በሕንድ ዋና ከተማ ደልሒ የአየር ብክለት በመባባሱ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደልሒ የአየር ብክለቱ እየከፋ በመምጣቱ ሁሉም ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች እንዲዘጉ ተወሰነ።
የግንባታ ሠራተኞችም ለጊዜው ማንኛውንም ግንባታ እንዲያቆሙ ታዘዋል።
ይህ የግንባታ እቀባ የሚመለከታቸው ከአገር መከላከያና ከትራንስፖርት ግንባታ ውጭ ያሉትን በሙሉ ነው።
ከከሰል ልማት ጋር በተያያዘ ደግሞ ከ11ዱ ግዙፍ ኃይል ማመንጫዎች 5ቱ ብቻ ሥራ እንዲቀጥሉ ታዘዋል።
ከሕንዶቹ አዲስ ዓመት ዲዋሊ ወዲህ በሕንድ ዋና ከተማ ደልሒ መርዛማ ጭስ አየሩን በክሎታል።
ሕንድ የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው የአየር ብክለት ምጣኔ እጅግ ከፍ ያለና አደገኛ የሚባል ደረጃ ያለ በካይ ጭስ ነው ያላት።
የሰዎች የመተንፈሻ አካል አካልን ሊደፍን የሚችል የፒኤም2.5 መጠን በዴህሊ ከፍተኛ መጠን ላይ ደርሷል።
የአከባቢ አየር ጥራት በሚለካበት ደረጃ መሰረት ከዜሮ እስከ 50 'መልካም' የሚባል ሲሆን ከ51 እስከ 100 ደግሞ 'አጥጋቢ' የሚባል ደረጃ አለው። በደልሒ ከዚህ ከፍ ሲል ግን አደገኛ ደረጃ ተብሎ ይቀመጣል።
የሕንድ በርካታ ከተሞች ከ400 በላይ የአየር ጥራት ምጣኔ የሚያስመዘግቡ ሲሆን ይህም ሳንባን ለከፍተኛ በሽታ የሚዳርግ ደረጃ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።
ባለፈው ሳምንት በርካታ ትምህርት ቤቶች በደልሒ እንዲዘጉ ተደርጎ ነበር። ሠራተኞችም ቢሆኑ ከቤታቸው ሆነው ሥራ እንዲሠሩ እየተበረታቱ ነው።
በደልሒ አየሩ እንዲበከል የሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች ሲኖሩ በተለይ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ጭሶች፣ አቧራ እና ሌሎች አየር በካይ ሁኔታዎች ደልሒን በዓለም የአየር ጥራት ዝቅተኛውን ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል።
በዲዋሊ አዲስ ዓመት የሚተኮሱ ርችቶችም እንደ አንድ አየር በካይ ምክንያት ይጠቀሳሉ።
በሕንድ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ብቻ ከሚፈጠሩ የጤና እክሎች የተነሳ በየዓመቱ ሚሊዮን ሰው ይሞታል ተብሎ ይገመታል።












