የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ ሞት ያወጁበት ሳልማን ሩሽዲ ማነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳልማን ሩሽዲ በዓለም ዙሪያ ዝነኛ ባደረገው ሙያ ውስጥ ለአምስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ቆይቷል። በዚህም ዝና ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ጠላቶች ተነስተውበታል።
ለዚህ ነው “ቀንህን ጠብቅ እንገድልሃለን” የሚሉ ዛቻዎች በሰውዬው ሕይወት ውስጥ አዲስ ያልሆኑት።
ደራሲው ባለፈው አርብ ኒው ዮርክ ውስጥ በተሰነዘረበት ጥቃት ሆስፒታል ይገኛል። የጥቃቱ አላማ ምን እንደሆነ ፖሊስ እስካሁን ባይደርስበትም ከሙያው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገምቷል። ለመሆኑ ሳልማን ሩሽዲ ማነው?
ሩሽዲ ደራሲ ነው፤ በብሪታኒያ እጅግ ስኬታማ እና ታዋቂ ከሆኑ የምንጊዜም ፀሐፊያን ጎን የሚሰለፍ ‘ሚድናይትስ ችልድረን’ በተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፉ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1981 በብሪታኒያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የቡከር ሽልማት አግኝቶበታል።
የሳልማን አራተኛ መጽሐፉ ግን ሽልማት ሳይሆን ውዝግቦችን ይዞ መጣ። ‘ዘ ሳታኒክ ቨርሰስ’ የተሰኘው እና በአውሮፓውያኑ 1988 የታተመው ድርሰቱ ከሥራዎቹ ሁሉ እጅግ አወዛጋቢው ነው። ውዝግብ ብቻ ሳይሆን አይቶት በማያውቀው ደረጃ በዓለም ዙሪያ ተቃውሞዎችን አስነስቶበታል።
በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮችን የመጽሐፉ ይዘት አስቆጥቷቸዋል። በመጽሐፉ ላይ ነብዩ መሐመድ የተገለጹበት መንገድ እምነታችንን የሚዘልፍ ነው በሚል ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።
ይህ መጽሐፍ ያመጣበት መዘዝ ብዙ ነው። የ75 ዓመቱ ደራሲ ሩሽዲ የሚደርስበት ቁጥር ስፍር የሌለው ማስፈራሪያ እና የግድያ ዛቻ ራሱን እንዲደብቅ እና በብሪታኒያ ፖሊስ ጥበቃ ስር እንዲሆን አስገድዶታል።
መጽሐፉ ከግለሰቡ አልፎ በዩናይትድ ኪንግደም እና በኢራን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ሰበብ ሆኗል። ኢራን በመጽሐፉ ላይ ተቃውሞዋን ለመግለጽ ከዩኬ ጋር ያላትን ግንኙነት ወዲያውኑ ነበር ያቋረጠችው።
ያም ብቻ ሳይሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ1989 በኢራን መንግሥት ውስጥ ቁጥር አንዱን ስፍራ የሚይዙት የሃይማኖት መሪ አያቶላህ ኾሚኒ ፀሐፊው እንዲገደል የሚያዝ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ ወይም ፈትዋ አስተላለፉ።
በተቃራኒው ምዕራቡ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ፀሐፊያን እና ልሂቃን ይህንን ትዕዛዝ እና መሰል በኃይል የተሞሉ የተቃውሞ ጥሪዎች፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተቃጡ ናቸው በሚል በጽኑ አውግዘውታል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ከሕንድ ወደ ብሪታኒያ
ሳልማን ሩሽዲ ህንድ ነጻ ልትወጣ ሁለት ወር ሲቀራት ነበር ቦምቤይ ከተማ ውስጥ የተወለደው። ያቺ ከተማ አሁን ሙንባይ በመባል ትታወቃለች።
ደራሲው በ14 ዓመቱ ወደ እንግሊዝ ተጓዘ። ቆይቶም በኬምብሪጅ ከሚገኝ ኮሌጅ በሕግ ትምህርት ተመረቀ።
ከጊዜ በኋላም የብሪታኒያ ዜግነት ያገኘው ደራሲው የእስልምና እምነቱን ተወ።
ድርሰቱን በሚጽፍባቸው ጊዜያት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ተዋናይ እና የማስታወቂያ ባለሙያ ሆኖ ሰርቷል።
‘ግሪመስ’ የተሰኘው የመጀመሪያው ድርሰቱ ትልቅ ስኬትን ባያገኝለትም፣ ሃያሲያን ግን ደራሲው ከፍ ያለ ተሰጥኦ ያለው እንደሆነ እንዲናገሩለት አድርጓል።
ሳልማን በብሪታኒያ እጅግ ውጤታማ እና ታዋቂ ከሆኑ የምንጊዜም ፀሐፊያን ጎን ያሰለፈውን ሽልማት ያስገኘለትን ‘ሚድናይትስ ችልድረን’ የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፉን ለመጻፍ አምስት ዓመታት ፈጅቶበታል።
‘ሚድናይትስ ችልድረን’ የሚያተኩረው በሕንድ ላይ ሲሆን በ1983 የታተመው ‘ሼም’ የተሰኘው መጽሐፉ ደግሞ ፓኪስታን ላይ ያነጣጠረ ነበር።
ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ ‘ዘ ጃጓዋር ስማይል’ የሚል ርዕስ የሰጠው እና በኒካራጓ ጉዞው ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ አሳትሟል።
በፈረንጆቹ መስከረም 1988 ብዙ የግድያ ዛቻ ያስተናገደበትን 4ኛ ሥራው ‘ዘ ሳታኒክ ቨርሰስ’ ለንባብ በቃ። የመጽሐፉ ይዘት እምነታችንን ዘልፏል ባሉት ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መጽሐፉ ያስከተለበት ተቃውሞ
ይህን መጽሐፍ በመጀመሪያ ያገደችው የትውልድ አገሩ ሕንድ ስትሆን ፓኪስታ ተከትላለች። በመቀጠል በርካታ የሙስሊም አገራት እና ደቡብ አፍሪካ መጽሐፍ አግደውታል።
በሌላ በኩል መጽሐፉ የተለያዩ ታላላቅ ሽልማቶች ጎርፈውለታል። ይህ ሲሆን መጽሐፉ ላይ የሚቀርበው ትችት እየጠነከረ ሄዶ ከሁለት ወር በኋላ የአደባባይ ተቃውሞን አስከትሏል።
የተወሰኑ ሙስሊሞች የመጽሐፉን ይዘት እስልምና ላይ የተሰነዘረ ዘለፋ እንደሆነ ያምናሉ። በመጽሐፉ ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል የነብዩ መሐመድ ሁለት ሚስቶች ስምን ደራሲው የተጠቀመበት መንገድን አምርረው ይቃወማሉ።
የመጽሐፉ ርዕስ በሰይጣን የመነጩ ናቸው በሚል በነብዩ መሐመድ ከቁርአን እንዲወጡ ተደርገዋል ተብለው ከሚታመኑ ጥቅሶች ጋር የተያያዘ ነው።
በፈረንጆቹ የካቲት 1989 በዩናይትድ ኪንግደም ብራድፎርድ ውስጥም በተደረገ ተቃውሞ፣ ሙስሊሞች የመጽሐፉን ቅጂ በእሳት አቃጥለዋል። ሆኖም ግን ሳልማን ሩሽዲ የሚቀርብበትን ክስ አይቀበልም።
በደራሲው የትውልድ ከተማ ከመጽሐፉ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሁከት 12 ሰዎች ሞተዋል። በቴህራን የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲም የድንጋይ ናዳ ወርዶበታ። ደራሲውን ለገደለም ኢራን 3 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት እንደምትሰጥ ቃል ገብታም ነበር።
ይህ ሁሉ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የተወሰኑ የእስልምና መሪዎች ተቃውሞው ልኩን አልፏል በሚል የተቹ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ ‘የይገደል’ ትዕዛዝ ትክክል ነው ብለው ይከራከራሉ።
አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባውያን ደግሞ የሞት ትዕዛዙን ይኮንኑታል፤ያወግዙታል።
ሳልማን ሩሽዲ እና ባለቤቱ ያልተቋረጠ የፖሊስ ጥበቃ ያላቸው ሲሆን፣ በመጽሐፉ ምክንያት በሙስሊሞች መካከል ለተፈጠረው ሐዘን በጥልቅ እንደሚጸጸት ገልጿል። ያም ሆኖ ግን የኢራኑ አያቶላ ኾሚኒ ያወጁበትን ሞት አጽንተውታል።
በለደን የሚገኘው የመጽሐፉ አሳታሚ ድርጅት በኒው ዮርክ ቅርንጫፉ በኩል ተከታታይ የግድያ ዛቻዎች በየጊዜው ይደርሱታል።
ያም ሆኖ መጽሐፉ ከፍ ያለ ሽያጭ ነበረው። ደራሲው ላይ የሚደርሰውን ጽንፈኝነት ያዘለ ውግዘት በመቃወም በርካታ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮቻቸውን ከቴህራን በጊዜያዊነት እስከመጥራት ደርሰዋል።
የዚህ መጽሐፍ ‘መዘዝ’ ከደራሲውም ያለፈ ነው። ይህንን መጽሐፍ ወደ ጃፓንኛ የተረጎመው ግለሰብ በቶኪዮ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተገድሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለሌሎች የተረፈው የመጽሐፉ ዳፋ
ረዳት ፕሮፌሰር የነበረው እና ሂቶሺ ኢጋራሺ የተባለው ተርጓሚው ታስቡካ በሚገኘው ዩኒቨርስቲ በተደጋጋሚ በስለት ከተወጋ በኋላ ከቢሮ አቅራቢያ በሚገኝ መንገድ ተጥሎ ተገኝቷል። የገዳዩ ማንነት እስካሁን አልተደረሰበትም።
ይህ ከመሆኑ አንድ ወር አስቀድሞ ደግሞ መጽሐፉን ወደ ጣሊያንኛ የመለሰው ኢቶሬ ካፕሪዮሎ ሚላን በሚገኘው አፓርታማው ውስጥ በስለት ቢወጋም ተርፏል።
‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ን ወደ ኖርዌ ቋንቋ የተረጎመው ዊሊያም ናይጋርድ እንደ አውሮፓውያኑ በ1993 ኦስሎ ከሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ የተተኮሰበት ቢሆንም ከሞት ተርፏል።
ሩሽዲ ከዚያም በኋላ የህጻናትን መጽሐፍ ጨምሮ በርካታ ጽሁፎችን አሳትሟል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2003 ወደ መድረክ ሥራ በተቀየረው ‘ሚድናይትስ ችልድረን’ መጽሐፉ ላይ ተሳትፏል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥም በርካታ መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል።
አወዛጋቢው ደራሲ አራት ጊዜ ትዳር የመሰረት ሲሆን ሁለት ልጆች አሉት። ሩሽዲ በአሁኑ ጊዜ ኑሮውን ያደረገው በአሜሪካ አገር ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ 2007 ለሥነ ጽሑፍ አበርክቶው ከእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤት ሽልማት ተበርክቶለታል።
በ2012 ደግሞ ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ መጽሐፍ ጋር በተያያዘ ስላለው ትውስታ ጽፏል።
በአውሮፓውያኑ 1998 ለተላለፈበት የሞት ትዕዛዝ የኢራን መንግሥት ድጋፉን ያቋረጠ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሻለ የነጻነት ሁኔታን አግኝቶ እንደነበር ይነገራል።
ሆኖም የግድያ ዛቻው ግን እንደቀጠለ ነበር። የአሁኑ የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ በደራሲው ላይ የተላለፈው ፈትዋ ወይም የሞት ትዕዛዝን በተመለከተ በአንድ ወቅት ሲናገሩ “ኢላማውን ሳያገኝ እንደማያርፍ ጥይት ነው” ብለው ነበር።
አወዛጋቢው መጽሐፍ ከታተመ ከ20 ዓመታት በኋላ ደራሲው በኒው ዮርክ አንድ መድረክ ላይ ንግግር በሚያደርግበት ወቅት አርብ ሐምሌ 06/2014 ዓ.ም. በስለት ተወግቷል።
ይህ ጥቃት ከኒው ጀርሲ ግዛት የመጣ ነው በተባለው የ24 ዓመቱ ወጣት ሐዲ ማታር መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን፣ የ75 ዓመቱ ሩሽዲ ለሕይወቱ በሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።
ፖሊስ ጥቃቱ ለዓመታት ሲዛትበት ከነበረው ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገና አላረጋገጠም።












