የአሜሪካ ዲፕሎማት በቁም እስር ካሉት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ

በቁም እስር ላይ የሚገኙት አብደላ ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በቁም እስር ላይ የሚገኙት አብደላ ሐምዶክ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ረዳት ሚኒስትር በሱዳን ለሦስት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት ካለፈው ወር መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ በቁም እስር ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን አነጋግረዋል።

ሞሊ ፊ "የሱዳንን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ወደነበረበት መመለስ በሚቻልባቸው መንገዶች" ላይ ስለመወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ከማስፈራቸው በቀር ስለተነጋገሩበት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት በመምራት ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ ያደረጉት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን አዲስ ምክር ቤት መስረተው እራሳቸውን ደግሞ መሪ አድርገው መሰየማቸው ይታወሳል።

ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን ይህን ምክር ቤት ያቋቋሙት መፈንቅለ መንግሥቱን ለመቀልበስ ከአገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ አካላትም ጫናው በጨመረበት ወቅት ነው።

የተባበሩት መንግሥታትም የሱዳንን ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ በአስቸኳይ ድርድር እንዲካሄድ ጠይቋል።

አሜሪካ እአአ ከ2019 ጀምሮ በጋራ ያስተዳድር የነበረው የወታደራዊ-ሲቪል መንግሥት ላይ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዛለች።

የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ኦማር አልበሽር ከሥልጣን መውረድን ተከትሎ የተመሰረተው ወታደራዊ-ሲቪል መንግሥት ለምርጫ መንገዱን ያመቻቻል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ሞሊ ፊ፤ የመፈንቅለ መንግሥቱን መሪ አብደል ፋታህ አል ቡርሐንንም አግኝተዋል።

ሱና የተሰኘውን የአገሪቱን የዜና ወኪል በመጥቀስም በቁጥጥር ስር የዋሉትን የመልቀቅ ሂደት መጀመሩን ዘግቧል።

መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም የሚካሄደው ተቃውሞ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

አንዳንድ ባልደረቦቻቸው የታሰሩባቸው ጋዜጠኞች ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም ማክሰኞ ሰልፍ አድርገዋል።