ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በ10 ወራት 100 ሺህ ኢትዮጵያን ተመልሰዋል አለ

ከስደት ተመላሾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በአውሮፓውያኑ 2020 በመጀመሪያዎቹ 10 ወራት 100ሺህ ኢትዮጵያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል አለ።

ድርጅቱ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ከመዘገብኳቸው 100ሺህ ስደተኞች መካከል ከ71ሺህ በላይ የሚሆኑት የተመለሱት ከሳዑዲ አረቢያ ነው ብሏል።

ይህ አሃዝ ከእአአ 2017 ጀምሮ ከሳዑዲ አረቢያ በግዴታ የተመለሱ ሰደተኞችን ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ያደርሰዋል ብሏል አይኦኤም።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደ አገራቸው የሚመሰሉት ምንም ሳይኖራቸው እና ለከፍተኛ የአእምሮ ጤና መታወክ ተጋልጠው በመሆኑ በአገሪቱ ላይ ጫናን ይፈጥራል ብሏል ድርጅቱ።

ከተመላሽ ስደተኞች መካከል አንድ ሦስተኛው ግጭት ከነበሩባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ በመሆናቸው በተመለሱ ጊዜ መሄጃ አጥተው መጉላለት ገጥሟቸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የስደተኞች መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ በሆነችው ኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መዳረሻቸውን መካከለኛው ምስራቅ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አውሮፓ አድርገው ለስደት የሚነሱባት አገር መሆኗን አይኦኤም ገልጿል።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነ ወደ ቀያቸው የሚመሰሉ እና ቀውስ ባጋጠማቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ እርዳታ እና ጥበቃ በ2022 አስፈልጓቸዋል ብሏል አይኦኤም።

በአሁኑ ወቅት 2.72 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሰዎች ትግራይ ክልልን ሳይጨምር በ11 የኢትዮጵያ ክልሎች መለየታቸውን የገለጸው ድርጅቱ፤ የሰሜን ኢትዮጵያው እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት ግጭቶች እና እንደ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሰዎችን በዋናነት ከቀያቸው የሚያፈናቅሉ እና እርዳታ ጠባቂ የሚያደርጉ ምክንያቶች ናቸው።

የተፈናቃዮች ከፍተኛ ቁጥር እና በግጭት ምክንያት መሠረታዊ አገልግሎቶች መውደማቸው የሕዝቡን የወደፊት ተጋላጭነት ያመላከቱ ሆነዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት

በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የሰላም ስምምነቱ መፈረሙ በግጭት ቀጠና ለቆየው አካባቢ የዘላቂ ሰላም ተስፋን ያጫረ ነው ብሏል አይኦኤም።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ የነበረው የደኅንነት ሁኔታ መሻሻሉ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እድል የሚከፍት ነው ብሏል ድርጅቱ።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች እና በረራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ እርዳታ ሳይደርስባቸው ወደ ቆዩ አካባቢዎች መድረስ እየቻሉ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ላ ሊና በፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ያጋጠማቸው ሲሆን 8 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና አፋር በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ የኢትዮጵያ ክልል መሆናቸውን እና በድርቁ ምክንያት 3.5 የጋማ ከብቶች መሞታቸው እና 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ እጥረት መኖሩ የሰዎች ስደተን ከፍ እንደሚያደርግ አይኦኤም አመልክቷል።