በማህተማ ጋንዲ ገዳይ ዙሪያ ያለው ምስጢር

የፎቶው ባለመብት, Mondadori via Getty Images
ጥር 30/1948 ምሽት ማህተማ ጋንዲ ወይም በሙሉ ስማቸው ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ በሕንድ መዲና ደልሂ ከፀሎት ሲወጡ በሽጉጥ ተገደሉ።
ከቅርብ ርቀት ሽጉጥ ተኩሶ የገደላቸውም ናታሁራም ቪናያክ ጎድሴ ይባላል።
የ38 ዓመቱ ገዳይ ሂንዱ ማሃሳብሃ ተብሎ የሚጠራው የአክራሪው ቀኝ ክንፍ ፓርቲ አባል ነው።
ጋንዲ ሙስሊሞችን ይደግፋሉ እንዲሁም ለፓኪስታን ገር የሆነ ልብ በማሳየት ሂንዲዎችን ክደዋልም ሲል ከሷቸዋል።
ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ በአንድ ግዛት ስር የነበሩት ሕንድና ፓኪስታን በሚል ለሁለት በመከፈል በ1947 ለተፈጠረው ደም መፋሰስም ጋንዲን ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
ማህተማ ጋንዲ ከተገደሉ ከዓመት በኋላ ጎድሴ የሞት ቅጣት ተፈረደበት። ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ካረጋገጠ በኋላ በኅዳር 1949 ዓ.ም ግለሰቡ በስቅላት ተቀጣ።
በግድያው ተባባሪ የነበረው ናራያን አፕቴም በሞት ሲቀጣ፣ ሌሎች እጃቸው አለበት የተባሉ ስድስት ግለሰቦች ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የጎድሴን የኋላ ታሪክ ስናይ የሂንዱ ማሃሳብሃን ከመቀላቀሉ በፊት የሕንድ ገዢ ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ርዕዮተ ዓለም መስረት የሆነው የራሽትሪያ ስዋያምሴቫክ ሳንግ (ብሔራዊ የበጎ ፈቃደኞች ድርጅት) አባል ነበር።
አገሪቱን በአሁኑ ወቅት እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲም ቢሆኑ በሕንድ ውስጥ በሂንዱ ብሄርተኝነቱ ፈር ቀዳጅ የሆነው የ95 ዓመቱ ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲን (ቢጄፒ) የተቀላቀሉት ከረጅም ዓመታት በፊት ነው።
የራሽትሪያ ስዋያምሴቫክ ሳንግ (አርኤስኤስ) በሕንድ ባለው አገዛዝ እንዲሁም በውጭው ዓለም ከፍተኛ ሚናን በመጫወት የሚጠቀስ ነው።
ለአስርት ዓመታትም አርኤስኤስ "የሕንዳውያን አባት" ተብለው የሚጠሩትንና በድንቅነታቸው ታሪክ የሚዘክራቸውን ማህተማ ጋንዲ ገዳይን ጎድሴን ሲያወግዝ ይሰማ ነበር።
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሂንዱ ቀኝ አክራሪ ቡድን ጎድሴን በጀግንነት በማወደስና የጋንዲን መገደል በይፋ አክብረዋል። በባለፈው ዓመትም የገዢው ፓርቲ ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑ ግለሰብ ጎድሴን "አርበኛ" ሲሉ አሞካሽተውታል።
እነዚህ ክስተተች በርካታ ሕንዳውያንን ቢያበሳጩም አርኤስኤስ ጎድሴ ጋንዲን ከመግደሉ በፊት ከድርጅት አባልነቱ ተሰናብቷል በሚል አቋሙ እንደጸና ነው።
ነገር ግን በቅርቡ የወጣ መጽሐፍ የአርኤስኤስን አለኝ የሚለውን እውነት የሚያፈርስ ነው።
ጎድሴ ዓይነ አፋር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያቋረጠና ማሃሳብሃን ከመቀላቀሉ በፊትም በልብስ ስፌትና ፍራፍሬ በመሸጥ ይተዳደር ነበር።
ማሃሳብሃን ከተቀላቀለ በኋላ የጋዜጣ አርትዖት ሥራ ተሰማራ። በፍርድ ሂደቱ ወቅት 150 አንቀፆች ያሉትን መግለጫ ይዞ የቀረበ ሲሆን ለአምስት ሰዓት ያህልም አንብቧል።

የፎቶው ባለመብት, Haynes Archive/Popperfoto
ጋንዲን ለመግደል ምንም አይነት የተቀነባበረ ሴራ የለም በማለትም ተባባሪዎቹን ከቅጣት ለማዳንም ሞክሯል።
የሂንዱትቫ ወይም የሕንዳዊነት ማንነትን እሳቤ በወለደው በመሪያቸው ቪናያክ ዳሞዳር ሳቫርካር መሪነት ተቀነባብሮ የተፈጸመ ግድያ ነው የሚለውን ክስም ውድቅ አደረገው።
መሪው ሳቫርካር ከሁሉም ክሶች ነፃ ቢወጣም ተቺዎች ጋንዲን የሚጠላው የአክራሪው ቀኝ ክንፍ ከግድያው ጀርባ እጁ አለበት ብለው ያምናሉ።
ጎድሴ ጋንዲን ከመግደሉ ከረጅም ጊዜ በፊት ከአርኤስኤስ ጋር መቆራረጡን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
የጋንዲ ገዳይ መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ድሪንደርድራ ጃሃ ጎሴ በበኩላቸው ከፖስታ ሠራተኛ አባትና ከቤት እመቤት እናት የተወለደው ጎድሴ በአርኤስኤስ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሠራተኛ እንደነበርም አስፍረዋል።
በተጨማሪም ከአርኤስኤስ ስለመባረሩ ምንም አይነት መረጃ የለም ይላሉ።
ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ቃሉን በሚሰጥበት ወቅትም የሂንዱ ማሃሳብሃ አባል ከሆነ በኋላ ከአርኤስኤስ ስለመውጣቱ ያለው ነገር የለም።
ሆኖም ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት አርኤስኤስን ከተሰናበተ በኋላ የሂንዱ ማሃሳብሃ አባል እንደሆነ ቢናገርም መቼ ከድርጅቱ እንደወጣም ሊያስረዳ አልቻለም።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የጎድሴ ህይወት አከራካሪ ሆኖ መቀጠሉንም ጃሃ ይናገራሉ።
የአርኤስኤስ ደጋፊ ጸሐፊዎች ጎድሴ ጋንዲን ከመግደሉ ከአስር ዓመት በፊት ድርጅቱን እንደተሰናበተና ከዚያም ሂንዱ ማሃሳብሃን ተቀላቅሏል የሚል አጀንዳን ለመግፋት ተጠቅመውበታል ይላሉ ጃሃ።
አሜሪካዊው ተመራማሪ ጄኤ ኩራን ጁኒየር ጎድሴ አርኤስኤስን በ1930 እንደተቀላቀለ እና ከአራት ዓመት በኋላ መሰናበቱን ያስረዳል፣ ነገር ግን ለዚህ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም።
ጎድሴ የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለፖሊስ በሰጠው ለሁለቱም ድርጅቶች ይሰራ እንደነበር አምኗል ሲሉ ጃሃ ጽፈዋል።
የጎድሴ የቤተሰብ አባላት የዚህ ክርክር አካል ሆነዋል። በ2005 የሞተው የናቱራም ጎድሴ ወንድም ጎፓል ጎድሴ በበኩሉ አርኤስኤስን እንዳልተሰናበተ ተናግሯል።
የጎድሴ ታላቅ ወንድም ልጅ በ2015 ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ቆይታ ጎድሴ አርኤስኤስን በ1932 እንደተቀላቀለና ከድርጅቱም እንዳልተባረረ ራሱም እንዳልወጣ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተለያዩ መዛግብትን ያገላበጡት ጃሃ ሁለቱ የሂንዱ ድርጅቶች ግንኙነት እንደነበራቸው ያስረዳሉ።
የሂንዱ ማሃሳብሃ እና አርኤስኤስ ተመሳሳይ ግብና ለየት ያለ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ነው ሲሉ ጽፈዋል።
ሁለቱም ድርጅቶች ጋንዲ እስከሚገደሉበት ጊዜ ድረስ የቅርብ ጊዜ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን የሁለቱም ድርጅቶች አባል የሆኑ ግለሰቦች ነበሯቸው።
ጋንዲ ከተገደሉ በኋላ አርኤስኤስ ከአንድ ዓመት በላይ ታግዷል።
አርኤስኤስ ጎድሴ በፍርድ ቤት የተናገረውን ድርጅቱን በ1930ዎቹ አጋማሽ ለቅቆ መውጣቱን በመጥቀስ እንዲሁም የፍርድ ቤት ውሳኔውን ከአርኤስኤስ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ማሳያ ነው ሲልም ይከራከራል።
የአርኤስኤስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ራም ማድሃቭ ጎድሴ በግድያው ወቅት "የአርኤስኤስ አባል ነበር ማለት ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት የተፈጠረ ውሸት ነው" ብለዋል።
በአርኤስኤስ በጣም ተደማጭነት ካላቸው መሪዎች አንዱ የሆኑት ኤም ኤስ ጎልዋልከር የጋንዲን ግድያ "ወደር የለሽ አሳዛኝ ሁኔታ" ሲሉ በመግለጽ በጣም አስደንጋጭ የሚያደርገውም ግድያውን ያቀነባበረው የአገሪቱ ዜጋና ሂንዱ መሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜም እንደ ኤምጂ ቫይድያ ያሉ የአርኤስኤስ አመራሮች "የሕንድን ታላቅ ሰው በመግደል የሂንዱትቫን ፅንሰ ሃሳብ ያንቋሸሸ ነፍሰ ገዳይ" ሲሉ ጎድሴን ጠርተውታል።
እንደ ቪክራም ሳምፓት ያሉ ደራሲዎች በበኩላቸው አርኤስኤስ እና የሂንዱ ማሃሳብሃ የሚሞቅና የሚቀዘቅዝ ግንኙነት እንደነበራቸው ያምናሉ።
የሳቫርካርን የህይወት ታሪክ በሁለት ጥራዝ የፃፉት ቪክራም ሳምፓት "የሂንዱዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ" በሚል የሂንዱ ማሃሳብሃ የበጎ ፈቃደኞች ቡድንን ከ"አብዮታዊ ምስጢራዊ ማኅበር" ጋር በማዋቀር ያደረገው ውሳኔ አሳዝኖታል፣ ከአርኤስኤስ ጋር የነበረውንም ግንኙነት አሻክሮታል።
ሳምፖት እንዳሉት "በጀግንነት አምልኮ የተጠመደ እና የተጋነነ አድናቆት "እሳቤን " ከሚከተለው ከማሃሳብሃ መሪ ሳቫርካር በመለየትም አርኤስኤስ ግለሰቦችን ጣኦት ከማድረግ ተቆጥቧል።
አርኤስኤስ 'ኤ ቪው ቱ ዘ ኢንሳይድን' የጻፉት ዋልተር ኬ አንደርሰን እና ሽሪድሃር ዲ ዳም በመጽሐፋቸው የቀድሞው አባል ናቱራም ጎድሴ በጋንዲ ግድያ ላይ መሳተፉ ድርጅቱን በከፍተኛ ሁኔታ አጠልሽቶታል፤ ጎድቶታልም ብለዋል።
ድርጅቱ የፋሽስት፣ አምባገነን፣ አጭበርባሪዎችን ከመደገፍ ጋር መያያዙ ስሙ ጠፍቷል።
ነገር ግን ጎድሴ የአርኤስኤስ አካል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥርጣሬዎች መቼም ደብዝዘው አያውቁም።
ጎድሴ በኅዳር 15/1949 ወደ መሰቀያው ስፍራ ከመወሰዱ በፊት የአርኤስኤስ ፀሎት የመጀመሪያዎቹን አራት ዓረፍተ ነገሮች ሲያነበንብ ነበር።
"ይህም የድርጅቱ ንቁ አባል እንደነበረ በድጋሚ ያሳያል" ሲሉ ጃሃ ያስረዳል። "አርኤስኤስን ከጋንዲ ገዳይ ማግለል የታሪክ ፈጠራ ነው" ይላሉ ጃሃ።
ማስታወሻ፦ በፅሁፉ የተጠቀሱት የቀን አቆጣጠሮች በሙሉ በአውሮፓውያኑ ነው
















