በኬንያ ምርጫ ሁለቱ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎቹ አንገት ለአንገት ተናንቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኬንያ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተገኘው ውጤት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው በምርጫ ኮሚሽኑ የተረጋገጠ ሲሆን ሁለቱ ተፎካካሪ እጩዎች በቅርብ ርቀት በመፎካከር ላይ ናቸው።
እስካሁን በተረጋገጠው ድምጽ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ 51 በመቶ ሲመሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ 48 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ኃላፊ ማክሰኞ የተካሄደውን ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረግ በጣም አዝጋሚ መሆኑን አምነዋል።
በሁለቱ ዋና ዋና እጩዎች ደጋፊዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ውጤቱን የማረጋገጥ ሥራ በተደጋጋሚ ተቋርጧል።
የራይላ ደጋፊዎች ውጤቱን የማጣራት ሂደቱን በተደጋጋሚ በማስተጓጎላቸው ታውቋል። አንዳንድ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ድምጽ እያጭበረበሩ ነው በማለት ከሰዋል።
በውዝግቡ መካከል የራይላ የምርጫ ዘመቻ ሥራ አስኪያጅ የምርጫ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደሚጠቀሙበት በማቅናት ውጤቱን የማጣራት ሂደቱን ተችተዋል።
"የኬንያው ቦማስ የወንጀል ማዕከል መሆኑን ለህዝብ ማሳወቅ እፈልጋለሁ" ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሳይታባኦ ኦሌ ካንቾሪ ተናግረዋል።
በኋላም ድምድ ማጉያው ተቋርጦ ከስፍራው እንዲርቁ ተደርጓል። ቦማስ በናይሮቢ የሚገግ የባህል ማዕከል መጠሪያ ሲሆን እንደ ዋና የድምጽ መቁጠሪያ ማዕከል በመሆን ያገለግላል።
በስፍራው ጸጥታውን ለማስከበር የአድማ በታኝ ፖሊሶች በህንጻው ተሰማርተዋል።
ከ292 የምርጫ ክልሎች የ141 ቱ ውጤት ተረጋግጧል።
የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ከ46 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ይፋዊ መረጃን በመጠቀም ጊዜያዊ ውጤቶችን እየለቀቁ ነበር። በሁለቱ እጩዎች መካከል ከፍተኛ የውጤት መቀራረብ መኖሩን አሳይተዋል።
ወደ 14 ሚሊዮን ድምጽ የሰጡ ሲሆን ይህም ከተመዘገቡት መካከል 65 በመቶ ያህሉ ነው።
የምርጫ ኮሚሽኑ እስከ ማክሰኞ ድረስ ውጤት ማሳወቅ ይጠጠበቅበታል።
ውጤቱን ለማሳወቅ “አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረግ ተጠብቆብናል” ሲሉ የኮሚሽኑ ኃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ ተናግረዋል።
ይህም አሠራራቸውን ለማፍጠን እንደሚረዳቸውን አስታውቀዋል።
ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል በአካባቢው ተሰማርቷል።
ከምርጫ ጣቢያዎች የተሰበሰበው እና በኮሚሽኑ ድረ ገጽ የተለጠፈው ጊዜያዊ ውጤትን በመጠቀም መገናኛ ብዙሃን የሰሯቸው የውጤት መግለጫዎች መለያየት ግርታን ፈጥሯል።
ድረ ገጹ በመረጃ በርባሪዎች ተሰብሮ ውጤት ተቀይሯል መባሉን የኮሚሽኑ ባለስልጣናት አስተባብለዋል።
ኬንያውያን ምን እያሰቡ ነው?
ከዚህ ቀደም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተነሳ አለመረጋጋት በመኖሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል።
እአአ በ2007 የተካሄደው ምርጫ ተሰርቋል በሚል በተነሳ አለመረጋጋት 1ሺህ 200 ያህል ሰዎች ሲገደሉ 600 ሺህ ያህሉ ደግሞ ከመኖሪያ ቤተታቸው ተፈናቅለዋል።
በ2017 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከፍተኛ የሎጂስቲክ ክፍተት ነበር በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል።
የአሁኑ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ባለስልጣናት ጫና ውስጥ ገብተዋል።
በመላ ሃገሪቱ እንስቃሴዎች ቀዝቀዝ ያሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።
በኬንያ የምርጫ ማጭበርበር ስሞታ ለዘመናት የነበር ጉዳይ ነው።
በዘንድሮው ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግም ተቀናቃኞችን ፍርድ ቤት ደጅ ከመጥናት አልመለሰም
ውጤት መቼ ይታወቃል?
ውጤቱ የሚታወቅበት ቀን ባይታወቅም የምርጫ ኮሚሽኑ ድምጽ የማጣራት ሥራውን እያከናወነ ነው።
የአሸናፊውን ዕጩ ማንነት የሚያሳውቀው ኮሚሽኑ ይሆናል።
ምርጫውን ለማሸነፍ ዕጩዎች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የመራጮች ድምጽ ማግኘት እና በ24 ክልሎች ከ25 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ካልሆነ ምርጫው በድጋሚ ጷጉሜ ውስጥ የሚከናወን ይሆናል።












