አና ፍራንክን ለናዚ አሳልፎ የሰጣትን ሰው ማንነት ያጋለጠው መጽሐፍ እየተተቸ ነው

አና ፍራክንክ

የፎቶው ባለመብት, ANN FRANK MUSEUM

የደች አሳታሚ በቅርብ ባሳተመው መጽሐፍ ዙርያ ይቅርታ ጠየቀ፡፡

መጽሐፉ ለዓመታት እንቆቅልሽ ሆኖ የነበረውን አና ፍራንክን እና ቤተሰቧን ለናዚዎች አሳልፎ የሰጠውን ከሃዲ ፍለጋ የተደረገ ምርመራን የሚዳስስ ነበር፡፡

የዚህ መጽሐፍ ድምዳሜ አና ፍራንክንና ቤተሰቧን የተደበቁበትን ጠቁሞ ለናዚዎች አሳልፎ የሰጣቸው ሰው አርኖልድ ቫን ዴን በርግህ የሚባል አይሁድ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

ይህ ግኝት ባለፉት ሳምንታት የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡

ሆኖም በርካታ ሰዎች መጽሐፉ የኅትመት ብርሃን ማየቱን ተከትሎ ትችት እያዘነቡበት ይገኛሉ፡፡

የአይሁድ ዝርያ የነበራት ጀርመናዊቷ አና ፍራንክ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ግዞትን በመፍራት አምስተርዳም በሚገኝ አንድ መሥሪያ ቤት በሚገኝ ቆጥ ላይ ተደብቃ ወራትን አሳልፋ ነበር፡፡

የጦርነቱን መጠናቀቅ ተከትሎ በዚህ አስጨናቂ ወቅት የጻፈቻቸው የግል ማስታወሻዎች ‹የአና ማስታወሻዎች› በሚል በዓለም ዙርያ ታትመው በበርካታ ቋንቋዎች በሚሊዮን ቅጂዎች ተነበውላታል፡፡

በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በኦሽዊትዝና ሌሎች የግዞት ካምፖች ውስጥ የአና ቤተሰብን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዶች ታጉረው እንዲሞቱ መደረጉን ታሪክ ሰንዶታል፡፡

በዚህ ረገድ የአና ማስታወሻ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶች በምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ እንደኖሩ ቱባ መረጃን የፈነጠቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ሆኖም ለዓመታት እንቆቅልሽ ሆኖ የነበረው ጉዳይ አናን፣ የአናን ታላቅ እህት፣ እናትና አባት እንዲሁም ሌሎች ጥቂት የቤተሰቦቿን አባላት ከተደበቁበት ምሥጢራዊ ስፍራ የናዚን ፖሊስን መርቶ የጠቆመው ሰው ማን ነው የሚለው ነበር፡፡

በዚህ ጉዳይ ላለፉት ዐሥርታት በርካታ መላምቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

አሁን ይቅርታ ጠየቀ በተባለው የደች አሳታሚ በኩል የታተመ አዲስ መጽሐፍ የዚህን ሰው ማንነት አጋልጦ ነበር፡፡

የምርመራ ቡድኑ የቀድሞ የኤፍቢአይ አባል የነበረ መርማሪን፣ አንድ የታሪክ ተመራማሪንና ሌሎች ልምድ ያላቸው የምርመራ ባለሙያዎችን የያዘ ሲሆን በዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎች የታገዘ ሰፊ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡

የምርመራ ቡድኑ ለዚህ ድምዳሜ ያበቃቸውን ነጥቦችንም በመጽሐፉ በዝርዝር ይዟል፡፡

ስድስት ዓመታት የፈጀው ይህ የምርመራ ሂደትና ድምዳሜ ቫን ደን በርግ የተባለ አይሁድ የራሱን ቤተሰብ ለማዳን ሲል እነ አና ያሉበትን በመጠቆም ለሞት አብቅቷቸዋል ይላል፡፡

ሆኖም መጽሐፉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተብጠለጠለ ይገኛል፡፡

ቢቢሲ ይህን አምቦ አንተንስ የተባለውን የደች አሳታሚ ለማነጋገር ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡

አሳታሚው የአንባቢዎችን ትችት ተከትሎ ለካናዳዊው የመጽሐፉ ደራሲ በጻፈው ማስታወሻ መጽሐፉ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን አምኖ ድጋሚ ኅትመቱን እንደሚያዘገይ አሳውቋል፡፡

‹‹ በዚህ መጽሐፍ ዙርያ ቅሬታ የገባቸውን አንባቢዎች ሁሉ ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን›› ሲልም አሳታሚው ለደች የዜና ማሰራጫ ተናግሯል፡፡

በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ አዳጊ አና ፍራንክና ሰባት ቤተሰቦቿ ከአንድ የመሥሪያ ቦታ ከነበረ ፎቅ ቤት፣ ቆጥ ላይ ለወራት ተደብቀው ሲኖሩ ነበር፡፡

ሆኖም እነሱ ይኖሩበት የነበረውን ቆጥ የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡

ከእለታት በአንድ ቀን የናዚ ወታደሮች እነ አና የተደበቁበትን ይደርሱበታል፡፡

ከዚህ መሸሸጊያ ቤት እንዴት ሊገኙ ቻሉ? ማንስ አጋልጦ ሰጣቸው? የሚለው ግን አሁንም እንቆቅልሽ መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡

አና ፍራንክ በወቅቱ በናዚዎች ግዞት ከተወሰደች በኋላ በርገን በልሰን በተሰኘ የጀርመን የግዞት ማጎርያ ውስጥ ሞታለች፡፡

እናቷና ታላቅ እህቷም አልተረፉም፡፡

እንደ ፈረንጆቹ በ1947 ማስታወሻዎቿ ለመጀመርያ ጊዜ የታተሙ ሲሆን እስከዛሬም በሚሊዮን ቅጂዎች እንደተሸጡ አሉ፡፡

የአና ማስታወሻ አማርኛን ጨምሮ በ70 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡