ሐማስ በቀረበለት የጋዛ የተኩስ አቁም ላይ መስማማቱን ምንጮች ገለፁ

በመጠለያ ድንኳን መስኮት ወደ ውጪ የምትመለከት ፍልስጤማዊት ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሐማስ ከእስራኤል ጋር በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾችን ለመልቀቅ በአሸማጋዮቹ የቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ መስማማቱን ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።

ግብፅ እና ኳታር ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ የአሜሪካ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በሰኔ ወር ባቀረቡት ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ ነው ተብሏል።

በመጀመርያው 60 የተኩስ አቁም ቀናት ሐማስ ከቀሩት 50 እስራኤላውያን ታጋቾች መካከል ግማሹን፣ 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል፣ በሁለት ቡድን በመክፈል የሚለቅ ይሆናል።

በዚሁ ወቅት ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ ድርድር ይኖራል ተብሏል።

የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ስምምነቱን ሊቀበል የሚችለው "ታጋቾቹ በሙሉ በአንድ ጊዜ የሚለቀቁ ከሆነ ብቻ ነው" ማለቱን ተከትሎ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልፅ አይደለም።

የሐማስ ይሁንታ ከተሰማ በኋላ በተለቀቀ ቪዲዮ ላይ ኔታንያሁ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ አስተያየት ሳይሰጡ "ከእነርሱ አንድ ነገር ሊገባችሁ ይችላል፤ ሐማስ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው" ብለዋል።

የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ኢያል ዛሚር በበኩላቸው "በጋዛ ከተማ በሐማስ ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረግ" ለ22 ወራት ለዘለቀው ጦርነት ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።

የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት በጋዛ ከተማ የእስራኤል ታንኮች በአየር እና በመድፍ ጥቃቶች እየታገዙ ወደ ደቡብ ሳብራ በመገስገስ ትምህርት ቤቶችን እና ብዙ ተፈናቃዮችን ያስጠለለ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፍ ክሊኒክ ከብበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ሳምንት መገባደጃ ላይ የእስራኤል ካቢኔ የጦር ኃይሉ የጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር ያቀረበውን እቅድ ያፀድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ተጠናክሮ የቀጠለው የእስራኤል ጥቃት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል።

ኔታንያሁ እስራኤል ከሐማስ ጋር በተዘዋዋሪ የምታደርገው ውይይት ያለ ስምምነት መቋረጡን ተከትሎ 2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን የተጠለሉባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ መላውን ጋዛ ለመቆጣጠር እና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስፋት ያላቸውን ፍላጎት አሳውቀዋል።

በሐማስ ዋነኛ ተደራዳሪ ካሊል አል ሀያ የሚመራ ልዑክ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አዲስ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ከሚሞክሩት አደራዳሪዎች ጋር በካይሮ ተገናኝቶ ነበር።

ሰኞ ማለዳ ላይ አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የልዑካን ቡድኑ እሁድ ዕለት የቀረበለትን አዲስ የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ እየገመገመ ነው።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱል ራህማን አል ታኒ "ሁለቱም ወገኖች በተቻለ ፍጥነት ከሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጫና ለማድረግ" ካይሮ መግባታቸውን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ተናግረዋል።

አብደላቲ ፍልስጤምን ከግብጽ በሚያዋስነው ራፋህ ድንበር በተገኙበት ወቅት አገሪቱ ያለችበትን ጥልቅ ሰብዓዊ ቀውስ ለመቅረፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት አሳስበዋል።

በጋዛ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ "ከአእምሮ በላይ" ነው ብለዋል።

ሰኞ ማምሻውን የሐማስ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለፁት ቡድኑ በቀረበው የተኩስ አቁም ሃሳብ ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያ እና ቅድመ ሁኔታ ሳያቀርብ መስማማቱን በመግለጽ ለአሸማጋዮቹ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል።

ውይይቱን በቅርበት የሚከታተሉ የፍልስጤም ባለስልጣን እንደገለፁት የአሁኑ የተኩስ አቁም ሃሳብ ከሁለት ወራት በፊት ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡት እና ሐማስ ውድቅ ካደረገው ጋር "ተመሳሳይ" ነው።

ዊትኮፍ የ60 ቀን ተኩስ አቁም እንዲደረግ ሐማስ 10 በሕይወት ያሉ እና የ18 የታጋቾችን አስከሬን እንዲለቅ በምላሹ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲፈቱ የሚጠይቅ ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

በዚሁ ምክረ ሃሳብ መሠረት በተኩስ አቁሙ ወቅት ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል ድርድር ይደረጋል።

እሁድ ምሽት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ቴልአቪቭ አደባባይ በመውጣት መንግሥታቸው ጦርነቱን አሁኑኑ እንዲያቆም እና ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ ከሐማስ ጋር ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የታጋቾች ቤተሰቦች በጋዛ ከተማ ሌላ ጥቃት መፈጸም በቁጥጥር ስር የሚገኙት እስራኤላውያንን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

የ48 ዓመቱ ልጃቸው ኦምሪ ለ682 ቀናት በእገታ ውስጥ ያለው ዳኒ ሚራን "ልጄ ላይ ጉዳት ይደርሳል ብዬ እፈራለሁ" ብለዋል።

ኔታንያሁ ሠልፈኞቹን የሐማስን የመደራደር አቋም አጠናክረውታል ሲሉ ከስሰዋል።

ፍልስጤማውያን ሰኞ ዕለት በጋዛ ከተማ ባደረጉት የተቃውሞ ሠልፍ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

"ሐማስ እና ጥያቄዎቹ እንዲሁም ድርድር ላይ ያሉት ጥያቄዎች እኔን አይወክሉኝም። በሰላም መኖር እፈልጋለሁ። የአእምሮ ሰላም እፈልጋለሁ።ጥያቄያችን ለልጆቻችን ሰላም እና ደህንነት ብቻ ነው" ስትል አንዲት ሴት ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ተናግራለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "የቀሩት ታጋቾች ሲመለሱ የምናየው ሐማስ ጫና ሲደረግበት እና ሲጠፋ ብቻ ነው!!! ይህ በፍጥነት በሚከናወንበት ጊዜ ስኬታማ የምንሆንበት ዕድል ይሰፋል" ሲሉ ጽፈዋል።

በቴልአቪቭ እሁድ ዕለት ሠላማዊ ሰልፍ ያካሄዱ እስራኤላውያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እሁዱ በቴላቪቭ በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ታጋቾቹን በሙሉ ለማስለቀቅ የሚያስችል አፋጣኝ ስምምነት እንዲደረግ ተጠይቋል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱ የሚያቆመው ሁሉም ታጋቾች ሲለቀቁ እና ሐማስ ትጥቅ ሲፈታ ብቻ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ጋዛ ከወታደራዊ ቁጥጥር ውጪ ሆና በእስራኤል የደህንነት ቁጥጥር ስር እንድትገባ እና ከሐማስ ወይም ከፍልስጤም አስተዳደር ጋር ግንኙነት በሌለው አስተዳደር እንድትመራ ይፈልጋሉ።

ሐማስ ያገታቸውን ለመልቀቅ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ እና ጦርነቱን እንዲቆም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ የሚያስችል አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረግ ጠይቋል።

ነጻ የፍልስጤም መንግሥት እስካልተመሰረተ ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታም አስታውቋል።

ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎች ካገተ በኋላ እስራኤል በጋዛ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 62,000 ሰዎች ተገድለዋል።

አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ በተደጋጋሚ የተፈናቀለ ሲሆን ከ 90 በመቶ በላይ ቤቶች ወድመዋል አልያም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሎ ይገመታል።

በጋዛ የጤና፣የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ተቀወማት ወድመዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የዓለም የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በጋዛ ባለው የምግብ እጥረት ሳቢያ "በአሁኑ ወቅት በጣም የከፋ የረሃብ ሁኔታ እየታየ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ እንደዘገበው ባለፉት 24 ሰዓታት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ሌሎች አምስት ሰዎች መሞታቸውንና ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 263 ደርሷል።