ለ30 ዓመታት በፖሊስ እየተፈለገ 28 ፊልሞች ላይ የተወነው ሕንዳዊ

የዚህ ሕንዳዊ ታሪክ የተወናቸው ፊልሞች ስክሪፕ እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይመስልም።
ኦም ፕራካሽ "በጣም ተፈላጊ" ተብሎ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበት በ28 ፊልሞች ላይ የፖሊስ አባል ሆኖ ጭምር ተውኗል።
ኦም ፕራካሽ ወይም ፓሻ ካሉ በሕንዷ ፕራዴሽ ግዛት ዝነኛ ነው። በሚኖርበት አካባቢ ሁሉም ያውቀዋል።
በሰሜን ሕንዷ ሃሪያና ግዛት ደግሞ ሌላ ነው ታሪኩ። ፖሊስ ስሙን "በጣም የሚፈለጉ ወንጀለኞች" ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።
ቀደም ሲል የሕንድ ጦር ባልደረባ የነበረው ፕራካሽ፤ ላለፉት 30 ዓመታት ከዘረፋ እና ከግድያ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በጥብቅ ሲፈለግ ከርሟል።
እርሱ ግን በነጻነት በፕራዴሽ ግዛት ሕይወቱን ይገፋል። አዲስ ሕይወትም ጀምሯል። አዳዲስ ይፋዊ ሰነዶችን አውጥቶ፤ የአካባቢውን ሴት አግብቶ ሦስት ልጆች ወልዶ በሰላም ይኖራል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ግን ዕድል ፊቷን አዞረችበት። ፖሊስ የ65 ዓመቱን አዛውንት በጋዚያባድ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ኦም ፕራካሽ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ ብዙ ነገር አድርጓል። የከባድ መኪና ሾፌር ሆኖ ሠርቷል። በአቅራቢያው ያሉ መንደሮችን በመጎብኘት በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የአምልኮ መዝሙሮችን ዘምሯል። ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ በፖሊስ የሚፈለገው ፕራካሽ በ28 ፊልሞች ላይ መተወኑ ነው።
ኦም ፕራካሽ አሁን በእስር ላይ ይገኛል። በእስር ላይ ስላለ ስለቀረበበት ክስ የእርሱን አስተያየት ማካተት አልተቻለም።
በቁጥጥር ስር ያዋለው የፖሊስ አባል ኢንስፔክተር ቪቭክ ኩመር እአአ በ1992 በተፈጸመ ግድያ ተባባሪ ነበር ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኦም ፕራካሽ ከታሰረ ከሁለት ቀናት በኋላ ቢቢሲ ቤተሰቦቹን ፍለጋ ወደ መኖሪያው አቀና። በእነሱ በኩል ያለውን አስተያየት ለመስማት ነበር ጉዞው።
የ25 ዓመታት የትዳር አጋሩ ራጅኩማሪ እንዲሁም ከሦስቱ ልጆቹ ሁለቱ ቤት ነበሩ።
አሁንም በድንጋጤ ውስጥ እንዳሉ ነው። ከመኝታ ክፍሉ ፍራሽ ስር ራጅኩማሪ አንድ ጋዜጣ አወጣች። ባለቤቷ የተከሰሰባቸውን ወንጀሎች ዝርዝር የያዘ የሕንድ ጋዜጣ ነው። “ስለተፈላጊው ወንጀለኛ” ምንም አለማወቃቸው ያስደነገጣቸው ይመስላል። የሆነውን ለመረዳት እየሞከሩ እንደሆነ ተናግራለች።
"በ1997 ነበር ያገባሁት። እሱ ቀድሞ ያገባ እና በሃሪያና ከተማ ቤተሰብ እንዳለው ሳላውቅ ነው ያገባሁት" የምትለው ራጅኩማሪ፤ በባለቤቷ እንደተከዳች ታስባለች።

ኦም ፕራካሽ ማን ነው? የቀረበበት ክስስ?
ፕራካሽን አውቀዋለሁ የሚለው የናራይና መንደር ነዋሪው ኩማር፤ "ኦም ፕራካሽ በሕንድ ጦር የሬዲዮ ጓድ ውስጥ ለ12 ዓመታት የጭነት መኪና ሾፌር ሆኖ ሠርቷል። ለአራት ዓመታት ከሥራው በመጥፋቱ 1988 ላይ ተባረረ" ይላል።
ኦም ፕራካሽ ከተጠረጠረበት የግድያ ወንጀል በተጨማሪ በብዙ ሕግ-ወጥ ተግባራት ላይ መሳተፉን ኩማር ያስታውሳል።
እአአ በ1986 መኪና ሰረቀ፤ ከአራት ዓመታት በኋላ ሞተር ሳይክል ጨመረበት። የልብስ ስፌት ማሽን እና አነስተኛ ሞተር ሳይክል ሰርቋል ይላል ኩማር። ወንጀሎቹ በተለያዩ ግዛቶች የተፈፀሙ ናቸው።
ፕራካሽ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በዋስ የተፈታበት አጋጣሚዎችም እንደነበሩ ገልጿል።
በጥር 1992 ኦም ፕራካሽ እና ተባባሪው በብስክሌት የሚጓዝን ሰው ለመዝረፍ እንደሞከሩ ኩማር ያስታውሳል።
"ሰውዬው እምቢኝ አለ፤ በስለት ወጉት። የመንደሩ ነዋሪዎች ሲመጡባቸው አነስተኛ ሞተር ሳይክላቸውን ትተው ሸሹ" ሲል ያክላል።

እንደ ኩማር ከሆነ ተባባሪው ተይዞ “ለስምንት ዓመታት ያህል በእስር” አሳልፏል። በኋላም በዋስ ተለቀቀ።
ኦም ፕራካሽ ግን አልተገኘም። ዱካው ጠፋ። ፖሊስም "ወንጀል ፈጻሚ" በማለት ፈረጀው።
ፕራካሽ በቁጥጥር ሥር ከዋላ በኋላ ፈጽሞታል ከተባለው ግድያ በኋላ የመጀመሪያውን ዓመት በደቡባዊ የታሚል ናዱ እና አንድራ ፕራዴሽ ግዛቶች እየተዘዋወረ በቤተ መቅደሶች ተጠልሎ እንደነበረ ለፖሊስ ተናግሯል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሰሜናዊ ሕንድ አቀና። 180 ኪ.ሜ. ርቆ በጋዚያባድ ጎጆውን ቀለሰ። የጭነት መኪናዎችን ማሽከርከርም ጀመረ።
እአአ በ1997 ራጅኩማሪን ያገባት ፕራካሽ በ1990ዎቹ ፊልሞችን የሚሸጥ እና የሚያከራይ ሱቅ ነበረው። በአካባቢው ሰዎች ባጅራንግ ባሊ ወይም ባጅራንጊ ተብሎ ይጠራ ጀመር። ለአገሪቱ ሠራዊት በማገልገሉም "ፋውጂ ታው" (ወታደሩ አጎቴ እንደማለት ነው) ተብሎ ይጠራል።
እአአ ከ2007 ጀምሮ ደግሞ በሕንድ ቋንቋ በተዘጋጁ ፊልሞች አነስተኛ ሚናዎችን ወስዶ መተወን ጀመረ።
ሊቀ መንበር እና የፖሊስ ኮንስታብል ሆኖ ሳይቀር ተጫወተ። ከተወነባቸው ፊልሞቹ መካከል አንዱ ዩቲዩብ ላይ 7.6 ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል። የፊልሙ ቅንጭብጫቢ ክሊፖችም ብዙ ሚሊዮን ጊዜ ታይተዋል።
30 ዓመታት ማንነቱን ደብቆ የቆየው ፕራካሽ አንድ ትልቅ ስህተት ሠራ። ሁሉም አዳዲስ ሰነዶቹ የእሱን እና የአባቱን ትክክለኛ ስሞች ይዘዋል።

የራጅኩማሪ ታሪክ
የኦም ፕራካሽ አዲስ ቤተሰብም ሆኑ ጎረቤቶቹ ስለ "ቀደመ ወንጀለኛነቱ" ምንም ዕውቀት እንደሌላቸው ፖሊስም ይስማማል።
ጎጆ ከቀለሱ በኋላ ኦም ፕራካሽ የሆነ ነገር እየደበቀ መሆኑን መረዳቷን ራጅኩማሪ ተረድታለች።
ወደ ናራይና ወስዶ ከወንድሙ እና ከቤተሰቦቹ ጋር አስተዋውቋታል። የነገራት ግን ጓደኞቹ እንደሆኑ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ "አንድ ቀን የመጀመሪያ ሚስቱ መጥታ ግርግር ፈጠረች። በዚህም ቀድሞ አግብቶ እንደነበር አወቅኩ" ትላለች።
"እኔ እና ጎረቤቶቻችን ሁሉ ሌላ ትዳር እና አንድ ልጅ እንዳለው አወቅን። እኛም እንደተከዳን ተሰማን።"
ብዙ ጊዜ ቤት አይኖርም ነበር። የጭነት መኪና አሽከርካሪ ስለሆነ የማይመጣ ይመስላት ነበር። አሁን ስታስብ ግን ሌላኛዋን ሚስቱን ለመጎብኘት እንደሚሄድ ጠርጥራለች።
ትዳራቸው ንፋስ ገባው። ጥንዶቹ በየጊዜው ይነታረኩ ጀመር። እአአ በ2007 በድረጋሚ ጠፋ።
"በጣም ተስፋ ስለቆረጥኩኝ ከውስጤ አወጣሁት። ወደ አካባቢው መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሄጄ ትዳሬን ማፍረሴን ገለጽኩ። ግን ከሰባት ዓመታት በኋላ ተመልሶ መጣ። በድጋሚ መሄድ መምጣቱን ቀጠለ" ትላለች።
"ሰዉ ብዙ ስም ይሰጠናል። በመጣ ጊዜ ግን አባታችንና ሽማግሌ በመሆኑ ከማዘናችን የተነሳ ምግብ እንሰጠዋለን" ትላለች የ14 ዓመቷ ሴት ልጁ።

እንዴት ተገኘ?
ፕራካሽ በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ቢሆንም፤ የፖሊስ መዝገቦች በአብዛኛው ዲጂታል አይደሉም። በተለያዩ አውራጃዎች የሚገኙ የፖሊስ ጽህፈት ቤቶች መካከል መረጃ የመለዋወጡን ግንኙነት ባለመዳበሩ በሌሎች ወንጀሎች ተፈላጊ እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም።
በሃሪያና እአአ በ2020 የተደራጁ ወንጀሎችን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ጥቃቶችን፣ ሽብርተኝነትን እና የድንበር ዘለል ወንጀሎችን የሚከታተል ልዩ ግብረ ኃይል ተቋቋመ። ከአንድ ዓመት በኋላም -የኦም ፕራካሽ ፋይል አቧራው ተራግፎ ተከፈተ።
ግብረ ኃይሉ "በጣም ተፈላጊ" ከሆኑት ዝርዝር ውስጥ አስገባው። ግለሰቡን ለመያዝ የሚረዳ መረጃ ለሚያቀርብ 315 ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥም አስታወቀ።
ከዚህ ባለፈም በጣም ለረጅም ዓመታት ሲሸሹ የቆዩ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር የዋሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
በጋዚያባድ ለዓመታት የወንጀል ታሪኮችን በመከታተል ያሳለፈው የሕንድ ኤክስፕረስ ባልደረባው ጋዜጠኛ አሚል ብሃትናጋር "ፖሊስ የተዳፈኑ ጉዳዮችን የሚከፍተው ከሽብርተኝነት ወይም ከበርካታ ግድያዎች ጋር ሲገናኙ ነው። ወይም ጥቆማ ካገኙ ነው" ብሏል።
ግብረ ኃይሉ ይህንን ጉዳይ እንደገና ለመመርመር ለምን እንደወሰነ ግን ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም።
ከሁለት ወራት በፊት ፖሊሶች የናራይና መንደርን ጎበኙ። "በ50ዎቹ እና በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ እና ኦም ፕራካሽን የሚያስታውሱ ሰዎችን አነጋገሩ።"
የመጀመሪያዎቹን ፍንጮች ያገኙት የዚያን ጊዜ ነው። ኦም ፕራካሽ መንደሩን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ጎብኝቶ እንደነበረ እና በኡታር ፕራዴሽ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ አገኙ።
በሁለተኛው ጉዟቸው በኦም ፕራካሽ ስም የተመዘገበ ስልክ ቁጥር አገኙ። በመጨረሻም አዲሱን አድራሻውን ማግኘት ቻሉ።
ፖሊስ ለአንድ ሳምንት ያህል አካባቢውን ሲያጠና ቆይቶ መኖሪያ ቤቱን መለየት ቻለ።
"ትክክለኛውን ሰው ማግኘታችንን ማረጋገጥ ነበረብን" ይላል ፖሊስ።
"ሥራው በከፍተኛ ምስጢር ተካሄደ። አንድ መጥፎ እርምጃ ከወሰድን ለተጨማሪ 30 ዓመት ሊደበቅ ይችላል ብለን ተጨንቀናል" ሲልም አንድ የፖሊስ ባልደረባ አክሏል።
በቀጣይስ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ለረጅም ጊዜ በሽሽት ላይ ያለን ሰው መያዝ ለልዩ ግብረ ኃይሉ እንደ ድል ይታያል።
ወንጀሉ የተፈፀመው ከበርካታ አሥርት ዓመታት በፊት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የማስረጃው ጥራትም ትኩረት እንደሚሰጠው ይጠበቃል።
ይህንን ሁሉ አሰባስቦ ለፍርድ ማቅረብ ለፖሊስም ሆነ ለዐቃቤ ሕግ ቀላል ተግባር አይሆንም።
ኦም ፕራካሽ ከተያዘ በኋላ ራጅኩማሪ ልታገኘው ሞክራ እንደሆነ ስትጠየቅ "ፖሊስ እሱን ለመጠየቅ ከፈለግን የመታወቂያ ካርዶቻችንን ማስገባት እንዳለብን ነግሮናል። ይህን ማድረግ ግን አልፈልግም። ከዚህ ምን ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?" ስትል ትመልሳለች።












