አውስትራሊያ መስከረም ላይ ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያ፤ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ እና ካናዳን እርምጃ በመከተል፤ በመስከረም ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና የመስጠት እቅድ እንዳላት አስታወቀች።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፤ ውሳኔው በመስከረም በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል። አገሪቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችውም የፍልስጤም ባለስልጣን ቃል የተገባላቸውን ቁርጠኝነት ተከትሎ እንደሆነም ተናግረዋል።
"በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የአመጽ ድግግሞሽ ለመስበር እንዲሁም በጋዛ ያለውን ግጭት፣ ስቃይ እና ረሃብ ለማስቆም የሁለት ግዛት መፍትሄ የሰው ልጅ ምርጥ ተስፋ ነው" ብለዋል።
በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት እንድስቆም ጫና እየበረታባት ያለችው እስራኤል፤ ለፍልስጤም አገረ መንግሥት እውቅና መስጠት "ሽብርተኝነትን የሚሸልም ነው" በማለት ትቃወማለች።
ከቅዳሜ ጀምሮ በጋዛ አምስት ሰዎች በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጦት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም 217 እንደደረሰ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከ2023 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የተገደሉ በጠቅላላው ሰዎች ብዛትም ከ61,000 በላይ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
እስራኤል ይህንን ዘመቻዋን የከፈተችው በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ መሪነት በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ለተፈጸመው እና 1200 ሰዎች ተገድለው 251 ታጋቾች ለተወሰዱበት ጥቃት ምላሽ በመስጠት ነው።
በእስራኤል የተወረረውን ዌስት ባንክ በከፊል የሚቆጣጠረው የፍልስጤም ባለስልጣን፤ የአገርነት እውቅና መስጠቱ ለሕዝቡ የራስን እድልን በራስ የመወሰን መብት የሚሰጠው ድጋፍ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ሲል ከዚህ ቀደም ተናግሮ ነበር።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት፤ ውሳኔውን የወሰደው የፍልስጤም ባለስልጣን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ፤ ሐማስ በየትኛውም በወደፊቷ የፍልስጤም አገርነት ውስጥ ምንም ሚና እንደማይኖረው ቃል ከገባላቸው በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰውም ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ኒውዚላንድ እና ጃፓን ካሉ አቻዎቻቸው ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ እንደሆነም አክለዋል።















