የእስራኤል መንግሥት የጋዛን የተኩስ አቁም እና የታጋቾች ስምምነትን አጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል መንግሥት የተኩስ ማቆም እና ታጋቾችን እና እስረኞችን ወደ መፍታት የሚያመራውን የጋዛ ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ አጽድቋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ "መንግሥት አሁን ሁሉንም ታጋቾች (በሕይወት ያሉትን እና የሞቱትን) የሚፈቱበትን ማዕቀፍ አጽድቋል" ሲሉ ጽፈዋል።
የእስራኤል ጦር 53 በመቶ ጋዛን ወደ ሚቆጣጠርበት መስመር ይወጣል።
ሐማስ በሕይወት ያሉ 20 ታጋቾችን በ72 ሰዓታት ውስጥ መልቀቅ አለበት። በመቀጠልም የሞቱትን የ28 ታጋቾች አስከሬን መመለስ ይጠበቅበታል።
እስራኤል በበኩሏ 250 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን የዕድሜ ልክ እስረኞችን እና ከጋዛ የተያዙ አንድ ሺህ 700 እስረኞችን እንደምትለቅ የፍልስጤም ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ መኪናዎች ምግብ፣ መድሀኒት እና ነዳጅ ይዘው ወደ ጋዛ በመግባት ለሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች እንደሚያደርሱ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል። አብዛኛዎቹ በድንኳን ወይም በፍርስራሾች ስር ተጠልለው የሚገኙ ናቸው።
እስራኤል በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት ውስጥ በየቀኑ 400 የእርዳታ መኪኖች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ትፈቅዳለች። ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ስር የሚመራ እና ወደ 200 የሚጠጉ ኃይሎችን የያዘ ቡድን የጋዛን የተኩስ አቁም ሁኔታ ይቆጣጠራል ሲሉ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
ኃይሉ ከግብጽ፣ ከኳታር፣ ከቱርክ እና ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተውጣጡ ወታደሮችን እንደሚያካትትም ታውቋል።
ሚናቸው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን "መቆጣጠር፣ መከታተል እና ምንም ዓይነት ጥሰቶች ወይም ወረራ አለመኖሩን ማረጋገጥ ነው" ብለዋል ባለሥልጣኑ።
ሌላኛው የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው በጋዛ የአሜሪካ ጦር እንደማይሰማራ ገልፀው የአሜሪካ ሚና የጋራ ቁጥጥር ማዕከልን መፍጠር ነው፤ ይህም የሚሰማራውን ሁለገብ ኃይል "ያዋህዳል" ብለዋል።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ቀጣይ ምዕራፍ ላይ ተጨባጭ ንግግሮች የሚጀመሩት የታጋቾች መፈታት ሲጠናቀቅ ይሆናል።
ስምምነቱ በእስራኤል መንግሥት የፀደቀው አርብ ረፋድ ላይ የአገሪቱ ካቢኔ ለሰዓታት ስብሰባ ካደረገ በኋላ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው የካቢኔውን ስብሰባ ተቀላቅለዋል።
ቀኝ ዘመሙ ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር ከድምጽ አሰጣጡ በፊት እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ እስራኤል በነፍስ ግድያ የከሰሰቻቸውን እስረኞችን እንድትፈታ ስለሚያደርግ እንደሚቃወሙ ተናግረው ነበር።
ሐማስ "አልፈረሰም" ከማለት ባለፈ የአገሪቱን ጥምር መንግሥት ለመበተን ድምጽ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
ስምምነቱ ጉልህ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ቢደረግበት፣ ከትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ሃሳብ የተወሰነውን ብቻ ይሸፍናል። ወሳኝ የተባሉት እንደ ሐማስ ትጥቅ ማስፍታት እና የጋዛ የወደፊት አስተዳደርን ጨምሮ ያሉ ጉዳዮች አሁንም አልተፈቱም።
ሐማስ የፍልስጤም መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ትጥቁን እንደማይፈታ አስታውቋል።
በትራምፕ ዕቅድ መሠረት ደግሞ ጋዛን ለፍልስጤም አስተዳደር ከመሰጠት በፊት በጊዜያዊ አስተዳደር ስር እንደሚቆይ ያሳያል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ መታወጅን ተከትሎ በእስራኤል እና በጋዛ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።
በቴል አቪቭ የታጋቾች አደባባይ ነዋሪዎች የእስራኤልን እና የአሜሪካን ባንዲራ በማውለብለብ "ወደቤታቸው እየመጡ ነው" በማለት ርችት በመተኮስ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ደቡባዊ ጋዛ ደግሞ በጦርነቱ የተፈናቀሉ እና የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ሃና አልማድሁን "እፎይታ እና ብሩህ ተስፋ" እንደተሰማቸው እና ሰሜን ወደሚገኘው ቤታቸው ለመመለስ እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል በተፈፀመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሌሎች ደግሞ ታግተዋል። የእስራኤል ጦር በምላሹ በጋዛ ጦርነት ከፍቷል።
የግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለፀው ከሆን ከጦርነቱ መጀመር ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 67,160 ሰዎች ተገድለዋል።
እነዚህ ቁትሮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት ትክክለኛ ተደርገው ይወሰዳሉ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፉ ባለሞያዎች በጋዛ ከተማ በነሀሴ ወር ረሃብ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ 182 ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች 460 ሰዎች በምግብ እጥረት መሞታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።















