የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ማጥቃት መጀመሩን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የእስራኤል ጦር የጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ እና ለመውረር በማቀድ "የመጀመሪያ እርምጃ" ያለውን የምድር ጥቃት መጀመሩን ተናገረ።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ ማክሰኞ ዕለት ያፀደቁት እና በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ለፀጥታው ካቢኔ እንደሚቀርብ ለሚጠበቀው ዕቅድ መሠረት ለመጣል የአገሪቱ ወታደሮች በዘይቶን እና ጃባሊያ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የጦሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በምድር ውጊያው ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ወታደሮች በዘመቻው ላይ እንዲያተኩሩ ወደ 60,000 የሚጠጉ ተጠባባቂ ኃይሎች በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ሐማስ እስራኤል "በንፁኃን ዜጎች ላይ የምታካሄደውን አረመኔያዊ ጦርነት" ለመቀጠል የተኩስ አቁም ስምምነቱን አደናቅፋለች ሲል መወንጀሉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በጋዛ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለቅቀው እንዲወጡ እና በደቡብ ጋዛ ወደሚገኘው መጠለያ እንደሚያመሩ ይታዘዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብዙ የእስራኤል አጋሮች ዕቅዱን አውግዘዋል።
ረቡዕ ዕለት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ሁለቱንም ሕዝቦች ወደ ቀውስ እንዲሁም አጠቃላይ ቀጠናውን ወደ ማያባራ የጦርነት አዙሪት ውስጥ የመክተት አደጋ አለው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በበኩሉ ተጨማሪ መፈናቀል እና የእርስ በርስ ግጭት መባባስ በጋዛ 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ "አሁን ያለውን አስከፊ ሁኔታ ሊያባብስ ይችላል" ብሏል።
ባለፈው ወር የእስራኤል መንግሥት ከሐማስ ጋር በተዘዋዋሪ እያደረገ የነበረው የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ መላውን የጋዛ ሰርጥ የመውረር ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።
ረቡዕ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፊ ደፍሪን በቴሌቭዥን በተላለፈ መግለጫቸው ላይ ሐማስ ከ22 ወራት ጦርነት በኋላ "ተመትቷል እንዲሁም ተጎድቷል" ብለዋል።
አክለውም "የአሸባሪው ድርጅት የመንግሥት እና ወታደራዊ ሽብር ምሽግ በሆነችው በጋዛ ከተማ በሐማስ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አጠናክረን እንቀጥላለን።"
"ከመሬት በላይ እና በታች ባሉ የሽብር መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በማጠናከር ሕዝቡ በሐማስ ላይ ያለውን ጥገኝነት እናቋርጣለን።"
ዴፍሪን አክለውም የእስራኤል መከላከያ ስራውን ለመጀመር "እየጠበቀ አይደለም" ብለዋል።
"የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ ጀምረናል፤ እናም አሁን የእስራኤል ወታደሮች የጋዛ ከተማን ዳርቻ እየተቆጣጠሩ ነው።"
በዘይቶን አካባቢ ሁለት ብርጌዶች የምድር ውጊያውን እያካሄዱ እንደነበር ጠቅሰው የጦር መሳሪያ የያዘ የመሬት ውስጥ ዋሻ ማግኘታቸውን እና ሦስተኛው ብርጌድ ደግሞ በጃባሊያ አካባቢ ይንቀሳቀስ ነበር ብለዋል።
"በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ" የጋዛ ከተማ ሰላማዊ ሕዝቦች ለደህንነታቸው ሲሉ እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት በጋዛ በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በዜይቶን ከተማ እና ሳብራ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ "በጣም አደገኛ እና ለመቋቋም የሚከብድ " መሆኑን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ረቡዕ ዕለት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት እና ድብደባ 25 ሰዎች ተገድለዋል።
ከጋዛ ከተማ በስተምዕራብ በሻቲ የስደተኞች መጠለያ በባድር አካባቢ የሚገኝ ድንኳን በቦምብ ተመትቶ ሦስት ልጆች ከእነ ወላጆቻቸው ተገድለዋል።
ዴፍሪን እንዳሉት የመከላከያ ኃይሉ አሁንም በጋዛ በሐማስ ቁጥጥር ስር ባሉ 50 ታጋቾች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።
በሐማስ ቁጥጥር ስር ከሚገኙት ታጋቾች መካከል 20 ያህሉ ብቻ በሕይወት መኖራቸው ይታመናል።
ቤተሰቦቻቸው በጋዛ ከተማ የሚገኙት በምድር ጥቃቱ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በጋዛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከተጠናከረ በፍልስጤም ሰላማዊ ዜጎችም ሆነ በታጋቾች ላይ አስከፊ ሁኔታ እንደሚፈጠር አስጠንቅቋል።
"ለወራት ሳያቋርጥ ከቀጠለው ግጭት እና ተደጋጋሚ መፈናቀል በኋላ በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተዳክመዋል።የሚፈልጉት ተጨማሪ ጫና ሳይሆን እፎይታ ነው። የበለጠ ፍርሃት ሳይሆን ፋታ ማግኘት ነው። በክብር ለመኖር የሚያስፈልጉ ነገሮች ማለትም የምግብ፣ የሕክምና እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ንጹህ ውሃ እና አስተማማኝ መጠለያ ማግኘት አለባቸው" ሲል በመግለጫው ላይ ገልጿል።
አክሎም "ተጨማሪ የወታደራዊ ዘመቻዎች መጠናከር ስቃዩን ከማባባስ፣ ብዙ ቤተሰቦችን ከመበታተን እና ሊቀለበስ የማይችል ሰብዓዊ ቀውስን ከማምጣት በተጨማሪ የታጋቾችንም ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ሲልም ገልጿል።
አፋጣኝ የተኩስ አቁም አንዲደረግ እና በመላው ጋዛ ፈጣን እና ያልተገደበ የሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስም ጠይቋል።
አሸማጋዮች ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል ጥረት እያደረጉ ሲሆን ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እና በሐማስ እጅ ከሚገኙት 50 ታጋቾች መካከል ግማሹን ለማስለቀቅ አዲስ ምክረ ሀሳብ አቅርበው ሐማስ ሰኞ ዕለት እንደተቀበለው ተናግሯል።
እስራኤል እስካሁን ድረስ ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም ባለስልጣናቷ ግን ማክሰኞ ዕለት ከፊል ስምምነት እንደማይቀበሉ በመግለጽ ታጋቾቹ በሙሉ እንዲለቀቁ የሚያስችል አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ረቡዕ ዕለት ሐማስ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሸማጋዮቹን የተኩስ አቁም ሃሳብ ችላ ብለዋል በማለት ወንጅሎ "የማንኛውም ስምምነት እውነተኛ አደናቃፊ" ናቸው ሲል መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎች ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቷል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ወታደራዊ ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋዛ ቢያንስ 62,122 ሰዎች ተገድለዋል።















