ኔታንያሁ ለፍልስጤም ዕውቅና እሰጣለሁ ያሉትን የአውስትራሊያ መሪ እስራኤልን "ከድተዋል" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርቡ ለፍልስጤም በአገርነት ዕውቅና እሰጣለሁ ያሉትን የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤልን "ከድተዋል" ሲሉ ወቀሱ ።
ኔታንያሁ በተጨማሪም በአገራቸው ያሉ የአውስትራሊያ የአይሁድ ማህበረሰብን "ትተዋል" ብለዋቸዋል።
"ጥንካሬ የሚለካው ስንት ሰው ልታፈነዳ ትችላለህ ወይም ሰዎችን በማስራብ አይደለም" ሲሉ የአውስትራሊያ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ቶኒ ቡርክ በበኩላቸው እስራኤልን ወቅሰው ለአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ታሪክ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝን "በማንነቱ፣ በደካማ ፖለቲከኛነቱ" ያስታውሰዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ይህንን ያሉት በሁለቱ አገራት መካከል የተከሰተው ውጥረት መካረሩን ተከትሎ ነው።
የአውስትራሊያ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ቶኒ ቡርክ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ እና ካናዳ ጋር በመሆን ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንደሚሰጡ ማወጃቸውን ተከትሎ "ይህንን ውርጅብኝ የሚያዘንቡት" ብለዋቸዋል።
አውስትራሊያ የናታንያሁ ገዥ ፓርቲ ጥምረት አባል የሆነውን የቀኝ አክራሪው አባላት ሰኞ ዕለት ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ዕግድ ጥላለች።
እስራኤል በበኩሏ የፍልስጤም አስተዳደር የአውስትራሊያ ተወካዮችን ቪዛ ሰርዛለች።
የእስራኤል ተቃዋሚ መሪ በበኩላቸው የኔታንያሁም ንግግር በመንቀፍ ለአውስትራሊያው መሪ "ስጦታ ነው" ያበረከቱላቸው ብለዋል።
"በአሁኑ ወቅት በዲሞክራሲያዊው ዓለም መሪን ጠንካራ የሚያደርገው በምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኛ መርዘኛ ከሆኑት ኔታንያሁ ጋር ያለው ፍጥጫ ነው" ሲሉ ያይር ላፒድ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
"ቢቢ [ቤንያሚን ኔታንያሁ" ይህንን ስጦታ ለአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ለመስጠት ለምን እንደተጣደፉ ግልጽ አይደለም" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በግዳጅ አፈናቅሎ በደቡባዊ ጋዛ በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን ፤ ጦሩ የጋዛ ከተማን የሚወርበት የጊዜ ሰሌዳ አላስቀመጠችም።
በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።
በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል። አንዳንዶች በተደጋጋሚ የተናፈናቀሉ ሲሆን በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሰፈራ በማፍረስ በአውሮፓውያኑ 2005 ጦሯን አስወጥታ ነበር።
ሆኖም ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን የጋዛን ፀጥታ እና መዳረሻ ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ይህ የእስራኤል እንደገና የመጠቅለል ዕቅድ የተሰማው ለአስርት ዓመታት የቀጠለውን የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት እልባት ለመስጠት የሁለት ግዛት መፍትሄ ሃሳቦች እንደገና እየቀረቡ ባሉበት ወቅት ነው።
የፍልስጤም አገር ምሥረታ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ጋዛን ያካተተ ዕቅድ ነው።
እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።
በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።
ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።
በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ይህንን አትቀበልም።
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል።
ሰፈራዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።















