በሕንድ የቤት ውስጥ አየር ብክለት ውጭ ካለው የባሰ እንደሆነ ተደረሰበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕንድ በቤት ውስጥ ያለው የአየር ብክለት ከቤት ውጭ ካለውም የባሰ እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ።
ይህ ጥናት እንደተረዳው ሳንባን በከፋ ሁኔታ የሚጎዳው ረቂቅ ብናኝ (PM2.5) በሕንድ ከደጅ ይልቅ በቤት ውስጥ በብዛት ይገኛል።
በተለይ በኒው ዴልሒ ያለው የአየር ብክለቱ መጠን ከሌሎች የዓለም ከተሞች ሁሉ በመጠን አደገኛ የሚባል ነው።
ዴልሒ በተከታታይ ዓመታት ከዓለም ከተሞች በአየር ብክለት ስሟ ተደጋግሞ ይነሳል። ይህም ከኢንዱስትሪ የሚወጣው ጭስ፣ አቧራ፣ የሚሊዮን ተሸከርካሪዎች ጭስ፣ ገበሬዎች የሚያቃጥሏቸው የእህል ተረፈ ምርቶች፣ በሕንድ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል (ዲዋሊ) የሚተኮሱ ርችቶች ለዚህ ክፉ የአየር ብክለት ምክንያት ሆነዋል።
በዚህ የተነሳም በተለይም ድሆች በሕንድ አየር ብክለት ከሀብታሞች ይልቅ ተጋላጭ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር። ይህ እንዳልሆነ ግን በጥናት ተረጋግጧል።
የቺካጎ ኢነርጂ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ከ2018 እስከ 2020 ባደረገው አንድ የናሙና ጥናት በሕንድ ሀብታምና ድሀ በእኩል በአየር ብክለት እንደሚጎዱ ደርሶበታል።
ምንም እንኳ ሀብታሞች አየር ብክለት መከላከያና ማጣሪያ በቤታቸው ቢያስገጥሙም ለበካይ አየር ከድሆች እኩል ተጋላጭ እንደሆኑም ጥናቱ ደርሶበታል።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ኬኔት ሊ እንዳሉት "በሕንድ ሃብታም መሆንና አለመሆን በዚህ ረገድ እምብዛምም ልዩነት የለውም።"
የዓለም ጤና ድርጅት በሚያወጣው መረጃ መሠረት በምድራችን ላይ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ይሞታሉ።
አሁን ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ የአየር ብክለቱ ደጅ ካለው ይልቅ በቤት ውስጥ ያለው በአምስት እጥፍ የከፋ መሆኑን ነው።
በዓለም የአየር ብክለት የከፋ ከሆነባቸው 30 ከተሞች ውስጥ 20ዎቹ የሚገኙት በሕንድ ነው።
በዚህ የተነሳም በሕንድ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ይሞታሉ ተብሎ ይገመታል።















