በርካታ ልጆች ከመጠን ካለፈ ውፍረት ጋር በተገናኘ በስኳር በሽታ እየተያዙ ነው

ከመጠን በላይ የወፈረ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩናይትድ ኪንግደም በሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የጤና ባለሙያዎችን እንዳሳሰባቸው አንድ የበጎ ድርጅት አስጠንቅቋል።

ህፃናቱ የስኳር ህመም ተጠቂ ያደረጋቸው ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንደሆነና ይህም ከኑሮ ውድነት ጋር በተገናኘ ያለው ደካማ የአመጋገብ ስርዓት መሆኑንም የዩናይትድ ኪንግደም የስኳር ህመምተኞች ማህበር አስታውቋል።

በተለይም የኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ መጠን ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ጤናማ የሚባሉ የምግብ አይነቶች በመወደዳቸው የበለጠ ሁኔታውን ሊያባብሰው እንደሚችልም ተገልጿል።

በተለይም የኑሮ ዝቅተኛነት በሚስተዋልባቸው የእንግሊዝና ዌልስ አካባቢዎች ጫናው ከፍተኛ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም ከተጠቁ አስሩ ወስጥ አራቱ የኑሮ ዝቅተኛነት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ነው።

ይህም አሃዝ የኑሮ ከፍተኛነት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ከ19ኙ አንዱ እንደሚጠቃ ያሳያል።

በእንግሊዝ ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህፃናት መካከል ከአስሩ አንዱ ከመጠን ያለፈ ውፍረት አለው።

ከመጠን በላይ ውፍረት በሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። በተጨማሪም ከዘር እንዲሁም ከቤተሰብ ታሪክ ጋር በተገናኘ በህመሙ የመጠቃት እድል አለ።

የስኳር በሽታ ምንድነው?

- የስኳር በሽታ ሰዎች በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ስኳር (ግሉኮስ) እንዲኖራቸው ያደርጋል።

- በአንደኛው አይነት ስኳር የተጠቁ ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ ኢንሱሊን አያመነጩም።

- በሁለተኛው ዓይነት ስኳር ህመም የተጠቁ ደግሞ የማይጠቅም ወይም በቂ ያልሆነ ኢንሱሊን ሰውነታቸው ያመነጫል።

በእንግሊዝ እና በዌልስ የህጻናት የስኳር ህመም ክፍል ውስጥ ህክምና ከሚያገኙ ህፃናት መካከል በሁለተኛው የስኳር ህመም የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ 50 በመቶ በላይ መጨመርን ያሳያል ።