የአየር ብክለት፡ ትራምፕ ስለ ሕንድ የአየር ብክለት የተናገሩት በርካቶችን አስቆጣ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሕንድ ዜጎች ስለሚነፍሰው አየር በሰጡት አስተያየት ምክንያት በርካታ ሕንዳውያን ቁጣቸውን እየገለፁ ነው። ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ክርክር ወቅት ነበር የሕንድን አየር 'አስጸያፊ' በማለት የገለጹት።

የፕሬዝዳንቱ አስተያየት ቁጣም መገረምም የፈጠረ ሲሆን አንዳንድ ሕንዳውያን እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ሌሎች ደግሞ የዋናዋ ከተማዋ ደልሂ አየር በጣም የተበከለ እንደሆነና ከዓለም እጅግ መጥፎው አየር እንደሆነ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

በቅርብ ሳምንታት የከተማዋ አየር ንጽህና በእጅጉ እየተባባሰ እንደመጣና ነዋሪዎቹ የመተንፈስ እክል ጭምር እያጋጠማቸው እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

የሕንድ የአየር ብክለት ደረጃ ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አየሩ በካይ የሆኑ ንጥረነገሮችን በውስጡ በብዛት የያዘ ነው ተብሏል።

በዋና ከተማዋ ያለው የብክለት መጠን ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው የጤናማ አየር ልክ በ12 እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

''ቻይናን ተመልከቱ፤ እንዴት አስጸያፊ እንደሆነ። ሕንድንም ተመልከቱ። እዛም ቢሆን አየሩ አስጸያፊ ነው። ከፓሪሱ የአየር ጸባይ ለውጥ ድርድር ላይ ጥዬ የወጣሁት በማይገባ መልኩ በትሪሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እየከሰርን ስለነበረ ነው'' ብለዋል።

ምንም እንኳን ቻይናን የተመለከቱት አብዛኛዎቹ አስተያየቶች እውነት ባይሆኑም ስለሕንድ የተናገሩት ግን በርካቶችን አስማምቷል።

በሰሜናዊ ሕንድ በርካታ ከተሞች የአየር ብክለት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ለሕዳር እስከ የካቲት ባሉት ወራት ደግሞ አርሶ አደሮች ለቀጣዩ ዓመት ማሳቸውን ለማዘጋጀት በርካታ ማሳዎችን በእሳት ያቃጥላሉ።

በተጨማሪም በሕንድ ያለው የመኪና ጭስ ብክለት ከፍተኛ ሲሆን ትልልቅ የማምረቻ ፋብሪካዎችም ቢሆኑ በካይ ንጥረነገሮችን ወደ ከባቢ አየር በብዛት እንደሚለቁ ይታወቃል።

በነዚህ ወራት ደግሞ ሕንዳውያን የተለያዩ በአላትን ለማክበር በማሰብ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ርችት ወደ ሰማይ ይተኩሳሉ። ይህ ደግሞ በዚህ ወቅት የአየር ብክለትን ይጨምራል።

ባለፈው ዓመት በህንዷ ዋና ከተማ ዴልሂ ባጋጠመ የአየር ብክለት ምክንያት ሃላፊዎች የማህበረሰብ ጤና ድገተኛ አደጋ አዋጅ ለማወጅ መገደዳቸው ይታወሳል። በተጨማሪም በከተማዋ ለሚገኙ 5 ሚሊየን ተማሪዎች አፍ መሸፈኛ ማስክ ሲከፋፈል ነበር።

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መለኪያ መሰረት ጎጂ ጥቃቅን አካላቱ በአንድ ቀን ውስጥ ከ 25 ማይክሮግራሞች መብለጥ የሌለበት ሰሆን በዴልሂ ኤር ውስጥ ግን 533 ማይክሮግራሞች የበለጠ ጎጂ ንጥረነገር ወደ ሳንባ ይገባል።

የፕሬዝዳንቱን አስተያየት ተከትሎ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ሰዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ሲሆን የሕንድ ተቀናቃኝ ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ካፒል ሲባል ትራምፕ ይህንን ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ካላቸው ቅርበትና ጓደኝነት ነው ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።