ከቀናት በፊት በስለት የተወጋው ሳልማን ሩሽዲ መናገር ጀመረ

ሳልማን ሩሽዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

‘ሳታኒክ ቨርስስ’ በሚለው መጽሃፉ በርካታ ውዝግቦችን ያስተናገደውና ከቀናት በፊት በስለት የተወጋው ደራሲ ሳልማን ሩሽዲ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እንደወጣለትና መናገርም መጀመሩ ተዘግቧል።

የ75 አመቱ ሳልማን ሩሽዲ በኒውዮርክ በነበረ አንድ ዝግጅት ላይ ንግግር እያደረገ ባለበት ወቅት ጥቃት የተሰነዘበረበት ሲሆን ህይወቱም በአስጊ ሁኔታ ላይ ነበር።

የደራሲው ወኪል አንድሪው ዋይሊ የሳልማን መናገር መጀመሩን ለአሜሪካ ሚዲያ ያረጋገጠ ሲሆን ነገር ግን ቀደም ሲል ደራሲው አይኑ ሊጠፋ እንደሚችል ተናግሯል።

ሳልማን ሩሽዲ አንዳንድ ሙስሊሞች እስልምናን ያዋረደ በሚሉት ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ ‘ በተሰኘው ልብ ወለድ መጽሃፉ ለዓመታት ያህል የግድያ ዛቻዎች ገጥመውታል።

በደራሲው ላይ ጥቃት በማድረስ የተከሰሰው ግለሰብ በግድያ ሙከራ ወንጀለኛ አይደለሁም በማለት ትናንት ቅዳሜ እለት ቃሉን የሰጠ ሲሆን በእስርም ላይ ይገኛል።

የ24 አመቱ ሃዲ ማታር ሳልማን ንግግር ወደሚያደርግበት መድረክ ሮጦ በመሄድ ደራሲውን ፊቱን፣ አንገት እና ሆዱ ላይ ቢያንስ 10 በስለት ወግቶታል ተብሏል።

ጥቃቱን ተከትሎ አንድሪው ዋይሊ አንደኛው ክንዱ ላይ የሚገኘው ነርቭ እንደተጎዳ፣ ጉበቱ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት እና አይኑን ሊያጣ እንደሚችል ተናግሯል።

የደራሲው የጤና ሁኔታ ምን ላይ እንደሆነ ያልተገለጸ ቢሆንም በርካታ ደራሲዎች እና ምሁራን ሳልማን መናገር መቻሉን በማወቃቸው እፎይታ እንደተሰማቸው በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት የቻውታኩዋ ተቋም ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሂል የሳልማን መናገር መጀመርን ዜና በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተውታል።

በዝግጅቱ ላይ ለሳልማን ቃለ መጠይቅ ሊያደርግ የነበረው ሄንሪ ሪሴ መጠነኛ የሆነ የጭንቅላት ጉዳት አጋጥሞታል። ሄንሪ በጽሁፋቸው ምክንያት ጥቃትና ማስፈራሪያ ደርሶባቸው በግዞት ላይ ላሉ መጠለያ የሚሰጥ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ተባባሪ መስራች ነው።

‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ በአውሮፖውያኑ 1988 ከታተመ በኋላ ደራሲው ለ10 አመታት ያህል ለመደበቅ ተደዷል። በርካታ ሙስሊሞች ነብዩ መሃመድ መጽሃፉ ላይ የተሳሉበት መንገድ የሚያዋርድ ነው በማለት ቁጣቸውንም ገልጸዋል።

በርካታ የግድያ ዛቻዎች የገጠሙት ሲሆን የያኔው የኢራኑ መሪ አያቶላህ ኻሜይኒ ሳልማንን ለመግደል ፋትዋ (ድንጋጌ) ያወጡ ሲሆን ለገዳዩም ሶስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅተው ነበር።