የጋዛ ከተማን ወረራ የጀመረችው እስራኤል በግብፅና በኳታር የቀረበውን ስምምነት እንደማትቀበል አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በግብፅና በኳታር የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበሉ ተናግረው፤ "ለእስራኤል ተቀባይነት ባለው መልኩ" የቀሩ ታጋቾች በሙሉ እንዲለቀቁ እና የጋዛ ጦርነት እንዲቋጭ የሚያስችል ድርድር እንዲጀመር መመሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢያኔያቸው ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ተቃውሞ የገጠመውን የጋዛ ከተማን ወረራ ማጽደቁን ሐሙስ ምሽት ለወታደሮቻቸው ተናግረዋል።
ሐማስ በኳታር እና በግብጽ አሸማጋይነት የቀረበውን ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ሰኞ ዕለት መቀበሉን አስታውቋል። ይህ ስምምነት በጋዛ ከቀሩት ታጋቾች ግማሾቹን እንዲለቀቁ የሚያስችል ነው።
ኔታንያሁ ይህንን ሐማስ የተቀበለውን ስምምነት እንዳልተቀበሉት በይፋ ተናግረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት እስራኤል የጋዛ ጦርነት እንዲቆም የምትስማማው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ እንደሆነ መግለጫ አውጥቷል።
እነዚህም "ሁሉም ታጋቾች ሲለቀቁ ሃማስ ትጥቅ ሲፈታ፣ ጋዛ ከወታደራዊ ትጥቅ ውጭ ስትሆን፣ እስራኤል የጋዛን ዙሪያ ስትቆጣጠር እና በጋዛ ሃማስ እና ዌስትባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ውጭ የሆነ አገዛዝ መምጣት ሲችል ብቻ ነው" ብሏል።
የእስራኤል ሚዲያ የአገሪቱ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ድርድር የሚካሄድበት ስፍራ ከተወሰነ በኋላ ተደራዳሪዎች ለአዲስ ውይይት እንደሚላኩ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋዛን ወረራ በበላይነት የሚያየውን በእስራኤል የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤት ሐሙስ ምሽት በጎበኙበት ዕለት "ሁሉንም ታጋቾቻችንን ለማስለቀቅ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር መመሪያ ሰጥቻለሁ" ብለዋል።
አክለውም "የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የጋዛ ከተማን እንዲቆጣጠር [እንዲወር] እና ሐማስን እንዲያሸንፍ የወጣውን ዕቅድ አጽድቄያለሁ ለማለት ነው የመጣሁት" ሲሉ ተናግረዋል።
"እነዚህ ሁለት ጉዳዮች፤ ሐማስን ማሸነፍ እና ሁሉንም ታጋቾቻችን ማስለቀቅ መሳ ለመሳ ይሄዳሉ" ቀጣዪ ውይይት ምን ሊሆን እንደሚችል ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ኔታንያሁ ተናግረዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ታጋቾችን በከፊል ለመልቀቅ ያስችላል የተባለውን የተኩስ አቁም ስምምነትን ተቃውመዋል።
ሐማስ በበኩሉ ኔታንያሁ የአሸማጋዮችን የተኩስ አቁም ሃሳብ ችላ በማለት ሆን ብለው ስምምነቱን እያደናቀፉ ነው ሲል መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል ከ50 ታጋቾች መካከል 20ዎቹ በህይወት እንዳሉ ታምናለች።
የእስራኤል ጦር የመጀመሪያ ዙር ወረራ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ሐሙስ ዕለት በጋዛ ምስራቃዊ ስፍራዎች ከፍተኛ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ፍልስጤማውያን ተናግረዋል።
ጦሩ ወታደሮቹ ከመግባታቸው በፊት የህክምና ባለሙያዎች፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም አንድ ሚሊዮን የሚሆነው የጋዛ ነዋሪ በሙሉ ቀየውን ለቆ ወደ ደቡባዊ ስፍራ መጠለያዎች እንዲገባ አስጠንቅቋል።
በጋዛ በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር " የቀረውን የጤና ስርዓት የሚያንኮታኩት እርምጃ" መሆኑን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የረድዔት ድርጅቶች ለመንቀሳሳቅ የማይችሉትን ወይም የማይፈልጉትን ለመርዳት ቃል ገብተዋል።
ኔታንያሁ እስራኤል መላውን የጋዛ ሰርጥ የመቆጣጠር [የመውረር] ፍላጎት እንዳላቸው ከሐማስ ጋር በተዘዋዋሪ ሲደረግ የነበረው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ አስታውቀው ነበር።















