እስራኤል በጋዛ ከተማ ያቀደችውን ጥቃት ከመጀመሯ አስቀድማ 60,000 ተጠባባቂ ኃይሏን ጠራች

አቧራ የለበሰ የእስራኤል ጦር ታንክ እና ወታደር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን በጋዛ ከተማ ጥቃት ላይ አምስት ዕዝ ጦር እንደሚሳተፍ ተናግረዋል

የእስራኤል ጦር መላውን የጋዛ ከተማ ለመቆጣጠር እና ለመውረር የምድር ጥቃት ከመጀመሩ በፊት ወደ 60,000 የሚጠጉ ተጠባባቂ ኃይሎችን እየጠራ መሆኑን ገለፀ።

አንድ ወታደራዊ ባለስልጣን እንደተናገሩት ተጠባባቂ ኃይሎቹ በመስከረም ወር ሪፖርት የሚያደርጉ ሲሆን አብዛኛዎቹ በምድር ለሚደረገው ውጊያ ዝግጁ የሚሆኑ ናቸው ተብሏል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ ማክሰኞ ዕለት ያፀደቁት እና በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ወደ የፀጥታ ካቢኔ የሚቀርበው ዕቅድ ዝግጅት አካል የሆኑት ወታደሮች ቀደም ሲል በዘይቶን እና ጃባሊያ አካባቢዎች የተሰማሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በጋዛ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ እና ወደ ደቡባዊ ጋዛ መጠለያ እንዲያመሩ ይታዘዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ የእስራኤል አጋሮች እቅዱን ያወገዙ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ22 ወራት ጦርነት በኋላ ሌላ ጥቃት እና ተጨማሪ የጅምላ መፈናቀል "አሰቃቂ የሆነ ሰብዓዊ ተጽዕኖ" እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤል መንግሥት ባለፈው ወር በተዘዋዋሪ ከሐማስ ጋር የሚያደርገው የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ሳይሳካ ከቀረ በኋላ መላውን የጋዛ ሰርጥ የመውረር ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

አሸማጋዮች ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል ትረት እያደረጉ ሲሆን ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እና በሐማስ እጅ ከሚገኙት 50 ታጋቾች መካከል ግማሹን ለማስለቀቅ አዲስ ምክረ ሀሳብ አቅርበው ሐማስ ሰኞ ዕለት እንደተቀበለው ተናግሯል።

እስራኤል እስካሁን ድረስ ይፋዊ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን የእስራኤል ባለስልጣናት ግን ማክሰኞ ዕለት ከፊል ስምምነት እንደማይቀበሉ በመግለጽ ታጋቾቹ በሙሉ እንዲለቀቁ የሚያስችል አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከታጋቾቹ መካከል 20ዎቹ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ ተብሎ ይታመናል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በመግለጫው እንዳስታወቀው በግንቦት ወር የጀመረው ጥቃት ቀጣይ የሆነው የጌዲዮን ሠረገላዎች ዘመቻ ዝግጅት አካል እንዲሆኑ 60,000 ተጠባባቂ ኃይሎች እንዲጠሩ ትእዛዝ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ጥሪ የተደረገላቸው 20,000 ተጠባባቂ ኃይሎች አሁን ያሉበትን ግዳጅ የሚያራዝም ትዕዛዝ እንደሚደርሳቸውም ገልጿል።

አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን ከፍተኛ አዛዦች በጋዛ ከተማ እና አካባቢዋ "ቀስ በቀስ" እና "ዒላማው ላይ ያነጣጠረ" ዘመቻ እንዲደረግ ማፅደቃቸውን ተናግረዋል። የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ኢያል ዛሚር በሚቀጥሉት ቀናት ዕቅዱን ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ከሆነ በጥቃቱ አምስት ዕዞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሃሬትስ ጋዜጣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ካትስ ማክሰኞ ዕለት "ዘመቻው አንዴ እንደተጠናቀቀ ጋዛ መልኳን ትለውጣለች፤ የቀድሞዋን አትመስልም" ማለታቸውን ዘግቧል።

በተጨማሪም ጦሩ ተጨማሪ የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎችን እና የመስክ ሆስፒታሎችን ማቋቋም በጀመረበት የባህር ዳርቻዋ አል ማዋሲ እና በደቡብ ክልል በሚገኘው የጋዛ ከተማ ነዋሪዎች "እንዲስተናገዱ" ዕቅድ ጸድቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት የእስራኤል ጦር ዓላማ በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ሁሉንም ታጋቾች ማስለቀቅ እና የሐማስን "ሽንፈት ማረጋገጥ" ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው የጊቫቲ ብርጌድ በሰሜናዊቷ ጃባሊያ እና በጋዛ ከተማ ዳርቻ ላይ "ከምድር በላይ እና በታች የሚገኙ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን በማፍረስ፣ አሸባሪዎችን በመደምሰስ እና በቁጥጥር ስር የማድረግ ዘመቻውን በማጠናከር ላይ ነው" ብሏል።

ሰላማዊ ዜጎች ለደህንነታቸው እና ያለባቸውን "የጉዳት ስጋትን ለመቀነስ" ወደ ደቡብ እንዲሄዱ እንደተነገራቸው ገልጿል።

በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ማክሰኞ ዕለት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል "ሁኔታው በጣም አደገኛ እና ሊቋቋሙት የማይችሉት ነው" ካሉ በኋላ በዜይቶን ከተማ እና ሳብራ አካባቢዎች "ድብደባው ያለማቋረጥ ቀጥሏል" ብለዋል።

ኤጀንሲው ረቡዕ ዕለት በጋዛ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት 21 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ እንደዘገበው ከጋዛ ከተማ በስተ ምዕራብ በሚገኘው በሻቲ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ አንድ ቤት በቦምብ ተመትቶ ሦስት ልጆች እና ወላጆቻቸው ተገድለዋል።

ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር የአየር ድብደባ ጉዳት የደረሰበትን ስፍራ ሲመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዲስ ጥቃት የሚያስከትለውን ሰብዓዊ ተጽዕኖ በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

"እስራኤል በጋዛ ከተማ ወታደራዊ ዘመቻዋን ለማጠናከር ማቀዷ ቀድሞ በተዳከሙ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በሐዘን በተጎዱ፣ በተፈናቀሉ እና ለኅልውናቸው የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን በተነፈጉ ሰዎች ላይ ዘግናኝ የሆነ ሰብዓዊ ተጽእኖ ይኖረዋል" ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

"በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ማስገደድ ለቀጣይ አደጋ የማዘጋጃ መመሪያ እና አስገድዶ ማፍለስንም ሊጨምር የሚችል ነው" ሲሉ ስጋታቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ይሄዳሉ ተብሎ የሚጠበቁባቸው የደቡብ አካባቢዎች "የተጨናነቁ እና የሰውን ኅልውና ለማስቀጠል የሚያስችል አቅርቦት የሌላቸው" ናቸው ብለዋል።

"የደቡብ ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ እየሰሩ ናቸው። ከሰሜን የሚመጡ ታካሚዎችን መቀበል ለሕይወት አስጊ የሆነ ውጤት ያስከትላል።"

ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎች ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቷል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ወታደራዊ ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋዛ ቢያንስ 62,122 ሰዎች ተገድለዋል።

አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ ብዙ ጊዜ ተፈናቅሏል።

በጋዛ ከ 90 በመቶ በላይ ቤቶች ፈራርሰዋል ወይም ወድመዋል ተብሎ ይገመታል።

በግዛቲቱ የሚገኙ የሕክምና መስጫ ተቋማት፣ የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና መጠበቂያ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የዓለም የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በምግብ እጥረት ሳቢያ "በአሁኑ ወቅት በጣም የከፋ ረሃብ እየታየ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።