የአሜሪካ ሚሳኤል አል-ዛዋሂሪን ከቤተሰቦቹ ነጥሎ እንዴት ሊገድል ቻለ?

በካቡል ሰዓት አቆጣጠር እሁድ ሐምሌ 24/2014 ዓ.ም. ንጋት ላይ የአል-ቃኢዳው መሪ ከጸሎት በኋላ እንደ ወትሮው ወደ በረንዳው ወጣ ይላል።
አይማን አል-ዛዋሂሪ ከጸሎት በኋላ ወደ በረንዳው ወጣ ብሎ መናፈስ የሚወደው ተግባር ነበር።
ግብጻዊው አል-ዛዋሂሪ እሁድ ጠዋት በረንዳ ላይ ወጥቶ የተመለከታት ጀምበር የመጨረሻው እንደምትሆን አልጠረጠረም።
አል-ዛዋሂሪ በካቡል ሰማይ ላይ የወጣችውን ፀሐይ ሲመለከት፤ እሳት የሚተፋው የአሜሪካ ድሮን ደግሞ ከላይ ከአናቱ ሆኖ ዒላማ ውስጥ አስገብቶታል።
ንጋት ከአንድ ሰዓት በፊት ከአሜሪካዋ ሰው አልባ አውሮፕላን የተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች አል-ዛዋሂሪ የነበረበትን በረንዳ ለይተው ዒላማ አደረጉ።
በዚህ ጥቃት የአል-ቃይዳ መሪ ብቻ ተለይቶ ተገደለ። አል-ዛዊሂሪ የተገደለበት በረንዳ መኖሪያ ቤት ውስጥ የነበሩት ባለቤቱ እና ሴት ልጁ ጭረት እንኳ አላጋጠማቸውም።
ብዙ ጊዜ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶ ዒላማቸውን እየሳቱ፤ አልያም የሚተፉት እሳት ለንጹሃን እየተረፈ ምዕራባውያን ሲተቹ ቆይተዋል።
በአል-ዛዋሂሪ ላይ የሆነው ግን ሌላ ነው። የተተኮሱት ሁለቱ ሚሳኤሎች ግለሰቡን ብቻ ነጥለው ገድለዋል።
ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ለዚህ ኦፕሬሽን ጥቅም ላይ የዋለው ሚሳኤል እና የአል-ዛዋሂሪ ዕለታዊ ተግባር ለኦፕሬሽኑ ስኬት እንዴት ምክንያት እንደሆነ እንመልከት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጨረር የሚመራ ዒላማ
ጥቃቱ ዒላማውን እንዲጠብቅ ያስቻለው ዋነኛው ጉዳይ፤ ጥቅም ላይ የዋለው የሚሳኤል አይነት ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአል-ቃኢዳውን መሪ ለመግደል 'ሄልፋየር' የተባለው ሚሳኤል ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
አሜሪካ ከአየር ወደ ምድር መተኮስ የሚችሉ ሚሳኤሎችን በፀረ-ሽብር ዒላማዎቿ ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለች ትገኛለች።
እአአ 2020 ኢራናዊውን ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ በባግዳድ እንዲሁም ትውልደ እንግሊዛዊው የኢስላሚክ ስቴትስ ጂሃዲስት ‘ጂሃዲ ጆን’ ለመግደል ይህን 'ሄልፋየር' ሚሳኤልን ጥቅም ላይ ሳታውል አትቀርም ይባላል።
ሄልፋየር ሚሳኤል ከድሮን ብቻ ሳይሆን፤ ከሄሊኮፕተር፣ ከወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ከመርከቦች ላይ ሊተኮስ ይችላል።
አሜሪካ ይህን ሚሳኤል በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ከምታውልባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፤ ሚሳኤሉ ዒላማውን የጠበቀ መሆኑ አንዱ ነው።
ለጥቃት የተሰማራን ድሮን የሚቆጣጠረው ሰው በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ተቀምጦ ድሮኑ ላይ በተገጠመ ካሜራ የጠላት መገኛን ይቃኛል።
መምታት የሚፈልገውን ዒላማውንም በጨረር ቴክኖሎጂ አማካኝነት ለመለየት ይችላል። ከዚያም ከድሮኑ የሚወነጨፈው ሚሳኤል የጨረሩን አቅጣጫ ተከትሎ ሄዶ ዒላማውን ይመታል።
ምንም እንኳ እስካሁን ማረጋገጫ ባይገኝም አሜሪካ በዛዋሂሪ ጥቃት አር9ኤክስ የተሰኘውን የሄልፋየር አዲስ ስሪት ሚሳኤል መጠቀሟ ተመላክቷል።

ይህ ሚሳኤል ፍንዳታ ከመፍጠር ይልቅ ዒላማ የሚያደርጋቸውን ስፍራ በኃይል ከመታ በኋላ በተገጠሙለት ስድስት ተሽከርካሪ ስለቶች በመቆራረጥ ይገድላል።
እአአ 2017 ላይ ሶሪያ ውስጥ ከዛዋሂሪ ምክትሎች አንዱ የነበረው አቡ ከህያረ አል-ማስሪም በዚሁ ሚሳኤል ነበር የተገደለው።
ከጥቃቱ በኋላ የተነሱ ፎቶግራፎች ሚሳኤሉ አል-ማስሪ ሲጓዝበት የነበረው ተሽከርካሪ ጣሪያ ቀዶ ከገባ በኋላ ተሳፋሪዎቹን በሙሉ በስለቱ ቆራርጦ መግደሉን አሳይተዋል።
ሚሳኤሉ ምንም አይነት ፍንዳታ ሳያስከትል፤ በተሽከርካሪው ላይም ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በውስጡ የነበሩትን ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ገድሏል።

የፎቶው ባለመብት, LOCAL CO-ORDINATION COMMITTEES
የዛዋሂሪ ‘በረንዳ ላይ የማዝወተር አባዜ’
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት በካቡል ጥቃቱን ከመሰንዘሩ በፊት የሰበሰባቸው መረጃዎች ይፋ እየሆኑ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሚሳኤል ጥቃቶቹን ከማዘዛቸው በፊት የዛዋሂሪን የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ተገንዝበን ነበር ብለዋል። ከዚህም መካከል አንዱ ዛዋሂሪ በረንዳውን ማዘውተሩ ነው።
ይህም የአሜሪካ ሰላዮች ዛዋሂሪን ለወራት ሲከታተሉት እንደቆዩ ማሳያ ነው ተብሎለታል።
የቀድሞ የሲአይኤ ባለሥልጣን ማርከ ፖለይሜሮፖሎስ አሜሪካ በዛዋሂሪ ዙሪያ የደኅንነት መረጃዎችን አፍጋኒስታን ካሉ ሰላዮቿ ሳታሰባስብ አትቀርም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌሎች ደግሞ የአሜሪካ ድሮኖች እና አውሮፕላኖች ዛዋሂሪ የተሸሸገበትን መኖሪያ ቤት ለሳምንታት ተመላልሰው ሲቃኙ ነበር ሲሉ ግምታቸውን ሰንዝረዋል። እነዚህ የቅኝት አውሮፕላኖች ታዲያ ከምድር ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም።
"ግለሰቡ በትክክል ተፈላጊው መሆኑ መረጋገጥ አለበት፤ እንዲሁም እርምጃው ሌሎችን አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ መፈፀም አለበት። . . . ይህ ትልቅ ትዕግስት ይጠይቃል" ይላሉ ፖለይሜሮፖሎስ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማርከ ፖለይሜሮፖሎስ አገራቸው አሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት በተለይ ከፍተኛ የአል-ቃኢዳ አመራሮችን በማደን አስደናቂ ተግባራትን አከናውናለች ይላሉ።
"በዚህ ላይ አስደናቂ ነን። ባለፉት 20 ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት ጥሩ መሻሻል አሳይቷል። አሜሪካውያን የተሻሉ ናቸው" ይላሉ የቀድሞ የሲአይኤ ከፍተኛ ኃላፊ ፖለይሜሮፖሎስ ለቢቢሲ ሲናገሩ።
ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ የአሜሪካ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ሁሌም ስኬታማ አይደሉም።
ከአንድ ዓመት በፊት አሜሪካ በካቡል የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቅርንጫፍ መሪን ለመግደል አስባ ሚሳኤል ተኩሳ 10 ንጹሃን ሰዎችን ገድላለች።
ፔንታጎን ይህን ክስተት "አስከፊ ስህተት" ሲል ጥፋቱን አምኖ ነበር።
አሁን ግን የአሜሪካ ሠራዊት እና የረቀቁት ደኅንነት ተቋማቷ ከ20 ዓመታት በላይ ሲያድኑት የነበረውን የአል ቃኢዳ መሪን አፍጋኒስታን ውስጥ በወሰዱት እርምጃ ማስወገዳቸውን ፕሬዝዳንት ባይደን አሳውቀዋል።
ከአስር ዓመት በፊት ደግሞ የቀድሞውን መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን ፓኪስታን ውስጥ ከአሁኑ በተለየ ዘመቻ መግደላቸው ይታወሳል። በወቅቱ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ።












