እስራኤል በኳታር መዲና ዶሃ በሐማስ ከፍተኛ መሪዎች ላይ ጥቃት ፈጸመች

ኳታር ዶሃ ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኳታር ዶሃ ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

እስራኤል ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ዒላማ አድርጋ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጠች፤ ኳታር ጥቃቱን በጽኑ አወገዘች።

ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ዶሃ ውስጥ ፍንዳታዎች መሰማታቸው እና ከፍተኛ ጭስ መታየቱን የፈረንሳዩ ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ኳታር ውስጥ በሚገኙ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የተነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት በሐማስ መሪዎች ላይ ዶሃ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት "ሙሉ ለሙሉ በእስራኤል የተፈጸመ ተልዕኮ ነው" በማለት አረጋግጧል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ጥቃቱ "በእስራኤል የተመራ፣ እስራኤል የፈጸመችው እና ሙሉ ኃላፊነቱንም የምትውስድበት ነው" ብሏል።

ከመከላከያ ኃይሉ የወጣው መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመው የት ቦታ ላይ እንደሆነ፣ የዒላማዎቹን ማንነት እና ስለደረሰው ጉዳት የተገለጸ ነገር የለም።

መግለጫው በተጨማሪም "ከጥቃቱ ቀድሞ ነጥሎ መምታት የሚያስችል መሳሪያ እና ዝርዝር መረጃን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ተደርጓል" ብሏል።

በተፈጸመው ጥቃት አንድ የእስራኤል ባለሥልጣንም ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ኳታር ውስጥ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የቡድኑ ተደራዳሪ ልዑክ ስብሰባ እያካሄደ ሳለ ዶሃ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ዒላማ መደረጉን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እስራኤል ኃላፊነቱን የወሰደችበትን ጥቃት የዓለም አቀፍ ሕጎች "ግልጽ ጥሰት" እና በኳታር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች "ከባድ ስጋት" ነው በጽኑ አውግዘውታል።

ቃል አቀባዩ ዶክተር ማጂድ አል አንሳሪ ጥቃቱ የተፈጸመው "በርካታ የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ አባላት በሚኖሩበት" በኳታር ዋና ከተማዋ ዶሃ በሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ኳታር የእስራኤልን ጥቃት "በጽኑ እንደምታወግዘው እና እንዲህ ያለውን በቀጣናው ደኅንነት እና በአገራት ሉዓላዊነት ላይ የተነጣጠረውን የእስራኤል ባሕሪ እንደማትታገሰው" አመልክቷል።

ከወራት በፊት በእስራኤል ከባድ ጥቃት የተፈጸመባት እና ሐማስን የምትደግፈው ኢራን ኳታር ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዛዋለች።

የእስራኤል ጦር ኃይል ጥቃቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ "የሽብር ድርጅት" ያለው የሐማስ ከፍተኛ አመራሮችን ዒላማ በማድረግ የተመረጠ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል።

ጨምሮም ዒላማ የተደረጉት የሐማስ ባለሥልጣናት በ2016 ዓ.ም. ቡድኑ በእስራኤል ላይ ለፈጸመው ጥቃት በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸውን እና ሐማስ በእስራኤል ላይ የሚያካሄደውን ጦርነት ሲመሩ ቆይተዋል ብሏል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይሉ እና የደኅንነት ተቋማት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ናቸው የተባለውን ሐማስ ለመደምሰስ የሚያካሂዷቸውን ዘመቻዎች እንደሚቀጥሉ አመልክቷል።