ለዘመናት ታዋቂነቱና ተወዳጅነቱ ያልደበዘዘው የሕንድ የፊልም ፈርጥ - ሻሩክ ካን

 በአለም ላይ ስመ ጥር የሆነው የፊልም ተዋናይ ሻሩክ ካን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቋንቋና ባህል ሳይወስነው ከአገሩ ሕንድ ተሻግሮ በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆነው የፊልም ተዋናይ ሻሩክ ካን በሕንድ ሲኒማ ሦስት አስርት ዓመታት ያስቆጠረበትን መታሰቢያ ባለፈው ወር አክብሯል።

የቦሊውድ ተዋናዩ ለሦስት አስርት ዓመታት ስሙ ሳይደበዝዝ በተወዳጅነት መዝለቁን በተመለከተ መጽሐፍ የጻፈው ሽራያና ባታቻሪያ፣ አሁንም ሻሩክ ከዓለማችን ታላላቅ የፊልም ዝነኞች አንዱ የሆነበትን ምክንያት ያስረዳል።

የ56 ዓመቱ ሻሩክ በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ በታዋቂነቱና በተወዳጅነት ይህን ያህል ረጅም ዕድሜ ቆየ የሚለውን ለማስረዳት ምሁራዊ ምክንያቶችን ማቅረብ ጉዳዩን ማቅለል ይሆንብናል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን ነዋሪዎች ተዋናዩን በማያሻማ ሁኔታ ይወዱታል። ሻሩክ በሕዝብ ዘንድ ያተረፈው ተወዳጅነትና አድናቆት አንዳንድ ጊዜ በሚያስፈራ መልኩ አምልኮ የሚመስልበት ሁኔታም አለ።

ሻሩክ ለምን “ተወደደ” እንዲሁም “ተመለከ?” ብለን ብንጠይቅ ልክ እንደ ፊልሞቹ፣ መልሱ የፍቅር እና ስሜት ነው የሚሆነው።

ሻሩክ ሁልጊዜም ቢሆን በፊልሞቹ ሕንድ እንዲሁም ደቡብ እስያን ሊሆኑ የሚችሉትን መልካም ነገሮችን ይገልጻል እንዲሁም ይወክላል። ተዋናዩ የበለጸገች ሕንድን፣ ሰብዓዊነትን እንዲሁም ፍቅርን በማሳየት በርካቶችን በተለየ ስሜት እንዲሞሉ ያደርጋቸዋል።

በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕንዳውያንም የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ታሪክ መወከያም ሆኖ ቆይቷል።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ሻሩክን በፊልሞቹ በስክሪኖቻችን መመልከት ስንጀምር ሕንድም በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ መድረክ ማንሰራራትና ወደፊት መምጣት ጀመረች። የሻሩክ ታዋቂነት ሲጨምር በተመሳሳይ የሕንድም ምጣኔ ሀብት ተመነደገ።

ሕንድ ያደረገቻቸው ተከታታይ የገበያ ማሻሻያዎች አካል የሆነውን የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ከፍታለች።

የቴሌኮም ዘርፉም በዚህ መንገድ ክፍት መሆን አዳዲስ የሚዲያ አውታሮች በሕንድ ውስጥ እንዲጀመሩ አስችሏቸዋል። እነዚህ ሚዲያዎች የሻሩክ ፊልሞች፣ ዘፈኖች እና ቃለ መጠይቆች ከእርሱ በፊት ከነበሩ ታዋቂ ሰዎች በበለጠ ሕዝቡ ዘንድ እንዲደርሱ ዕድል ፈጥሯል።

ሕንድ ኢኮኖሚዋን የበለጠ ነፃ ስታደርግ አዳዲስ የለስላሳ መጠጥ ምርቶች፣ መኪኖች ገበያውን ተቀላቀሉ ሻሩክንም የምርታቸው አምባሳደር ማድረግ ጀመሩ።

መካከለኛ ኑሮ ከነበራቸው ቤተሰብ የተገኘው ሻሩክ በሕንድ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ዘመድ ሳይኖረው ወይም የተለየ ግንኙነት ሳይፈጥር ለዓለም አቀፍ ዝና መብቃቱ “የኒዮ ሊበራል ህልም” ስኬት ማሳያ ተደርጎም ተቆጠረ።

በተለይም የቀኝ አክራሪ ሃይማኖተኞች ማንሰራራት በጀመሩበት ጊዜ፣ ሻሩክ በርካታ ሕንዶች ሊጨብጡት የሚሞክሩት የተራማጅነት ምሳሌ ሆነ።

ሻሩክ ከአድናቂዎቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክራሪ የሂንዱ ብሔርተኛ የሚባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግሥት የሕንድ ሙስሊሞችን አግልሏል በሚል በሰፊው የሚወቀስ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ አለመቻቻል በከፍተኛ ሁኔታ በአገሪቱ እየጨመረ መምጣቱን ተቺዎች ይናገራሉ።

የሻሩክ ልጅ አሪያን ካን ባለፈው ዓመት ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውሎ ነጻ ቢወጣም በርካታ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ሙስሊሞችን ኢላማ ያደረገ ነው በሚል እስሩ ተተችቷል።

ሻሩክ በሕንድ ብዝሃነት እንዲሰፍን በሳል አስተያየቶችን ሲሰጥ የሚሰማ ሲሆን ከሌሎች ተዋናዮችም በበለጠ የሙስሊም ገጸ ባህርይን ወክሎ ተጫውቷል።

ነገር ግን ወዳጆቹና አድናቂዎቹ በሃይማኖታዊ ማንነቱ (በእስልምና እምነቱ) ዓይን ሊያዩት ፈቃደኛ አይደሉም። በምትኩ ሻሩክን የሚያዩት ብልህና በሳል፣ ስኬታማ እንዲሁም ጉብልነቱን ነው የሚያጎሉት።

ሻሩክ እምነቱ ሙስሊም ቢሆንም ባለቤቱ ሂንዱ ናት፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ አክራሪው የሂንዱ ቀኝ ክንፍ ኢላማ አድርጎታል፣ ይህንንም አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ ያደረግኩላት የሻሩክ ወጣት አድናቂ “ሻሩክ ሃይማኖተኛ አይደለም እንዲሁም በጣም ውብ ነው” ብላለች።

ከሁሉም በላይ ተዋናዩ ሁላችን እንደ ሰው ልጅ የምንጋራውን ደካማነትን ወይም ተሰባሪነትን ያሳያል።

ሻሩክ ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ አፍቃሪ፣ አሳዛኝ ጀግና፣ አሳዛኝ ባል፣ አሳዛኝ ሙስሊም እንዲሁም አልፎ ተርፎም አሳዛኝ ጠላት ገጸ ባህሪያትን ይጫወታል። ወክሎ የሚጫወታቸው ገጸ ባህሪያት ከራሳቸው እና በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀለል ያለ አይደለም።

ገጸ ባህሪያቱ የሚታይባቸው አለመረጋጋት ለሦስት አስርት ዓመታት በዘለቀው የፊልም ህይወቱ እየተሻሻለም ታይቷል።

ብዙውን ጊዜ በስሜታዊነት የተጎዱ ናቸው፣ ሙሉ በሙሉ የመፈቀር ስሜት የማይሰማቸው እንዲሁም ፍቅርን የማግኘት ፍላጎታቸውን መተው የማይፈልጉ ናቸው - ገጸ ባህሪያቱ።

ሻሩክ በደቡብ እስያ የፍቅር ልዕለ ኃያል ተደርጎ ነው የሚታየው። ፊልሞቹ ሁሉም አፍቃሪዎች ለሟሟላት እንደ መስፈርት የሚያዩዋቸውና የፍቅርም ከፍተኛ ደረጃ መለኪያ ናቸው ይባላሉ።

መረጃ እንደሚያሳየው ገፀ ባህሪያቱ ሌሎች የቦሊውድ ወንድ ፊልም ተዋናዮች ከሚጫወቷቸው ገጸ ባህሪያት በበለጠ ከሴቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ነው።

ነገር ግን የሻሩክ ገጸ ባህሪያት የሚፈልጉት የተለመደውን የሴትን ፍቅር ብቻ ሳይሆን የአባቶችን፣ የጓደኞቻቸውን እና የአገራቸውን ሰዎች ፍቅር እና ይሁንታ አጥብቀው ይፈልጋሉ።

ሻህ ሩክ ካን ድልዋሌ ዱልሃኒያ ለጄንጌ በተሰኘው ፊልሙ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሚጫወታቸው ወንድ ገጸ ባህሪያት ጥልቅ ስሜት የሚሰማቸው፣ ለሌላው ዕይታ ያለማቋረጥ የሚጋለጡና በርካታ ጊዜ ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱ ናቸው።

የፊልም ፀሐፊዎች ሻሩክ እንዴት ከዓለማችን ተዋናዮች በተሻለ ማልቀስ እንደሚችል አብዛኛውን ጊዜ አስተያየት ሲሰጡም ይደመጣሉ።

ማልቀሱም ሆነ በእንባ የተሞሉ ዐይኖቹና ሆደ ቡቡነቱን ማሳየቱ ስፍር ቁጥር በሌላቸው አድናቂዎች እንዲወደድ አድርገውታል።

ከፊልሙ ባሻገር በቴሌቪዥን የሚያደርጋቸው ቃለ መጠይቆቹ እና ሕዝባዊ ንግግሮቹ ቀልዱን እና ትህትናውን አጉልተውታል።

ከፊልሞቹ ይልቅ የሻሩክን ቃለ መጠይቅ አሳድደው የሚያደምጡ በርካታ አድናቂዎች አሉት። እነዚህ የሚዲያ ንግግሮቹ ተዋናዩ እስከ ዛሬ ያለውን ምርጥ ትወናም አመላካች ናቸው - ባለልበ ሙሉው የመካከለኛው መደብ የተዋናዮች ኮከብ።

ሻሩክ ለብዙዎች የማይጎረብጥ ትንሽ እብሪተኛነትን እንዲሁም ጨዋ ሕዝባዊ ስብዕናን ፈጥሯል።

ከፍተኛ አጫሽ፣ ድፍረት የተሞላ፣ ራሱን የሚያውቅና አስቂኝ የሆነው ሻሩክ በጭራሽ አሰልቺ አይደለም።

ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እንዲሁም በችግር የተሞላ ጓደኝነትን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ጥሩ ምክር ከመስጠት ጀምሮ፣ በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ስለ እርጅና እና ስለራሱ የወሲብ ሕይወት ወይም አስቂኝ ቀልዶችን በማውራት ማንነቶቹን ለመግለጥ ችግር እንደሌለበትም አስመስክሯል።

ስለራሱ እና ስለዓለም በሚያቀርባቸው ጥቅሶች እና ቀልዶች ውስጥ ሁልጊዜ ጠንክሮ የሚሠራ፣ ለሙያው የሚጠበብ እና በራሱ ላይ መሳቅ የሚደሰት ሰው መሆኑን ደጋግሞ ያሳያል።

እርግጠኛ ባልሆነችው እና ፈታኝ በሆነችው ዓለም ውስጥ፣ የሻሩክ ማንነትም ሆነ ፊልሞቹ የመደነቂያ፣ የማምለጫ እና የመዝናኛ ምንጭ ሆነዋል።

ተዋናዩ በአውሮፓውያኑ 2023 የሚያወጣቸው ሦስት ትልልቅ ፊልሞች አሉት። አድናቂዎቹ በጉጉት እና በደስታ እየጠበቁት ቢሆንም፣ ስኬታማ ሙስሊም የቦሊውድ ተዋናዮችን ፊልም እንዲታገዱ አድማ የሚያደርጉ የቀኝ ክንፍ የሂንዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን በጥንቃቄ ነው የሚመለከቷቸው።

ፖለቲካችን በጣም ከፋፋይ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ሻሩክ ብዙዎቻችንን በፈገግታ እና በታሪኮች እንዴት አንድ እንደሚያደርገን በማሳየት ያለውን ኃይልን አስመስክሯል።

ለሚቀጥሉት 30 ዓመታትም የዚህን ፈርጥ ተአምራት ለማየት ሕንዶችና በመላው ዓለም ያሉ አድናቂዎቹ ይመኛሉ። በተለይ ሕንዶች የተሰበረውን ባህላቸውን ለመጠገን የእሱን ቀልዶች እና አቃፊነቱን በእጅጉ ይፈልጉታል።