ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች መውጣቱን አስታወቀ።
የእስራኤል ወታደሮች ስምምነት ወደተደረሰባቸው አካባቢዎች ቢመለሱም በአጠቃላይ ከጋዛ ሰርጥ ለቀው አልወጡም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ሲጓዙ የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ አካባቢ እስራኤል ከፍተኛ ድብደባ ስትፈጽም ቆይታለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ የእስራኤል መንግሥት ይሁንታ ከሰጠው በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ቀጣዩ የሰላም ዕቅዱ ዝርዝር ላይ ድርድር ይቀጥላል።
በስምምነቱ መሠረት ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች ይለቃል። በሐማስ ሥር ካሉት 20 የሚደርሱት ታጋቾች በሕይወት እንዳሉ ይታመናል። ሐማስ የ28 ታጋቾችን አስክሬንም ያስረክባል።
እስራኤል 250 ፍልስጤማውያን እስረኞች ትለቃለች። ከእስረኞቹ መካከል 100 የሚሆኑት ወደ ዌስት ባንክ እና አምስቱ ወደ ምሥራቅ እየሩሳሌም ይለቀቃሉ።
ከጋዛ የታገቱ 1,700 ፍልስጤማውያንም ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እርዳታ ባልተገደበ ሁኑታ ወደ ጋዛ እንዲገባም ስምምነቱ ያዛል። የጋዛ ነዋሪዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
ከዛሬ በኋላ 600 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ይገባሉ።
ተመድ እንዳለው፤ ከ500,000 በላይ ፍልስጤማውያን ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል።
እስራኤል በጋዛ ረሃብ መኖሩን አታምንም።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የነበሩ 200 የአሜሪካ ወታደሮች ወደ እስራኤል ይገባሉ። የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚከታተሉም ተገልጿል።
በጋዛ የሚኖሩ የዐይን እማኝ እንደተናገሩት፤ የእስራኤል ወታደሮች ከሰሜን ምዕራብ የጋዛ አካባቢዎች ለቀው እየወጡ ነው።
ከደቡባዊ ካሀን ዩኑስ አካባቢ የተወሰኑ የእስራኤል ወታደሮች እየለቀቁ መሆኑም ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ "ወታደሮቻችን ስምምነት ወደተደረሰባቸው አካባቢዎች ማምራት ጀምረዋል" ብሏል።
የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እንደተናገሩት፤ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ አካባቢዎች መውጣታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።
ባለፈው ሳምነት በዋይት ሀውስ ይፋ የተደረገ ካርታ የእስራኤል ወታደሮች እስከየትኛው መስመር ድረስ መጓዝ እንዳለባቸው አስቀምጧል።
የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረገበት የመጀመሪያው ዙር የሰላም ዕቅድ፤ የእስራኤል ወታደሮች በ53 በመቶ የጋዛ አካባቢዎች ይቆያሉ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ቤታንያሁ ታጋቾችን ለማስመለስ የገቡትን ቃል እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የእስራኤል ወታደሮች "አሁንም ድረስ ሐማስን ከሁሉም አቅጣጫ ከበዋል" ሲሉም ገለጸዋል።
የትራምፕ የሰላም ዕቅድ በቀጣይ ያስቀመጠው ነጥብ ሐማስን ትጥቅ ማስፈታትን የያዘ ነው። ሐማስ ግን በዚህ ላይ መስማማቱን አልገለጸም።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስከተደረሰበት ቅጽበት ድረስ እስራኤል በጋዛ ጥቃት ስትፈጽም እንደነበር የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 17 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች ቢወጣም፣ ባለበት አካባቢ ሆኖ "የደኅንነት ስጋት የማስወገድ" ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ አካባቢዎች ሲወጡ በምትኩ የሐማስ ኃይሎች ተሰማርተዋል።
የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ጋዛን በማስተዳደር ረገድ ሐማስ ሚና እንደማይኖረው ይገልጻል።
ሐማስ በበኩሉ ጋዛን መልሶ ለመገንባት "የአረብ አገራትና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር ያሻል" ብሏል።
የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሲወጡ ፍልስጤማውያን ንብረታቸውን ሸክፈው ወደየመንደራቸው ሲመለሱ ታይተዋል።
ከስድስት ልጆቹና ባለቤቱ ጋር ከጋዛ የተፈናቀለው መምህር አላ ሳሌህ "መንገዱ ረዥምና ከባድ ነው። ምግብና ውሃ የለም" ይላል።
ጃባሊያ ወደሚገኘው ቤቱ እየተመለሰ ያለው ዋል አል-ናጂር "ቤቴ ቢወድምም፤ ፍርስራሽ ብቻ ቢቀርም እመለሳለሁ። በድንኳን ውስጥም ቢሆን እኖራለሁ" ብሏል።
ሼኽ ራድዋን፣ ሳብራ እና ዘይቱን የተባሉትን መንደሮች ጨምሮ አብዛኛው ጋዛ እንዳልነበረ ሆኗል።
ሐማስ ባደረሰው ጥቃት 1,200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ወረራ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ67,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል።
ከ18,000 በላይ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።
የተመድ መርማሪ አካል እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች ሲል ከሷል። እስራኤል ግን አስተባብላለች።















