ሐማስ የሁሉንም ታጋቾች አስከሬን ካላስረከበ ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳታ እንደሚገደብ እስራኤል አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐማስ የሁሉንም ታጋቾች አስከሬን ካላስረከበ ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳታ እንደሚገደብ እስራኤል አስጠነቀቀች።
ሐማስ እስከአሁን ድረስ የአራት ታጋቾችን አስከሬን ማስረከቡን የእስራኤል መከላከያ ገልጿል። የአራቱን ሰዎች ማንነት ለመለየትም የአስከሬን ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።
ሐማስ የ28ቱን ታጋቾች አስከሬን ካላስረከበ ወደ ጋዛ የሚገባውን ሰብአዊ እርዳታ እንደምትገድብ እስራኤል አስጠንቅቃለች።
እስራኤል የ45 ፍልስጤማውያንን አስከሬን አስረክባለች።
ሐማስ ለቀይ መስቀል ካስረከባቸው አስከሬኖች አንደኛው የኔፓል ዜጋ ነው። ሐማስ የተቀሩትን 20 አስከሬኖች እንዲለቅ ጫና በርትቶበታል።
አስከሬኖቹ ካልተለቀቁ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል ተብሏል።
የእስራኤል መከላከያ "ሐማስ ስምምነቱን ማክበር አለበት። የታጋቾችን አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ይመልስ" ብሏል።
"ይህ ሳይሆን ከቀረ ወይም ሒደቱ ከዘገየ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል" ሲልም አስጠንቅቋል።
ሐማስ ስምምነቱን አላከበረም በሚል እስራኤል ሰብአዊ እርዳታ ለመገደብ እና የራፋሕን ድንበር ላለመክፈት ወስናለች።
ሐማስ የተቀሩትን ታጋቾች አስከሬን ለማግኘት እንደተቸገረ ገልጿል። በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው የሁሉም ታጋቾችን አስከሬን ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል።
ዓለም አቀፍ ቡድን በጋዛ ተሰማርቶ አስከሬናቸው እንዲፈለግም እስራኤል ትሻለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድት ትራምፕ በበኩላቸው "ትልቅ ሸክም ቀሎልናል። ሥራችን ግን አላለቀም። አስከሬኖች ገና አልተለቀቁት። ሁለተኛው የሰላም ዕቅዱ ክፍል አሁን ይጀምራል" ብለዋል።
በካሀን ዩኑስ የሚገኘው ዕውቅ ፍልስጤማው ጸሐፊ ታይሰር አባድ፤ አሁን ያለው ፍጥጫ "የተኩስ አቁሙን የሚፈትን ነው" ብሏል።
"የአስከሬኖቹ አለመመለስ ሌላ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል" ሲልም ስጋቱን ገልጿል።
ሐማስ 20 በሕይወት ያሉ ታጋቾችን ሲለቅ፤ እስራኤል በምላሹ 2,000 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።
ከቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ቀጣዩ የሰላም ዕቅዱ ክፍል ይተገበራል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"ሐማስ ትጥቅ ፈትቶ ወታደራዊ እንቅስቃሴውን የማይገታ ከሆነ ግን ገሀነም ይጠብቃቸዋል" ሲሉም ዝተዋል።
በጋዛ "ማንኛውም የጦር መሣሪያ ማምረቻ" እንዲኖር እንደማይፈቅዱ እና ወደ ጋዛ "ማንኛውም መሣሪያ እንደማይገባም" ተናግረዋል።
ትራምፕ "ሐማስ ትጥቅ እፈታለሁ ብሏል። ትጥቅ ካልፈቱ ግን እኛው እናስፈታቸዋለን" ብለዋል።
ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ በእስራኤል ኃይሎች በምሥራቅ ጋዛ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።
በምሥራቃቂ ጋዛ ሸጃሊያ አካባቢ በእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውም ተዘግቧል።
በአካባቢው ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዳሉት እስራኤል ጥቃት የፈጸመችው ነዋሪዎች ቤታቸው ለመመለስ ፍተሻ ሲያደርጉ ነው።
እስራኤል ግን 'ቢጫውን ማስጠንቀቂያ መስመር ስላለፉ' ጥቃቱን መፈጸሟን በመግለጽ ክሱን አስተባብላለች።
ሐማስ "ሰላም ለማስፈን እና ሕገ ወጥ ድርጊትን ለማቀብ" እንደሚሠራ ገልጿል።
ከትናንት በስትያ በግብፅ፣ ሻርም ኤል-ሻይክ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአገራት መሪዎች ተሰባስበው በቀጣዩ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል።
ግብፅ፣ ኳታር፣ ቱርክ እና አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጠባቂዎች ሆነው ፊርማቸውን ማኖራቸውም ይታወሳል።
20 ነጥቦች ያሉት የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ድርድሩ መቀጠል አለበት።
ጋዛ በጊዜያዊነት በፍልስጤማውያን የሽግግር ኮሚቴ አባላት የምትመራ ይሆናል። ከዚያም በፍልስጤም አስተዳደር ሥር ትሆናለች።
ይህንን የሰላም ዕቅዱ ክፍል ለመተግበር ተከታታይ ድርድሮች መደረግ አለባቸው።
ስምምነት ላይ ካልተደረሰባቸው ነጥቦች አንዱ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣት፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታት እና የጋዛ ሰርጥ አስተዳደር ይጠቀሳሉ።
የፍልስጤም አገርነት እስካልተረጋገጠ ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታ ሐማስ አስታውቋል። ጋዛን የውጭ ኃይል እንዲያስተዳድራት እንደማይፈቅድም አስረግጧል።















