የፍልስጤም ፕሬዚዳንት የጋዛን ጦርነት ለማስቆም በግብጽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ሊካፈሉ ነው

የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ማሃሙድ አባስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ማሃሙድ አባስ ዛሬ ሰኞ፣ በግብጽ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች የዓለም መሪዎች ጋር በመሆን ሊካፈሉ ነው።

ስብሰባው በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የተግባቡበትን ስምምነት ከፍጻሜ ለማድረስ ያለመ መሆኑን ጽሕፈት ቤታቸው ገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ በስብሰባው ላይ የተጋበዙት በሻራም ኤል ሼክ ከትራምፕ ጋር በመሆን ጉባዔውን የሚመሩት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ናቸው።

በስብሰባው ላይ የዩኬውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጨምሮ ከ20 አገራት በላይ መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡት ዕቅድ በአባስ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር፣ ሪፎርሞች ከተካሄዱ በኋላ ጋዛን በማስተዳደር ሚና ሊኖረው እንደሚችል ይገልጻል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ይህንን ሃሳብ አይቀበሉትም።

የፍልስጤም አስተዳደር የሐማስ ተቀናቃኝ በሆነው ፋታህ የሚመራ ሲሆን በእስራኤል ወረራ ስር የሚገኘውን ዌስት ባንክ ያስተዳድራል።

የ89 ዓመቱ አባስ ባለፈው ወር ለመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ ወደ ኒው ዮርክ እንዳይገቡ የእርሳቸው እና የ80 ልዑካን ቡድኖቻቸው ቪዛ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰረዙ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በወቅቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በእስራኤል እና ፍልስጤማውያን መካከል ተግባራዊ በሚሆን የሰላም ዕቅድ ላይ ከዓለም መሪዎች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

ሐማስ በወደፊቷ ጋዛ ላይ የሚኖረውን ሚና ውድቅ ያደረጉት አባስ ትጥቁን እንዲፈታ በንግግራቸው ላይ ጠይቀዋል።

የትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ የመጀመርያ ምዕራፍ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ረቡዕ ዕለት ስምምነት የተደረሰበት ሲሆን ከአርብ ዕለት ጀምሮ የተኩስ አቁም ተጀምሯል፥።

ዛሬ ሰኞ የፍልስጤማውያን እስረኞችን እና እስራኤላውያን ታጋቾች ልውውጥ ይደረጋል።

በሰላም ዕቅዱ ቀጣይ ዙሮች ላይ፣ ጋዛን ማን ያስተዳድራታል፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታት እና የእስራኤል ጦር መውጣትን የሚሉትን ጨምሮ ድርድሮች መካሄድ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል እና ሐማስ በግብፁ ስብሰባ ላይ ባለሥልጣኖቻቸው እንደማይሳተፉ አረጋግጠዋል።

በትራምፕ ዕቅድ መሠረት የጋዛ አስተዳደርን ይቆጣጠራል የተባለውን "የሰላም ቦርድ" ይመራሉ ተበሎ የሚጠበቁትን የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ቶኒ ብሌር እሁድ ዕለት የፍልስጤምን አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሁሴን አል ሼክ አግኝተው አነጋግረዋል።

የሲሲ ቢሮ የሰኞው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ዓላማ "በጋዛ ሰርጥ የሚካሄደውን ጦርነት ማስቆም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር " መሆኑን ተናግሯል።

የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በጋዛ ሰርጥ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ የሚቀርበውን ሰነድ" ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

በስብሰባው ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማርኮን፣ የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ 2ኛ፣ የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶዋን ይገኛሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ስብሰባው ላይ ከሚገኙት መካከል ናቸው።