የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት የማይተባበር ከሆነ "ድምጥማጡ ይጠፋል" አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት የማይተባበር ከሆነ "ድምጥማጡ ይጠፋል" ሲሉ ተናገሩ።
ጄዲ ቫንስ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት አተገባባር "ከሚጠበቀው በላይ በተሻለ ሁኔታ" እየሄደ ነው፤ እንዲሁም ስምምነቱ ጸንቶ ይቆያል ብለዋል።
ቫንስ እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት ታጣቂ ቡድኑ አሜሪካ በምክረ ሃሳቧ ላይ ያቀረበችውን እና ገና ስምምነት ላይ ያልተደረሰበትን ትጥቅ መፍታት በመጥቀስ "ሐማስ የማይተባበር ከሆነ ድምጥማጡ ይጠፋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ታላላቅ አጋሮች ሐማስ ተገቢ ባልሆነ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ "ሐማስን ለማስተካከል፣ ወደ ጋዛ በከፍተኛ ኃይል ለመግባት" ዝግጁ ናቸው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቫንስ ወደ እስራኤል ያቀኑት እሁድ ዕለት በሐማስ እና በእስራኤል ጦር መካከል ግጭት ተቀስቅሶ 12 ቀናት ያስቆጠረውን የተኩስ አቁም አደጋ ላይ የወደቀ በመሰለበት ወቅት ነው።
እስራኤል ሐማስ ሁለት ወታደሮቿን መግደሉን ገልጻ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ሐማስ አሁንም ትክክል የሆነውን ያደርጋል የሚል ተስፋ አለ" ካሉ በኋላ "ያንን የማያርጉ ከሆነ ግን የሐማስ መጨረሻ ፈጣን፣ በቁጣ የተሞላ እና ድምጥማጡን የሚያጠፋ ይሆናል" ብለዋል።
ቫንስ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር የሚካሄደውን ጦርነት የሚያስቆም እና ቋሚ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደረስ እንዲደራደሩ ግፊት ያደደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቫንስ በደቡብ እስራኤል መግለጫውን በሰጡበት ወቅት ሁሉቱ ልዩ መልክተኞች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጄሬድ ኩሽነር አብረዋቸው ነበሩ።
ዊትኮፍ እና ኩሽነር ሰኞ ዕለት እስራኤል ከደረሱ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር ተነጋግረዋል።
ትራምፕ ምክትላቸውን እና ልዩ መልዕክተኞቻቸውን ዳግም ወደ እስራኤል የላኩት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ባለበት እንዲቀጥል ግፊት ለማድረግ እና የጋዛ የሰላም ዕቅድ ወሳኝ ምዕራፍ ነው የተባለው ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ንግግር እንዲጀመር ለማድረግ ነው።
ይህ የሁለተኛው ምዕራፍ ንግግር በፍልስጤም ግዛት ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም፣ ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይልን ማሰማራት፣ የእስራኤል ጦርን መውጣት፣ እንዲሁም የሐማስ ትጥቅ መፍታትን ያካተተ ነው።
እስራኤል ከዚህ በፊት ሐማስ የሞቱትን ታጋቾች አስከሬን በሙሉ እስካልመለሰ ድረስ ለንግግር አልቀመጥም ብላ ነበር።
ቫንስ፣ ዊትኮፍ፣ እና ኩሽነር በመጀመርያው የሰላም ዕቅዱ መሠረት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ባለበት መቀጠሉን እና አለመፍረሱን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የአሜሪካ ባለሥልጣናት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከስምምነቱ "ወጥተው" ሐማስ ላይ ዳግም ጥቃት ይከፍታሉ የሚል ስጋት አላቸው።
ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት ለእስራኤል ፓርላማ ከጄዲ ቫንስ ጋር "ስለ ፀጥታ ተግዳሮቶች" እንዲሁም "የፖለቲካ እድሎች" ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ገልፀዋል።
አክለውም ሐማስ እሁድ ዕለት "ግልጽ በሆነ መልኩ" የተኩስ አቁሙን መጣሱን ተከትሎ 153 ቶን ቦምብ በጋዛ ላይ ማዝነባቸውን ለፓርላማው ተናግረዋል።
"አንደኛው እጃችን መሳሪያ ይይዛል፤ ሌላኛው እጃችን ለሰላም ይዘረጋል" ያሉት ኔታንያሁ፣ ሰላም የምትመሰርተው ከጠንካሮች ጋር እንጂ ከደካሞች ጋር አይደለም። ዛሬ እስራኤል ከምን ጊዜውም በላይ ጠንካራ ናት" ብለዋል።
በካይሮ የሚገኙት የሐማስ ዋና ተደራዳሪ ካሊል አል-ሀያ በበኩላቸው ቡድናቸው እና ሌሎች የፍልስጤም አንጃዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ እና "እስከመጨረሻው ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸወን" አጽንኦት ሰጥተዋል።
"ከአደራዳሪዎቹ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሰማነው ነገር የጋዛ ጦርነት ማብቃቱን አረጋግጦልናል" ሲሉ ለግብፅ አልቃሄራ ኒውስ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምንም እንኳን በልዩ መሳሪያ እጥረት የተነሳ በፍርስራሹ ውስጥ ያሉትን ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት "እጅግ አስቸጋሪ" ቢያደርግበትም ሐማስ በጋዛ የሚገኙትን የሟቾችን አስከሬን ለማስረከብ ፈቃደኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ሐማስ የሁለት እስራኤላዊያን ታጋቾች አስከሬንን በጋዛ ለቀይ መስቀል ማስከረቡን ገልፀዋል።















