አሜሪካ ከጋዛ ለሕክምና የሚመጡ ሰዎች ያገኙ የነበረውን የጉብኝት ቪዛ መስጠት አቆመች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጋዛ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉንም ዓይነት የጉብኝት ቪዛዎች መስጠት ማቆሙን አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን እገዳ ተግባራዊ ያደረገው "ባለፉት ቀናት ጥቂት ጊዜያዊ የሕክምና ሰብአዊ ቪዛዎችን ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋሉ ሂደቶች እና አሰራሮች ላይ ሙሉ እና ጥልቀት ያለው ግምገማ ለማካሄድ" እንደሆነ በኤክስ ገጹ ገልጿል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ከፍልስጤም የመብት ተሟጋች ቡድኖች ተቃውሞ ገጥሞታል።
'ፓለስታይን ችልድረንስ ሪሊፍ ፈንድ' የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ባወጣው መግለጫ ውሳኔው "የተጎዱ እና በጠና የታመሙ ሕፃናትን ከጋዛ ወደ አሜሪካ ለመውሰድ በሚኖረን አቅም ላይ አስከፊ እና የማይመለስ ተጽእኖ ይኖረዋል" ብሏል።
ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖሊሲ ለውጥ ይፋ የተደረገው ላውራ ሉመር የተባለች ቀኝ አክራሪ አክቲቪስት የቪዛ ፕሮግራሙን በመተቸት እንዲሁም "አጸያፊ" ስትል የጠራችውን ፕሮግራሙን የትራምፕ አስተዳደር እንዲዘጋ በመጠየቅ በኤክስ ገጿ ተከታታይ ልጥፎችን ካጋራች በኋላ ነው።
አክቲቪስቷ ቀጥሎ በለጠፈችው ጽሑፍ ይህ እርምጃ ለመወሰዱ ያደረገችውን አስተዋጾ የገለጸች ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጊዜያዊነት ቪዛ የመስጠት ሂደትን ስላቋረጡ አመሰግናለች።
'ፓለስታይን ችልድረንስ ሪሊፍ ፈንድ' በ2024 ተግባራዊ ባደረገው የውጭ አገር ሕክምና መርሃ ግብሩ አማካኝነት 169 ሕፃናትን ከጋዛ በማውጣት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣አውሮፓ፣ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጿል።
ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ስካሄድ የቆየው ጦርነት በጋዛ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የሕክምና መሠረተ ልማቶች እንዲወድሙ ያደረገ ሲሆን ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዲፈጠርም ምክንያት ሆኗል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እስራኤል በመጋቢት ወር ተግባራዊ ያደረገችው እገዳ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቂ ምግብ ወደ ጋዛ እንዳያደርሱ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።
የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ የእርዳታ እንቅስቃሴ ላይ የጣላቸው ደንቦቹ ወደ ጋዛ የሚገባው ምግብ በሐማስ እንዳይወሰድ መከላከልን ዒላማ ያደረጉ ናቸው ብሏል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የምግብ ዋስትና ድርጅቶች፣ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች እና ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች በጋዛ ረሃብ እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል።
በሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ ቢቢሲ፣ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ፣ ከአሶሺዬትድ ፕሬስ እና ከሮይተርስ ጋር በመተባበር ባወጡት መግለጫ በጋዛ ያሉ ጋዜጠኞች ረሃብ እንደተጋረጠባቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
የዜና ምንጮቹ በመግለጫቸው፤ "እነዚህ ገለልተኛ ጋዜጠኞች ለበርካታ ወራት ጋዛ ውስጥ የዓለም ዓይን እና ጆሮዎች ሆነው ቆይተዋል። አሁን ከሚዘግቧቸው ጉዳዮች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አስከፊ ሁኔታዎችን እየገጠሟቸው ነው" ብለዋል።
በሐምሌ ወር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛ ውስጥ "እውነተኛ ረሃብ" እንዳለ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ አስተዳደራቸው አሁንም ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጎን በመሆን ጠንካራ አቋም ይዟል።















