"አሁን መልሶ ግንባታ እንጀምራለን"- ዶናልድ ትራምፕ

ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, 1,700 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል ምክር ቤት ንግግር ካደረጉ በኋላ ወደ ግብፅ አቅንተዋል።

በግብፅ፣ ሻርም ኤል-ሻይክ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአገራት መሪዎች ተሰባስበው በቀጣዩ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል።

ግብፅ፣ ኳታር፣ ቱርክ እና አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጠባቂዎች ሆነው ፊርማቸውን አኑረዋል።

"አዲስ ውብ ቀን መጥቶልናል። አሁን ጊዜው መልሶ የመገንባት ነው" ብለዋል ትራምፕ።

"ለመካከለኛው ምሥራቅ ታሪካዊ ቀን ነው" ሲሉም አክለዋል።

እስራኤላውያን ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞች ቢለቀቁም የተኩስ አቁም ስምምነቱ በቀጣይ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ።

20 ነጥቦች ያሉት የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ድርድሩ መቀጠል አለበት።

የመጀመሪያው የሰላም ዕቅዱ ክፍል የሆነው እስረኞች እና ታጋቾችን መለዋወጥ ተጠናቋል።

የተኩስ አቁሙን ተከትሎ ወደ ጋዛ የሚገባው ሰብዓዊ እርዳታ መጠን ጨምሯል።

ታግቶ የነበረው እስራኤላዊ አርብል ዩውድ "ደስ ብሎኛል። ለሁለት ዓመት ያቆየኝ አንድ ቀን ቤተሰቤን አያለሁ የሚለው ተስፋነው" ብሏል።

ሐማስ ከሞቱት ታጋቾች መካከል የአራቱን አስክሬን ብቻ እንደሚመልስ አስታውቋል። በጋዛ የ24 ታጋቾች አስክሬን ይቀራል ተብሎ ይታመናል።

1,700 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል።

ከእስር ነፃ የወጣችው ፍልስጤማዊት ከልጇ ጋር ከተገናኘት በኋላ "በስተመጨረሻ ሰላም አግኝቻለሁ። የሚሰማኝን ደስታ መግለጽ አልችልም። የደረሰብን ስቃይ እንዳለ ሆኖ ዛሬ የደስታ ቀን ነው" ብላለች።

የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ ወደ 250 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችም ተለቀዋል። ከእነዚህ መካከል 100 ያህሉ በእስራኤል ይዞታ ሥር ወዳለው ዌስት ባንክ አቅንተዋል።

ፍልስጤማውያኑ ከተለቀቁ በኋላ በቀይ መስቀል መኪና ውስጥ ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር።

ሆኖም ግን አብዛኞቹ ሰውነታቸው ጠውልጎ ለመራመድ ሲቸገሩ ታይተዋል።

በካሃን ዩኑስ ልጁን ሲጠብቅ የነበረው ካሕሊል መሐመድ አብዱራሕማን አል-ቃታሩስ "ደስታም፣ ሐዘንም አለ" ሲል ስሜቱን ገልጿል።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግብፅ፣ ካታር፣ ቱርክ እና አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጠባቂዎች ሆነው ፊርማቸውን አኑረዋል

ትራምፕ በእስራኤል ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ "ለእስራኤላውያንም ለፍልስጤማውያንም ረዥም እና በሰቆቃ የተሞላው ጊዜ አልፏል" ብለዋል።

ትራምፕ ንግግር ሲያሰሙ የሕዝብ ተወካዮች ቆመው ስማቸውን ደጋግመው እየጠሩ አጨብጭበውላቸዋል።

ትራምፕ ሲናገሩ አንድ እስራኤላዊ ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል "ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ይሰጥ" የሚል ጽሑፍ በማሳየታቸው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጧል።

አፈ ጉባዔ አሚር ኦሀና በምክር ቤቱ "ሥነ ሥርዓት ይከበር" ብለው ሲያስጠነቅቁ፤ ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርጓል።

በግብፁ ውይይት ላይ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ማሐሙድ አባስ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ በርካታ መሪዎች ተገኝተዋል።

እስራኤላውያን ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤላውያን ቤተሰቦች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል

አብዛኞቹ የአረብ አገራት መሪዎች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።

ትራምፕ "ሰላም በመካከለኛው ምሥራቅ" የሚል ጽሑፍ አጠገብ ከአገራት መሪዎች ጋር ፎቶ ተነስተዋል።

የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌርም በውይይቱ ታድመዋል። ብሌር የትራምፕ የሰላም ዕቅድን የሚያስፈጽመው ቦርድ ኃላፊ ይሆናሉ።

ጋዛ በጊዜያዊነት በፍልስጤማውያን የሽግግር ኮሚቴ አባላት የምትመራ ይሆናል። ከዚያም በፍልስጤም አስተዳደር ሥር ትሆናለች።

ይህንን የሰላም ዕቅዱ ክፍል ለመተግበር ተከታታይ ድርድሮች መደረግ አለባቸው።

ስምምነት ላይ ካልተደረሰባቸው ነጥቦች አንዱ የእስራኤል ወታደሮች ይዞታ፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታት እና የጋዛ ሰርጥ አስተዳደር ይጠቀሳሉ።

የፍልስጤም አገርነት እስካልተረጋገጠ ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታ ሐማስ አስታውቋል። ጋዛን የውጭ ኃይል እንዲያስተዳድራት እንደማይፈቅድም አስረግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋዛ በፍልስጤም አስተዳደር ሥር እንድትሆን አይፈልጉም።

ትራምፕ የሰላም ዕቅዱ ሁለተኛ ክፍል ተጀምሯል ብለዋል።

ትራምፕ በግብፁ ውይይት ላይ "ሁሉም ሰው ደስተኛ ነው። እዚህ ለመድረስ 3,000 ዓመታት መውሰዱን ታምናላችሁ? ብለዋል።

የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደልፋታሕ አል-ሲሲ በአገራቸው ትልቁ የሆነውን 'ኦርደር ኦፍ ዘ ናይል' ሽልማት ለትራምፕ ሰጥተዋል።

አል-ሲሲ "አስከፊው ጊዜ ያከተመበት ታሪካዊ እርምጃ ነው" ሲሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ገልጸዋል።