በሕንድ የሚቀናበሩ ፀረ-ሙስሊም ሙዚቃዎች ቁጥር ለምን አሻቀበ?

ቻቱርቬዲ የሙዚቃ ስቱዲዮ ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, ቻቱርቬዲ የሙዚቃ ሥራውን የጀመረው በሃይማኖታዊ መዝሙሮች ነው

ሳንዲፕ ቻቱርቬዲ 29 ዓመቱ ነው። አዲስ ሙዚቃ ከአድማጮቹ ጆሮ ለማድረስ ተፍ ተፍ እያለ ነው። በሰሜን ሕንድ በምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት አዮዲያህ ከተማ ከምትገኘው ሱቱዲዮ ተገኝቷል።

ዘፈኑ ስለ አንድ መስጂድ ያወራል። የሒንዱ እምነት ተከታዮች በመስጂዱ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ዘፈኑ በሙስሊሞች ላይ በሚሰነዝሩ ጥቃቶች የተሞላ ነው። ቻቱርቬዲ ሙዚቃው ወደ ዘርፉ ገበያ እንደሚያስገባውም ተማምኗል።

የቻቱርቬዲ ሙዚቃ ዩቲዩብ እና ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተሰራጩ ከሚገኙ ቀኝ ዘመም የሒንዱ ትርክቶች መካከል ናቸው። ትኩረታቸውም በሙስሊሞች ዙሪያ አደገኛ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ነው።

ግጥሞቹ ስድብ አዘል ወይም ማስፈራሪያ የያዙ ናቸው። መሠረታቸው የሒንዱ እምነት ተከታዮች ለዘመናት ተበድለዋል የሚል ነው። አሁን ደግሞ የደረሰውን ኪሳራ መመለሻ ጊዜ ነው ይላሉ።

እነዚህ ሙዚቃዎች የገቢ ምንጭ ከመሆናቸውም በላይ ዘፋኞችንም ወደ ታዋቂነት ማማ ያደርሳሉ የሚሉት ፀሐፊ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ኒላንጃን ሙክሆፓድያይ ናቸው።

ለእርሳቸው እነዚህ ሙዚቃዎች አይደሉም።

“እነዚህ ጦርነት ካልተጀመረ ባዮች ናቸው። ሙዚቃ ጦርነት የሚያሸንፍ ይመስላቸዋል። ይህ ሙዚቃን ያለ ዓላማው መጠቀም ነው። ለዓመታትም ተግባራዊ ተደርጓል” ይላሉ።

ቻቱርቬዲ የዩቲዩብ ቻናሉ ከመታገዱ በፊት ሙዚቃው በሚሊዮኖች ታይቷል። እገዳው የመጣው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቅሬታ ማስገባታቸውን ተከትሎ ነው። ሙስሊሞች ናቸው ሙዚቃው አግባብ አይደለም እያሉ ቅሬታ ያስገቡት ይላል።

ቻቱርቬዲ ስቱዲዮ ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, ቻቱርቬዲ የሙዚቃ ሥራዎቹን የሚሰራው ጥራት በሌለው ጊዜያዊ ስቱዲዮ ነው።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቻቱርቬዲ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማጣቱ” ቢቆጭም ከዩቲዩብ እያገኘ ያለውን ገንዘብ ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆነም። የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ለመስራት ግን 253 ዶላር ይፈጅበታል።

“ከዩቲዩብ ብዙ ገንዘብ እያገኘሁ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እንደ ብሔረተኛ-አብዮታዊ ዘፋኝ ያገኘሁት እውቅና ነው” ሲል በልበ ሙሉነት ተናግሯል።

ቻቱርቬዲ አሁን ዩቲዩብ ላይ አዲስ ቻናል ከፍቷል። የለቀቃቸው አንዳንድ ቪዲዮዎች ያላቸው ዕይታ እምብዛም ነው። ይህንን በአዲሱ ዘፈኑ ለመለወጥ ተስፋ አድርጓል።

ቻቱርቬዲ በሙዚቃው ብዙ ጊዜ ሙስሊሞችን ዒላማ አድርጓል ተብሎ ቢከሰስም ይቅርታ አይጠይቅም። “የራሴ ለማግኘት እጆቼን አጣጥፌ ብለምን ትስማማለህ? አትቀበልም። ስለዚህ ቀስቃሽ መሆን አለብን፣ አይደል?” ይላል።

አፔንድራ ራና መቀመጫው ዴልሂ አቅራቢያ በምትገኘው ዳድሪ ነው። እሱም ተመሳሳይ ሙዚቃ ያዘጋጃል።

ተልዕኮዬ ታሪክን “ማረም ነው” ይላል። ዘፈኖቹ የሂንዱ ተዋጊዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። የሙስሊም ገዥዎችንም ተራ አድርጎ ይስላል።

“ብዙ እውነት የሆኑ ነገሮች ተደብቀው ውሸት ተጭኖብናል” ሲል በትምህርት ቤቶች ስለሚሰጠው የታሪክ ትምህርት ተናግሯል።

ራና ከዩቲዩብ ቪዲዮዎቹ ጥሩ ገቢ እያገኘ መሆኑን ያስረዳል።

“ለሕንድ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘን ነው። ዩቲዩብ የሚከፍለው በዶላር ነው” ብሎ ዓይኑን ግድግዳው ላይ ዩቲዩብ ከፍተኛ ተከታይ ላላቸው ቻናሎች ወደሚሰጠው ሽልማት እና ወደ ሒንዱ ተዋጊ ምስሎች ወረወረ።

ራና የአምልኮ እና የፍቅር ዘፈኖችን ከማቀናበር ወደ “ታሪካዊ” ሥራዎች ከተሸጋገረበት ጊዜ ጀምሮ በዳድሪ ኮከብ ለመሆን በቃ።

በዩቲዩብ ላይ ወደ 400,000 የሚጠጉ ተከታዮች አሉት። ብዙዎቹ ዘፈኖቹም በሚሊዮን ለሚቆጠር ጊዜ ታይተዋል።

የሙዚቃ ፖስተሮች
የምስሉ መግለጫ, አፔንድራ ራና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዩቲዩብ ሰብስክራይበሮች አሉት።

የሙዚቃ ቪዲዮ ለመስራት 100 ዶላር እንደሚያስወጣው ራና ይናገራል። ቪዲዮዎችን መቅረጽን ጨምሮ ካሜራ እና ሌሎች የሙያ ባለቤቶችን ያካተተ ቡድን አለው።

ሙክሆፓድያይ እንደሚሉት ከሆነ ሙዚቃን በቁጥር አናሳ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማስጠቃት ማዋል ከበፊትም ጀምሮ የመጣ ነው።

እአአ በ1989 በቀኝ ዘመሙ ቪሽዋ ሒንዱ ፓሪሻድ (ቪኤችፒ) ባዘጋጀው አወዛጋቢው የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ምክንያት በ1992 ባብሪ የተባለ መስጂድ መፍረሱን ያስታውሳሉ።

“ከዚያ በፊት የኦዲዮ ካሴቶች ኢንዱስትሪ ብቅ አለ። ሃይማኖታዊ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይካተቱባቸው ነበር። ሰዎችን ለማነሳሳትም ሲባል እነዚህ ካሴቶች በተከታታይ ይጫወቱ ነበር” ብለዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላም ድምፁ እየጨመረ መጥቷል።

“ሕንድ ውስጥ መኖር ከፈለክ ቫንዴ ማታራም (“እናቴ አመሰግንሽላሁ”) ማለትን ተማር…በአቅምህ መኖርንም ተማር” ወይም “ሒንዱዎችን ደካማ አድርጎ ማሰብ የጠላት ስህተት ነው” የሚሉ ሥራዎች ማን ላይ እንዳነጣጠሩ መገመት ከባድ አይደለም።

እነዚህ ዘፈኖች ቀኝ ዘመም ድርጅቶች የካድሬዎቻቸውን “ቀልብ እንዲገዙ” ረድተዋቸዋል።

የቀኝ ክንፍ ሒንዱ ራክሻ ዳል ቡድንን የሚመራው ፒንኪ ቻውድሪ “ወጣቶች ጉጉታቸውን እና ሞራላቸውን ከፍ ስለሚያደርጉ እነዚህን ዘፈኖች ይወዳሉ” ሲሉ እንዲህ ዓይነት ዘፈኖች ለወጣቶች ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያግዙ ይከራከራሉ።

በስልክ ቪዲዮ የሚያይ ግለሰብ
የምስሉ መግለጫ, ብሔርተኛ ሙዚቃዎች በበርካታ ወጣቶች ይታያሉ።

“እነዚህን ዘፈኖች ሳዳምጥ ድንገቴ የሆነ ከፍተኛ ኃይል በፍጥነት ይሰማኛል። በአንድ ወቅት የተደረጉብንን ነገሮች እና አሁን የት እንደደረስን ያስታውሰኛል” ይላል ቪጃይ ያዳቭ።

እንደዚህ አይነት ሙዚቃዎችን ማዳመጥ እንደሚወድ የሚናገረው የ23 ዓመቱ ያዳቭ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኝ ሰዓሊ ነው።

ያዳቭ “ድንገቴ የሆነ ከፍተኛ ኃይል” ሲል የተናገረው በሚያዝያ ወር በሚከበሩት የሒንዱ በዓላት ወቅት በበርካታ ግዛቶች ከፍተኛ ግጭቶች የተከሰቱበት ሁኔታን ያሳያል ተብሎ ይታመናል።

በበዓላቱ ወቅት ሒንዱዎች ለሃይማኖታዊ ሰልፎች ወጥተው ሙስሊሞች ወደሚበዙባቸው አካባቢዎች ሲቃረቡ ቀስቃሽ ሙዚቃዎች በድምጽ ማጉያዎች ይስተጋባሉ።

ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ የቻቱርቬዲ የ2016 ሙዚቃን ጨምሮ ጸያፍ እና ቀስቃሽ ዘፈኖች ሁከትን ለመቀስቀስ አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብሏል።

ቻቱርቬዲ እነዚህን ክሶች ውድቅ ያደርጋል።

“በሙዚቃዬ ግንዛቤን ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው። ምንም ነገር በፍቅር አይመጣም። መታገል እና የእኛ የሆነውን መንጠቅ አለብን” ይላል።