የ'ባልን እንዴት መግደል ይቻላል' ደራሲ ባለቤቷን በመግደል እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, Multnomah county Sheriff's office
“ባልን እንዴት መግደል ይቻላል” የተሰኘው ፅሁፍ ደራሲ ባለቤቷን በመግደል ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባታል።
በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት እስር የተበየነባት ደራሲዋ ናንሲ ክራምፕተን ብሮፊ፣ ባለቤቷን በጥይት ተኩሳ ገድላዋላች ተብሏል።
የ71 ዓመቷ ክራምፕተን ለ26 ዓመታት አብራው የኖረችውን ባለቤቷን የ1.5 ሚሊዮን ዶላር የህይወት መድን ዋስትና ክፍያን ለማግኘት ስትል እንደገደለችው የፍርድ ቤት ማስረጃ ያሳያል።
ክሮምፕተን በባሏ ግድያ ወንጀል በእስር ከመቀጣቷ በፊት ልብ አንጠልጣይ የሆኑ ድርሰቶችን አበርክታለች። ከእነዚህም መካከል “ዘ ሮንግ ሃዝባንድ” እና “ዘ ሮንግ ላቨር” ይገኙበታል።
ባለቤቷ ዳንኤል ብሮፊ በኦሪገን የምግብ አሰራር ተቋም ምግብ አዘጋጅ እና የተከበረ መምህር ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ነበር በሚሰራበት ተቋም ማዕድ ቤት ውስጥ በሁለት ጊዜ በጥይት ተመትቶ ሞቶ የተገኘው።
ባለቤቱ ባለፈው ወር ነበር በግድያው ወንጀል የተከሰሰችው።
ክራምተን ብሮፊ “ባልን እንዴት መግደል ይቻላል” በሚለው መጽሐፏ ምክንያት የፍርዱ ሂደት የበርካቶችን ትኩረት ስቧል።
“ስለ ግድያ የማውቀው ነገር እያንዳንዳችን በበቂ ሁኔታ ስንገፋ በውስጣችን መንፈሱ እንዳለን ነው” በማለት በአሁኑ ወቅት ባጠፋችው ፅሁፍ ላይ አስፍራ ነበር።
ደራሲዋ “ሰዎችን ከመግደል እንዲሞቱ መመኘት ቀላል ነው” በማለትም ጠመንጃ፣ ጩቤ፣ መርዝ እንዲሁም ለቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ መክፈልን ጨምሮ የተለያዩ መግደያ መንገዶችን አስፍራለች።
አክላም “ግድያው ነፃ የሚያወጣኝ ከሆነ በእስር ቤት ውስጥ ምንም ጊዜ ማሳለፍ አልፈልግም” ስትል አክላለች።
አንደኛዋ ዳኛ ይህ ከዓመታት በፊት የተጻፈው ፅሁፍ በፍርድ ሂደቱ ላይ ማስረጃ አይሆንም በማለት ውድቅ አድርገውታል።
በተማሪም ዐቃብያነ ሕጎቹም ለክሳቸው ፅሁፉን አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም።
ክራምፕተን ብሮፊ የትዳር አጋሯን የመግደል ተነሳሽነት፣ ምክንያት እና መንገዱ ነበራት ሲሉ በተሳካ ሁኔታ ተከራክረዋል።
ጥንዶቹ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እሷም ከሞቱ ከፍተኛ የኢንሹራንስ ክፍያን ለማትረፍ ገድላዋለች ብለዋል።












