እስራኤል በኳታር ከፈጸመችው ጥቃት በዶሃ ያሉ የሐማስ አመራሮች መትረፋቸው ተገለጸ

እስራኤል በኳታር የፈጸመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል በኳታር መዲና ዶሃ በፈጸመችው ጥቃት የሐማስ ተደራዳሪ ቡድን መትረፉን ቡድኑ አስታወቀ።

ሐማስ ባወጣው መግለጫ "ጠላት የተደራዳሪ ልዑካችን ላይ የፈፀመው የመግደል ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።

መግለጫው አክሎም ጥቃቱ "ኔታንያሁ እና መንግሥታቸው ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ እንደማይፈልጉ ያረጋገጠ ነው" ብሏል።

እስራኤል ማክሰኞ፣ ጳጉሜ 4/ 2017 በዶሃ በፈጸመችው ጥቃት ስድስት ግለሰቦች መገደላቸውንም መግለጫው አክሏል።

"የአሜሪካ አስተዳደር በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ወረራ እና ጥቃቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ በመደገፍ ለዚህ ለተፈጸመው ጥቃት በጋራ ተጠያቂ ነው" ብሏል ሐማስ።

ሐማስ በዶሃ ባለው የተደራዳሪው ልዑክ ቡድን ላይ ጥቃቱ እንዳነጣጠረ የገለጸ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ በሐማስ አመራሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጣለች።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል የሐማስ ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ካህሊል አል ሃያ ልጅ እንደሚገኝበት ተገልጿል።

በጥቃቱ የኳታር የጸጥታ ኃይል አባልን ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ዝርዝር የወጣ ሲሆን እነሱም የካህሊል አል ሃያ ልጅ ሁማም አል ሃያ፣ የአል ሃያ ቢሮ ዳይሬክተር ጂሃድ ላባድ፣ አቡዱላህ አቡዱል ዋሂድ፣ ሞአመን ሃሱና፣ አህመድ አል ማምሉክ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ስድስተኛው የተገደለው ግለሰብ የኳታር የደኅንነት አባል የሆነው ባድር ሰዓድ መሐመድ አል ሁማይዲ መሆኑም ተነግሯል።

እስራኤል በኳታር ላይ ጥቃቷን ከመፈጸሟ በፊት ለአሜሪካ ጦር ማሳወቋና ይህም እንደተነገራቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

የሚፈጸመውን ጥቃት ለኳታር ለማሳወቅ ቢሞክሩም ሁኔታው "ዘግይቷል" ብለዋል።

ኳታር ይህንን ጥቃት "ዓይን ያወጣ የአለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው" ስትል ወቅሳለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ለሃማስ መሪዎች ምንም አይነት "ከለላ" ሊኖር አይገባም ብለዋል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን አልታሪ አገራቸው "ለዚህ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ መብቷ የተጠበቀ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ይህንንም ለቀጣናው "ወሳኝ ጊዜ" ብለውታል።

"ለዚህ አይነት አረመኔዊ ድርጊቶች ከመላው ቀጣናው ምላሽ ሊኖር ይገባል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አጽንኦት ሰጥተዋል።

እስራኤል በዶሃ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመረች ከ10 ደቂቃ በኋላ የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው አልታኒ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው የጋዛን ጦርነት መቋጨት በተመለከተ የምታደርገውን የማሸማገል ሥራ ለመቀጠል ምንም የሚከለክላቸው እንደሌለ አስረድተል።

የኳታር አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ያደረጉትን የስልክ ጥሪ ተከትሎ በእስራኤል ጥቃት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሚሩ፤ ትራምፕ አሜሪካ ለኳታር ያላትን አጋርነት እንዳረጋገጡላቸው እንዲሁም "በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀው አውግዘዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

አሚሩ በምላሹ ኳታር ይህን የእስራኤል ጥቃት "ግዴለሽነት የተሞላበት ወንጀል" አድርጋ እንደምትቆጥረው እና አገራቸው "ደኅንነቷን እንዲሁም ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ትወስዳለች" ሲሉ ለትራምፕ መንገራቸውን በዚሁ መግለጫቸው ላይ አስረድተዋል።