አል ካሊድ የተባለ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ከሟቾች መካከል እንደሆነም ተናግረዋል።
የጋዜጠኞች ድንኳን ላይ ያነጣጠረው ይህ ጥቃት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ ውግዘት የገጠመው ሲሆን፤ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ ኳታር እንዲሆም የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ተሟጋች ቡድነት አውግዘውታል።
እስራኤል አል ሻሪፍ "የሐማስ ሽብር ቡድን ሕዋስ አዛዥ" ነበር ያለች ቢሆንም ይህን ክሷን የሚደግፍ እዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ አላቀረበችም። ይህን ውንጀላ አልጀዚራ እና የሚዲያ መብት ተሟጋች ቡድኖች ውድቅ አድርገውታል።
አል ሻሪፍ ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት ከሐማስ የሚዲያ ቡድን ጋር ይሠራ እንደነበር ቢቢሲ ተረድቷል።
አናስ አል ሻሪፍ በጦርነቱ በጋዛ የአልጀዚራ በጣም ታዋቂ ዘጋቢ ሆኗል።
በተጨናነቀው የጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ጃባሊያ ውስጥ የተወለደው ጋዜጠኛው ለአልጀዚራ ለሁለት ዓመታት መሥራቱን ተቋሙ አስታውቋል።
የአልጀዚራ እንግሊዝኛ ዜና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ሳሌህ ንግም "ለሁለት ዓመት ለሚዘልቅ ጊዜ በጋዛ ውስጥ በየቀኑ ስላለው የሕዝቦች ሁኔታ እና በሚፈፀሙ ጥቃቶች ዙሪያ እየዘገበ ነበር" ብለዋል።
ባለትዳር እና የአራት ዓመት ሴት ልጅ እና የአንድ ዓመት ወንድ ልጅ አባት የሆነው አናስ፤ እስራኤል ለቀው እንዲወጡ የሰጠችውን ትዕዛዝ ባለመቀበል በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ሲዘግብ ለረጅም ጊዜ ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ ቆይቷል።
ከባለቤቱ ጋር በሚጋራዊ የኢንስተግራም አካውንት ባለፈው ጥር ላይ የለጠፈው ምሥል አል ሻሪፍ ከልጆቹ ጋር በፈገግታ ተሞልቶ ያሳያል።
የምሥሉ መግለጫ ከ15 ወራት ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆቹን ሲያገኝ እንደሆነ ይገልፃል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አናስ አል ሻሪፍ በቀጥታ ሥርጭቶች በተደጋጋሚ ሽፋን በመስጠት በጋዛ ስላለው ቡኔታ በስፋት ዘገባዎች ሠርቷል።
በአውሮፓውያኑ 2024 በጋዛ ከተማ በአየር ጥቃት የተገደሉት የአልጀዚራ ስመ ጥር ወኪል እስማኢል አል ጓል እና የካሜራ ባለሙያው ራሚ አል ሪፊን ጨምሮ በባልደረቦቹን ዒላማ ስላደረጉ ጥቃቶችም ዘግቧል።
የቤተሰቡ ቤት በእስራኤል ጥቃት ሲፈፀምበት አባቱ ታኅሣሥ 2023 ተገድለዋል።
እሱም ከመገደሉ ከሰዓታት በፊት በጋዛ ከተማ ስለተፈፀመ ከባድ ድብደባ በቀጥታ ዘገባ አስተላልፏል።
የአልጀዚራ የአርታኢያን ኃላፊ ሞሐመድ ማዋድ "በጋዛ ከተማ የቀረው ብቸኛ ድምፅ" ሲል ገልፆታል።
የአልጀዚራ የአረቢኛ ቋንቋ ጣቢያ ሌላ ኃላፊ ራሺድ ፋኪህ ለቢቢሲ አል ሻሪፍ ስኬታማ ጋዜጠኛ እና የማኅበራዊ ትስስር ገፁ በመቶ ሺህዎች ተከታዮች እንዲያገኝ ያስቻለው "ደፋር፣ ታታሪ እና ሐቀኛ" በመሆኑ ነው ብሏል።
"ታታሪነቱ ሌሎች ጋዜጠኞች ወዳልደረሱበት ስፍራ ወስዶታል፤ በተለይም ጭፍጨፋዎችን የተመለከቱ። ታማኝነቱ እንደ ጋዜጠኛ ለመልዕክቱ ሐቀኛ እንዲሆን አድርጎታል።"
"የጋዛውያንን ደምፅ ከማስተጋባት ባለፈ ሌላ ምርጫ እንደሌለው ይሰማው ነበር። እነሱ እንደሚኖሩት ተመሳሳይ ከባድ ሕይወት እየኖረ ነበር። በረሃብ መሰቃየት፣ የቤተሰቦቹን ሐዘን መሰማት. . ."
"አባቱ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ነው የተገደሉት። በዚህ መንገድ ሞትን በመሸከም፣ በህመም እና በመቋቋም እንደ ሁሉም የጋዛ ነዋሪ ነው። በሞት ፊትም ሆኖ ወደ ኋላ አላፈገፈገም። ምክንያቱም ይህ መነገር ያለበት ታሪክ ነውና" በማለት ስለ አናስ ተናግሯል።
እንደ አናስ የሁለት ልጆች አባት የሆነው ሞሐመድ ቄሪህ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘጋቢ የነበረ ሲሆን፣ ለወራት ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ ነበር።
እሁድ ዕለት ከመገደሉ ከደቂቃዎች በፊት በቀጥታ ሲዘግብ እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል።
ሐማስ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እያካሄደችው ባለው ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ 200 የሚሆኑ ጋዜጠኞች መገደላቸውን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን አስታውቋል።
የአልጀዚራው ፋኪህ "በጋዛ እየተፈፀመ ያለውን ለመደበቅ" የእስራኤል ጦር ጋዜጠኞችን ከመግደሉ በፊት የውሸት ታሪክ እያቀረበ ነው ሲል ወቅሷል።
እስራኤል ከዚህ ቀደም ጋዜጠኞች ላይ ማነጣጠሯን አስተባብላለች።















