በሕይወት ሳሉ ‘ሞተዋል’ ተብለው መሬታቸውን የተቀሙ ሕንዳውያን

የ70 ዓመቱ ፓድሳር ያዴቭ
የምስሉ መግለጫ, የ70 ዓመቱ ፓድሳር ያዴቭ

የ70 ዓመቱ ፓድሳር ያዴቭ ልጃቸው እና የልጃቸው ባለቤት ከሞቱ በኋላ ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን ማሳደግ ግዴታቸው ሆነ።

የእድሜ ባለጸጋው የልጅ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ በትውልድ ቀያቸው ከአባታቸው የወረሱትን መሬት ሸጡ።

መሬታቸውን ከሸጡ ከወራት በኋላ ግራ የሚያጋባ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው።

"መሬቱን የሸጥኩለት ሰውዬ ደውሎ የወንድሜ ልጅ 'አጎቴ ሞቷል። መሬቱን በአጎቴ ስም የሸጠለህ ሰው አጭበርባሪ ነው' እንዳለው ነገረኝ።"

የፓድሳር የወንድም ልጅ ፓድሳር እንደሞቱ እያስነገረ ነበር። ይህንን ዜና ሲሰሙ ወደ ኮልካታ ግዛት በፍጥነት ተጓዙ።

ኮልካታ ከተማ ሲደርሱ ፓድሳርን ያዩ ሰዎች ይደነግጡ ጀመር። በሕይወት ያለ ሰው ሳይሆን መንፈስ ሥጋ ለብሶ ሲራመድ ያዩ እየመሰላቸው በርካቶች በረገጉ።

"ሲያዩኝ የሙት መንፈስ ያዩ ይመስል ክው አሉ። ሞተህ የለ እንዴ? ለቅሶህን ደርሰን፣ ሐዘናችንን ገልጸን የለ እንዴ? እያሉ ጠየቁኝ።"

ፓድሳር እና የወንድማቸው ልጅ ይቀራረባሉ። ልጁ አዘውትሮ ይጠይቃቸውም ነበር።

መሬታቸውን ሊሸጡ እንደሆነ ሲነግሩት ግን ቤታቸው እየሄደ መጠየቅ እንዳቆመ ይናገራሉ።

መሬቱ የፓድሳር ሳይሆን የእሱ እንደሆነ ማስነገር ሲጀምር ያለበት ቦታ ድረስ ሄደው አነጋገሩት። ለምን መሬቱ የእኔ ነው ትላለህ? ብለው ሲጠይቁት ግን ማን እንደሆኑ እንደማያውቅ አስመሰለ።

"አጎቴ ሞቷል። አንተ ማነህ?" ብሎ የወንድማቸው ልጅ በድፍረት ሲጠይቃቸው ነገሩን ለማመን ከበዳቸው።

"እዚህ ፊት ለፊትህ ቆሜ እያነጋገርኩህ እንዴት አጎቴ ሞቷል ትላለህ?" ቢሉትም ምላሹ አልተቀየረም።

ፓድሳር በወንድማቸው ልጅ ድርጊት አዝነው ለቀናት አለቀሉ። ከዚያም ጉዳያቸውን ወደ አንድ ማኅበር ለመውሰድ ወሰኑ።

ይህ ማኅበር 'ሊቪንግ ዴድ ኦፍ ኢንዲያ' ይባላል። በሕይወት ሳሉ 'ሞተዋል' ተብለው ንብረታቸውን የተቀሙ ሕንዳውያንን ጉዳይ ይከታተላል።

'ሟች ላል'

የማኅበሩ መሪ ላል ቢሀሪ ሚታክ ይባላሉ። በ60ዎቹ እድሜ ክልል ይገኛሉ። ላል የሕይወታቸውን አንድ ሦስተኛ ያሳለፉት 'ሞተዋል' ተብለው ነው።

ቤተሰቦቻቸው ድሀ ናቸው። ልጅ ሳሉ በፋብሪካ ሠራተኛነት ስለተቀጠሩ ማንበብና መጻፍ አልተማሩም።

በ20 ዓመታቸው ገደማ የጨርቅ ማምረቻ ለመክፈት አሰቡ። ከባንክ ብድር ለመውሰድ መያዣ እንዲሆናቸው ከአባታቸው መሬት መውረሳቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ፍለጋ ወደ ቀበሌ አቀኑ።

የተሰጣቸው ሰነድ ግን 'ላል ሞቷል' የሚል ነበር።

የማኅበሩ መሪ ላል ቢሀሪ ሚታክ ይባላሉ። በ60ዎቹ እድሜ ክልል ይገኛሉ።
የምስሉ መግለጫ, የማኅበሩ መሪ ላል ቢሀሪ ሚታክ ይባላሉ። በ60ዎቹ እድሜ ክልል ይገኛሉ።

ላል የቀበሌው ሰነድ እንደተሳሳተና በሕይወት እንዳሉ ገልጸው ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም።

ቀበሌው መሞታቸውን የሚገልጽ ሰነድ ካዘጋጀ በኋላ መሬታቸውን ለአጎታቸው ቤተሰቦች አውርሷል።

ላል በሕይወት እያሉ 'ሞቷል' የሚል ሰነድ በቀለቤ የተመዘገበው በስህተት ይሁን በአጎታቸው አሻጥር እርግጠኛ አይደሉም።

ነገር ግን በዚህ ሰነድ ሳቢያ ንግዳቸውን መቀጠል አልቻሉም። ቤተሰባቸውን ማስተዳደርም ተቸገሩ።

ብዙም ሳይቆይ ግን እሳቸውን የገጠማቸው አይነት ነገር የብዙዎች ታሪክ እንደሆነ ሰሙ። ቤተሰቦቻቸውን ወይም ዘመዶቻቸውን 'ሞተዋል' እያሉ መሬት የሚቀሙ ሰዎች እንዳሉ ደረሱበት።

ከዚያም እነዚህን ቀማኞች ለመታገል ማኅበር አቋቋሙ።

በሕንድ፣ ሁታር ፕራድሽ በተባለ ግዛት ውስጥ ብቻ በሕይወት ሳሉ 'ሞተዋል' ተብለው የተመዘገቡ 40,000 ነዋሪዎች አሉ።

አብዛኞቹ ድሆች፣ ያልተማሩና፣ መገለል ከሚገጥማቸው ጎሳዎች የተወለዱ ናቸው።

ላል በማኅበሩ አማካይነት ንቅናቄ ማድረግ ጀመሩ። ራሳቸውን 'ሟች ላል' እያሉ በመጥራት ነው ንቅናቄውን የሚመሩት። በሂንዲ ቋንቋ 'ሚታክ ላል' ሲሉ ራሳቸውን ይጠራሉ።

ንቅናቄው የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ቢያገኝም እምብዛም ለውጥ አልመጣም። ላል ለውጥ አለመምጣቱን ሲያዩ በብሔራዊ ምርጫ ተወዳደሩ።

መንግሥት ግን በሕይወት መኖራቸውን ሊቀበል አልቻለም። በዚህ ተበሳጭተው ሦስት ጊዜ የረሃብ አድማ በማድረግ ራሳቸውን ለመግደል ሞክረዋል።

ይህም አልሳካ ሲላቸው የአጎታቸውን ልጅ አፈኑ። አላማቸው ፖሊስ አስሯቸው በሕይወት መኖራቸው ማረጋገጫ እንዲያገኝ ነበር።

መቼም በቁጥጥር ሥር የሚውለው በሕይወት ያለ ሰው ነው ብለው የአጎታቸውን ልጅ ቢያግቱም ፖሊስ ግን በጉዳዩ ጣልቃ አልገባም ብሎ ሳያስራቸው ቀረ።

በስተመጨረሻ አንድ በቅርቡ የተቋቋመ የአስተዳደር መዋቅር የላልን ጉዳይ ተመልክቶ 'በሕይወት አሉ' ብሎ ፈረደላቸው።

ለ18 ዓመታት 'ሞተዋል' የተባሉት ላል በሕይወት እንዳሉ ተረጋገጠላቸው።

የሺዎች ትግል

ማኅበራቸው በመላው ሕንድ በሺዎች የሚቆጠሩ 'ሞተዋል' የተባሉ ሰዎችን ጉዳይ መፍትሔ ሰጥቷል።

ሁሉም ሰዎች ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም። በሂደቱ መሀል ራሳቸውን ያጠፉ፣ እድሜ ልካቸውን በሕይወት እንዳሉ ለማስመስከር የታገሉ፣ ተስፋ ቆርጠው ጉዳዩን የተዉ እና ጉዳያቸው እልባት ሳያገኝ ሞት የቀደማቸውም በርካታ ናቸው።

ቲላክ ቻንድ ዳህካድ አሁን የ70 ዓመት አዛውንት ናቸው።

ወጣት ሳሉ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ከገጠር ወደ ከተማ ገቡ። ገጠር ያለውን መሬታቸውን ለጥንዶች አከራይተው ነበር ከትውልድ መንደራቸው የወጡት።

ወደ መንደራቸው ሲመለሱ ግን ስማቸውም ከመሬቱ ባለቤት ሰነድ መፋቁ ተነገራቸው። ምክንያቱ ደግሞ ሞተዋል ተብሎ ለቀበሌ ሪፖርት መደረጉ ነው።

ጥንዶቹ ቲላክ 'ሞተዋል' ብለው አስመዝግበው መሬታቸውን እያከራዩ ነበር። መሬቱን ተከራይተው የነበሩት ጥንዶች ፍርድ ቤት ሄደው፣ ሚስትየው የቲላክ ባለቤት እንደሆነች በማስመሰል መስክረው ነበር መሬቱን የራሳቸው ያደረጉት።

ስለ ጉዳዩ ቢቢሲ ጥንዶቹን ቢጠይቃቸውም ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም።

አኒል ኩመር ጠበቃ ነው። በሕይወት ሳሉ ሞተዋል የተባሉ ብዙ ደንበኞች አሉት። አንዳንድ ባለሥልጣናት በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሞተዋል የሚል ሰነድ ለማውጣት ጎቦ እንደሚቀበሉ ይናገራል።

አንዳንዴ ደግሞ ሐኪም ቤት ውስጥ በሚሠራ ስህተት በሕይወት ያለ ሰው ሞቷል ይባላል።

የሕንድ ገዢ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሻንያ ኤንሲ እንደሚሉት መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ነው።

ሙሰኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም አክለወዋል።

ጠበቃው ግን ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ የፍርድ ቤት ጉዳዮች በቀላሉ እልባት እንደማያገኙ ይናገራል። ለ25 ዓመታት ያህል ፍርድ ቤት የተመላለሰባቸው ነገር ግን ብይን ያልተሰጣቸው ጉዳዮች እንዳሉ እንደ ማስረጃ ይጠቅሳል።

"ከእነዚህ ወንጀሎች ጀርባ ያሉ ሰዎች ቢቀጡ ሌሎች ወደ ወንጀሉ እንዳይገቡ ማስጠንቀቂያ ይሆናል" ይላል።

ላል ሞተዋል ከተባሉ 45 ዓመታት ተቆጥተዋል። በሕይወት እንዳሉ ከተረጋገጠ ደግሞ 20 ዓመታት አልፏል።

ልደታቸውን ሲያከብሩ የሚቆርሱት ኬክ እውነተኛ የሚበላ ኬክ ሳይሆን ከእንጨት የተሠራ የይምሰል ኬክ ነው። "ይህ ኬክ ውስጣቸው ባዶ የሆነና ለፍትሕ ያልቆሙ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተምሳሌት ነው" ይላሉ።

አሁንም ድረስ ከመላው ሕንድ በርካቶች ይደውሉላቸውና "በሕይወት ሳለን ሙት ተብለናልና መፍትሔ ፈልግልን" ይሏቸዋል።

ላል ግን እድሜ እየተጫጫናቸው ነው።

"ማኅበሩን እየመራሁ የምቀጥልበት ገንዘብ እና አቅም የለኝም። የሚረከበኝም ሰው የለም" ይላሉ።

መንግሥት ለዓመታት ሙስናን አጠፋለሁ ቢልም እምብዛም ለውጥ አለማስተዋላቸው ያሳዝናቸዋል።

ለ18 ዓመታት ያህል አለመሞታቸውን ለማስመስከር የታተሩት ላል አንድ ቀን፣ ቀናቸው ደርሶ ይቺን ዓለም መሰናበታቸው አይቀርም። የትግላቸውን ፍሬ ሳያዩ የሚያልፉበት እድል ሰፊ መሆኑ ደግሞ ያስቆጫል።