"ለመካከለኛው ምሥራቅ ታሪካዊ ቀን ነው"- ዶናልድ ትራምፕ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "ለመካከለኛው ምሥራቅ ታሪካዊ ቀን ነው" ብለዋል።

ሐማስ በሕይወት ያሉ 20 ታጋቾችን መልቀቁን ተከትሎ ትራምፕ በምክር ቤቱ ንግግር ሲያሰሙ የሕዝብ ተወካዮች ቆመው አጨብጭበውላቸዋል።

እስራኤል 1,968 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።

ትራምፕ ንግግር ሲያደርጉ አንድ እስራኤላዊ ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል "ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ይሰጥ" የሚል ጽሑፍ በማሳየታቸው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጧል።

አፈ ጉባዔ አሚር ኦሀና በምክር ቤቱ "ሥነ ሥርዓት ይከበር" ሲሉ፤ ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርጓል።

ትራምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን "ልዩ ጀግንነት የተሞላው ሰው" ሲሉ አመስግነዋል።

በሐማስ እና እስራኤል መካከል ድርድሩን ላካሄዱት የአረብ አገራትም ትራምፕ ምስጋና አቅርበዋል።

"በጋራ በመሥራት ታላቅ ድል አስገኝተዋል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"አሁን የእስራኤል ወርቃማ ዘመን ነው" ያሉት ትራምፕ መላ ቀጣናውም "ወርቃማ ዘመን" ላይ ይገኛል ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ ጨምረውም "ከሁለት አሰቃቂ ዓመታት በኋላ 20 ጀግና ታጋቾች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል። የተቀሩት 28 ታጋቾች አስክሬናቸው መጥቶ በሰላም ያርፋሉ" ብለዋል።

ከትራምፕ በፊት በምክር ቤቱ ንግግር ያደረጉት ኔታንያሁ "በትራምፕ አስተዳደር ድጋፍ ከአረብ አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ጤናማ እናደርጋለን" ብለዋል።

ኔታንያሁ "በሞቱት ወታደሮች ጀግንነት አገራችን ትድናለች፤ ታድጋለች፤ ሰላም ታገኛለች" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕን የመሰለ "የእስራኤል ወዳጅ" በዋይት ሀውስ ታሪክ አልታየም ብለዋል ኔታንያሁ።

የፕሬዝዳንቱ የሰላም ዕቅድ ሰላም በማስፈን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቅሰዋል።

ኔታንያሁ በንግግራቸው ትራምፕ "የእስራኤል ታሪክ አካል" ናቸው ብለው "በመላ አገሬው ስም" ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ሐማስ እና እስራኤል የሰላም ዕቅድ ላይ መስማማታቸውን አሜሪካ ከሦስት ወራት በፊት በኢራን ኒውክሌር ማብላያ ላይ ካደረሰችው ጥቃት ጋር አስተሳስረዋል።

"ጥቃቱ ባይፈጸም ስምምነት ላይ አይደረስም ነበር። ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስራኤል ላይ ጨለማ ደመና ተገፏል" ብለዋል።

ጊዜው መካከለኛው ምሥራቅ "በሰላም የሚያብብበት ነው" ሲሉም ትራምፕ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለእስራኤል እና ለፍልስጤም ሕዝቦች "ረዥሙና የሚያመው የሰቆቃ ጊዜ አብቅቷል" ብለዋል።

ዛሬ ከሰዓት፤ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት መሐሙድ አባስ የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ውይይት በግብፅ ይካሄዳል።

ስብሰባው የጋዛን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰውን ስምምነት ከፍጻሜ ለማድረስ ያለመ ነው ተብሏል።

በግብፅ፣ ሻርም አል-ሼይክ ከትራምፕ ጋር በመሆን ጉባዔውን የሚመሩት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ናቸው።

በስብሰባው ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመርን ጨምሮ ከ20 አገራት በላይ መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።