እስራኤላውያን በቴል አቪቭ አደባባይ በመውጣት ፕሬዚዳንት ትራምፕን አመሰገኑ

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ አደባባይ በመውጣት ፕሬዚዳንት ትራምፕን ሲያመሰግኑ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ አደባባይ በመውጣት የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አመሠገኑ።

እስራኤላውያኑ አደባባይ የወጡት በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ታጋቾች ከመለቀቃቸው አስቀድሞ ነው።

አደባባይ ለወጡት እስራኤላውያን ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ታጋቾቹ "ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ" ብለዋል።

ዊትኮፍ አክለውም በጋዛ ተኩስ እንዲቆም እና ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርገው ስምምነት እንዲደረስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማድረጋቸው አመስግነዋቸዋል።

የፍልስጤም ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ የእስራኤል ጦር አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ 500,000 ነዋሪዎች ወደ ፈራረሰችው ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ አንዳለ ግብጽ ጦርነቱን ሊያስቆም ይችላል የተባለውን ስምምነት ከፍጻሜ ለማድረስ ሰኞ ዕለት ጉባዔ አንደምታካሂድ አስታውቃለች።

ትራምፕን ጨምሮ ከ20 በላይ መሪዎች በሻራም ኤል ሼክ የተዘጋጀው ጉባዔ ላይ እንደሚሳተፉ የግብጽ መንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን፣ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ሰኞ ዕለት በሚጀመረው ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት ወደ ግብጽ ከማምራታቸው በፊት እስራኤልን ይጎበኛሉ ተብሏል።

ቅዳሜ ዕለት በቴል አቪቭ የተካሄደው ትዕይንተ ሕዝብ ላይ ልጃቸው ኢቫንካ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር ንግግር አድርገዋል።

በጋዛ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የማስለቀቅ ስምምነት ሐማስ 48 ታጋቾችን ለመልቀቅ 72 ሰዓታት የተሰጠው ሲሆን ይህም ሰኞ ዕለት ያበቃል።

ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የሆኑት ኦስማ ሐምዳን ለኤኤፍፒ አንደተናገሩት "በስምምነቱ ላይ እንደተፈረመው የእስረኛ ልውውጥ ማድረግ የሚጀመረው ሰኞ ማለዳ ነው። እናም በዚህ ረገድ ሌላ ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም" ብለዋል።

አክለውም በስፍራው የሚገኙ የሐማስ ታጣቂዎች የእንቅስቃሴውን መሪዎች የእስረኞች ልውውጥ የሚደረግበትን ስፍራ አላሳወቁም ብለዋል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. የቤተሰብ አባሉ የተገደለበት እና የታገተበት አቪቭ ሐቭሮን ለቢቢሲ "መለቀቃቸው ለማኅበረሰቡ በጣም ጠቃሚ ነው. . . ያለ እዚያ ሕይወታችንን ዳግም መጀመር አንችልም" ብሏል።

"እህቶቼ እና ሁለት አማቾቼ ተገድለዋል። ሰባት የቤተሰብ አባላቶቼ ታግተዋል።ታላቅ እህቴ፣ልጇ፣ የልጅ ልጇ ታግተዋል። አራት የቤኤሪ አባላት (ማኅበረሰብ አባላት) አስከሬን በጋዛ ነው ያለው"

በጋዛ ሐማስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹን ጠርቶ በቅርቡ የእስራኤል ጦር ለቅቆ የወጣባቸውን አካባቢዎች እንዲቆጣጠሩ ማዘዙን ምንጮች ተናግረዋል።