“ከእናቴ ቀድሜ በ25 ዓመቴ አረጥኩኝ” ይህ እንዴት ሊከሰት ይችላል?

በ23 ዓመቷ ማረጥ ያጋጠማት ሶኢ ምያት

በአስራዎቹ ዕድሜ ወይም 20ቹ እድሜ ላይ ሆናችሁ ማረጥ ቢያጋጥማችሁ ምን ታደርጋላችሁ?

ማሰብ እራሱ ከባድ ነው።

ኤማ፣ ሶኢ ምያት እና ኤልስፔት የገጠማቸውም ይኸው ነው።

የወጣትነት ህይወት ዘመናቸው እንዲህ ይሆናል ብለው በጭራሽ አልገመቱም።

ነገር ግን በአንዳንድ ሴቶች ላይ የሚያጋጥመው የወጣትነት ማረጥ እንዳጋጠማቸው ተነገራቸው።

ብዙም የማይነገርለት የወጣትነት ማረጥ ከዕድሜ እኩዮቻችው ተለይተው ብቸኛ እንዲሆኑ አደረጋቸው።

ኤማ ዴላኔ በ25 ዓመቷ ማረጥ እንዳጋጠማት በህክምና ባለሙያ የተነገራት በአውሮፓውያኑ 2013 ነበር።

ኤማ ይህ መርዶ የሚባል ዜና ሲነገራት ከሆስፒታሉ ወንበር መነሳት አቃታት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዶክተሩ እየተናገረው ያለውን ነገር እንደ መጥፎ ቅዠት ነበር ያየችው።

ይህ ዜና ከመነገሩ በፊት በነበሩ ዓመታት የእርግዝና መከላከያ ትወስድም ስለነበር የወር አበባዋ ተቋርጦ ነበር።

ከዚያ በኋላም በነበሩት ጊዜያትም የወር አበባዋ ቆመ።

“ምን እንደምመልስ አላውቅም ነበር። ልጆች መውለድ እንደማልችል የሰማሁትን ዜና ልክ ቁልፍ እንደጠፋብኝ ያህል ነው የተነገረኝ” በማለት ታስረዳለች።

ኤማ የመጀመሪያ ደረጃ የኦቫሪያን (የዘር እንቁላል የሚያመርቱ እንቁልጢቶች) ብቃት ማነስ ወይም በምህጻረ ቃል ፒኦአይ በተባለ በሽታ ከተጠቁ ሴቶች መካከል አንዷ ናት። ይህም ማለት ከ40 በታች የሆኑና ማረጥ ያጋጠማቸው ሴቶች ማለት ነው።

የዚህ ችግር መንስኤ አይታወቅም። በዩናይትድ ኪንግደም ከመቶ ሴቶች መካከል አንዷ በፒኦአይ ተጠቂ መሆኗን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ ባለሙያዎች ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ምንም እንኳን ችግሩ በበርካታ ሴቶች ላይ ቢያጋጥምም፣ ዝም የተባለ ጉዳይ ነው።

“በወጣትነት ዕድሜ ስለሚያጋጥመው ማረጥ በቂ ውይይት የለም። በተለምዶ አሮጊት ሴቶች ከሽበታቸው ጋር ነው የሚታዩት። ይህ ግን ክስተቱን አይወክልም” ሲሉ የማረጥ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኒግሃት አሪፍ ያስረዳሉ።

እንደ ኤማ ላሉት አንዳንዶች ኦቫሪያቸው የመስራት ችግር ለምን አጋጠማቸው የሚለው ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ሰውነት አንዳንድ ጤነኛ ህዋሳትን እንደ በሽታ የሚያይበት ሁኔታ ሲፈጠር (አውቶ ኢሚውን) በሚባለው ሁኔታ፣ የሰውነታችንን ዲኤንኤ የያዘው ክሮሞዞም እክል ወይም በማህጸን ላይ በሚደረግ ቀዶ ህክምና ሊከሰት ይችላል።

ኤማ ይህንን ዜና ከሰማች በኋላ መኪናዋ ውስጥ ገብታ ለብቻዋ ለአንድ ሰዓት ያህል አለቀሰች። ሐዘን፣ ድንጋጤ፣ አለማመን ተፈራረቁባት።

በ25 ዓመቷ ማረጥ ያጋጠማት ኤማ
የምስሉ መግለጫ, በ25 ዓመቷ ማረጥ ያጋጠማት ኤማ

ኤማ ስለ ማረጥ ብዙም የምታውቀው ጉዳይ አልነበረም። በምትሰራበት ፀጉር ቤት ማንችስተር የሚመጡ ትልልቅ ሴቶች ከሚያወሩት አንዳንድ ወሬዎች በስተቀር።

የወደፊቱን፣ ህልሟን እንደተነጠቀች ተሰማት። ለወደፊቱ ለመውለድ ያቀደቻቸው ሁለት ልጆች ህልምም ጨለመ።

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተተኪ የሆርሞን ህክምና (ሆርሞን ሪፕሌስመንት ቴራፒ) ክኒኖችን መዋጥ ጀመረች።

በሰውነቷ ውስጥ ያሉት የዘር እንቁላል የሚያመርቱት ኦቫሪዎች (እንቁልጢዎች) ሥራ እንዳቆሙና ሰውነቷ በቂ የኤስትሮጅን እንዲሁም ፕሮጄስትሮን ሆርሞኖችን እያመረተ እንዳልሆነ ተረዳች። እነዚህ ሆርሞኖች የወር አበባ ዑደትን የሚቆጣጠሩ ናቸው። ይህም አለመመጣጠን ለዓመታት ጤናዋ ላይ ጫና እያሳረፈ ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ጭጋግ ተብሎ የሚጠራው ደካማ የማስታወስ ችሎታ እና ትኩረት ማጣት ከእሷ ማንነት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳልሆነ ተረዳች። ሰውነቷ ሙቀት ሙቀት የሚላት ለረጅም ሰዓታት የፀጉር ማድረቂያ በመጠቀሟም አልነበረም። እንዲሁም እንቅልፍ እጦቷም በሰውነቷ ውስጥ የነበሩ ሆርሞኖች አለመመጣጠን ምልክቶች ነበሩ።

በወቅቱ 40ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረችው እናቷ ማረጥ አልገጠማትም። ጓደኞቿ ያገቡበት እና ልጅም ለመውለድ እያሰቡ የነበረበት ወቅትም ነበር። “ማንም እንደማይረዳኝ ተሰማኝ” በማለትም ታስረዳለች።

ኤማ ከዚህ ሁሉ ጭንቀት ለመውጣት ትኩረቷን ሁሉ ሥራዋ ላይ አደረገች። የምርመራ ውጤቷንም ከመወያየት ተቆጠበች።

ከብዙ ወንዶች ጋር መውጣት እና መጠጣትም ማዘውተር ጀመረች።

“ሰውነቴን በአልኮል መጠጥ እና በወሲብ በደልኩት። ምን ያህል ለሰዎች ችግሬን ማዋየት እንደነበረብኝ አልተረዳሁም ነበር” ትላለች።

በለንደን የግራፊክስ ዲዛይን ተማሪ የሆነችው ሶኢ ሚያት ኖይ በበኩሏ ከካንሰር ህክምናዋ ጋር ተያይዞ ያልተጠበቀ ማረጥ ገጥሟታል።

የ23 ዓመቷ ሶኢ ደረጃ ሦስት የአንጀት ካንሰር ህመም አለባት። ይህንንም ለማከም የጨረር ህክምና (ራዲዬሽን ቴራፒ) ያደረገች ሲሆን በዚህም በወቅቱ ያልተረዳችው ጉዳይ አጋጠማት። ጨረሩ ኦቫሪዎቿን ክፉኛ ጎዳቸው።

“ዶክተሮቹ እና ነርሶቹ ያተኮሩት ከካንሰር ህመሜ እንዴት ማዳን እንደሚችሉ ብቻ ነበር። በወቅቱ ስለ ማረጥ የነገረኝም የለም” ትላለች።

በኋላ ላይ ግን ከፍተኛ ጭንቀት፣ ድካም እና ሌሎች የማረጥ ምልክቶችን ማየት ጀመረች። ምልክቶቹም የከፉ ነበሩ።

ሶኢ ስታድግ ስለ ወር አበባ፣ ማረጥ እና የመሳሳሉ ጉዳዮች የተለመዱ ውይይቶች አልነበሩም በቤተሰቦቿ። ስለዚህም ምን እንደሆነም በደንብ አልተረዳችውም ነበር።

በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርስቲ ጓደኞቿ ስለ እርግዝና መከላከያ አይነቶች ሲወያዩ ለእሷ ግን ይህ ሩቅ ነው።

“በእኔ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳይ ሁሉ በዕድሜ ከፍ ካሉ ሰዎች ጋር ነበር የማገናኘው። ወጣትነቴን የተነጠቅኩ፣ ግማሹን ሕይወቴን የዘለልኩ ያህል ተሰማኝ” ብላለች።

ሶኢ ሚያት ከኬሞቴራፒ በተጨማሪ ስለ ማረጥ ህክምና ምን አይነት መድኃኒቶችን መውሰድ እንዳለባት በራሷ ከኢንተርኔት መፈለግና ህክምናውን በደንብ መመርመር ነበረባት።

ምንም እንኳን ከዚህ ጋር በተያያዘ ተተኪ የሆርሞን ህክምና (ኤችአርቲ) ለተወሰኑ የካንሰር ህመሞች የማይስማማ ቢሆንም ለሶኢ የተስማማ መድኃኒት በማግኘቷም የማረጥ ምልክቶቿ መሻሻል ጀመሩ።

ከመድኃኒት በተጨማሪም ረዥም የእግር ጉዞ ማድረግ እና ትኩስ መጠጦችን በማስወገድም ተገቢውን እንክብካቤ ታደርጋለች።

ሆኖም ቀደም ብላ ስለ ማረጥ አውቄ ቢሆን ኖሮ ትላለች።

በርካታ እንዲህ የወጣትነት ማረጥ ካጋጠማቸው ሴቶች መልዕክቶች እንደሚደርሳቸው ዶክተር ኒንጋት ይናገራሉ።

የጤና ባለሙያዎች የተሻለ ግንዛቤን እንዲኖራቸው እና በሁሉም ዕድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ሊወያዩበትም እንደሚገባ ያስረዳሉ።

“ከእናቶቻችሁ፣ ከአያቶቻችሁ፣ ከአክስቶቻችሁ፣ ከየትኞቹም ሴቶች ቤተሰቦቻችሁ ጋር እንዲሁም ከትዳር አጋሮቻችሁ ጋር ተወያዩ። ከእነሱ ልምድ ተማሩ። ምንም የሚያሳፍር ነገር የለም” ይላሉ።

ፒኦአይ ቶሎ ካልታከመም በሴቶች አጥንት፣ ልብ እና የአእምሮ ጤና ላይ የረጅም ጊዜ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

በተጨማሪም ህመም የተሞላበት ወሲብ እና የወሲብ ፍላጎት ማጣትንም እንደሚያስከትል ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

የ23 ዓመቷ ኤልስፔት ዊልሰን በፒኦአይ መጠቃቷን ያወቀችው ገና በ15 ዓመቷ ነው።

ለዓመታት በወሲብ ወቅት መቸገር በፍቅር ሕይወቷ ላይ የቀጠለ ደንቃራ ሆኖባታል።

“ከአንድ ሰው ጋር በጓደኝነት መቀጠል እና እንደምትወጂውም ማሳየት በጣም ከባድ ነው። ሰውነትሽ ከእሱ ጋር ካልተስማማ አንዳንድ ጉዳዮች የማይመቹ ይሆናሉ” ትላለች።

አክላም “እኔን የሚያበሳጨኝ ዶክተሮቹ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በጭራሽ አለማወቃቸው ነው” በማለት ታስረዳለች።

በ15 ዓመቷ ማረጥ ያጋጠማት ኤልስፔት

ኤልስፔት በኒውካስል በገበያ ተመራማሪነት አዲስ ሥራ የጀመረች ሲሆን ቀጣሪዎቿ ችግሯን ተረድተው ድጋፍ መስጠታቸውንም እንደ በጎ ነው የምታየው።

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የአዕምሮ ጭጋግ በሚያጋጥማት ወቅት ሁኔታዋ የከፋ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ እያለፉ ያሉ ሴቶች ቡድን ያገኘች ሲሆን፣ በዋትስአፕም በርካታ ነገሮችን ይወያያሉ።

ይህም ትንሽ እፎይታን ፈጥሮላታል።

“ማንኛውንም ጥያቄ ለመጠየቅ እና ምንም ዓይነት እፍረት በሌለበት ሁኔታ መነጋገር የሚቻልበት ቦታ ማግኘት ያረጋጋል።”

በካንሰር ህክምና ምክንያት ማረጥ ያጋጠማቸው ወጣት ሴቶች የኢንተርኔት የድጋፍ ቡድን የሆነውን የተቀላቀለችው ሶኢም በዚህ ትስማማለች።

ኤማም በጊዜ ሂደት የተማረችውም ትምህርት ይህንኑ ነው።

ህመሟን ለመደበቅ ካደረገችው ከብዙ ዓመታት ሙከራ በኋላ ኤማ በመጨረሻም ስለደረሰባት ስቃይ፣ ስላለፈችበት ሕይወት ማካፈል ጀመረች። ያለፈችበትን፣ እንዲሁም አሁን ያለችበትን ስሜት ለሥነ ልቦና ባለሙያም አናገረች። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ረድቷታል።

ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሁኔታዋን የሚረዳት አንድ የሕይወት አጋር አገኘች፣ በአሁኑ ወቅትም አብረው ይኖራሉ።

ኢንስታግራም ላይ ከማረጥ ጋር በተያያዘ የሚለጠፉ ሃሽታጎችን በመከተል ፒኦይ ላለባቸው ሴቶች መረጃ እና ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመውን 'ዴዚ ኔትወርክ' የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት አገኘች። ለመጀመሪያ ጊዜ ምንም እየገጠማት እንደሆነ የሚረዱ ሌሎች ሰዎችን ማናገሯ ትልቅ ስፍራ የምትሰጠው ነው።

የ34 ዓመቷ ኤማ የወደፊቱም ብሩህ ሆኖ ነው የሚታያት። ልጆችም እያሰበች ነው። በእንቁላል ልገሳ እና በቤተሙከራ ድጋድ (አይቪኤፍ) ልጅ መውለድ የማትቀበለው ነገር በመሆኑም በማደጎ ለመውሰድም እያሰበች ነው።

አልፎ አልፎ “ማረጥ ትኩረታችን መሆን አለበት” የሚል በቀይ የተጻፈ መፈክር ያለው ጥቁር ቲሸርት ትለብሳለች።

ደንበኞቿ ለማረጥ ገና ህጻን ነሽ ይሏታል። ሆኖም የወጣትነት ማረጥ እንዴት እንደሚከሰት ታስረዳቸዋለች።

“ከእኔ ጋር በሚያሳልፉት 30 ደቂቃ ውስጥ በሕይወታቸው ሁሉ ስለ ማረጥ ከሚያውቁት ባለፈ እንዳወቁ ይነግሩኛል። ለእያንዳንዷ ሴት መልዕክቴን በማስተላለፌ ኩራት ይሰማኛል።”

በርካታ ሴቶች በ40ዎቹ ዕድሜ ላይ እስኪሆኑ ድረስ ስለ ማረጥ አያስቡም።

ነገር ግን ቀደም ብሎ ሊጀምር ይችላል። የወጣትነት ማረጥ ያጋጠማቸው ኤማ፣ ሶኢ ሚያት፣ ኦሊቪያና ኤሌስፔት ሴቶች በማንኛውም እድሜ ማረጥን እንዲቋቋሙ ለመርዳት ልምዶቻቸውን ያካፍላሉ።

ማረጥ ምንድን ነው?

ማረጥ የሚከሰተው የሴቶች የወር አበባ የሚቆምበት ወቅት ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው በ51 ዓመት አካባቢ ይከሰታል።

ይህም ወቅት ሴቶች ልጆች የሚያፈሩበት ጊዜ የሚያከትምበት እና አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመሩን አመላካች ነው።

የወር አበባ መደበኛ አለመሆን እና መቆራረጥ በአማካይ በ46 ዓመት የሚጀምር ሲሆን፣ ይህም ቅድመ ማረጥ ይባላል።

በዚህም ወቅት የወር አበባቸው መምጫ መለዋወጥ፣ ወይም ከባድ መሆን የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ከዚህ በፊት አይተውት በማያውቁት ሁኔታ ስሜታቸው ይቀያየራል ወይም አካላዊ ችግሮች ያጋጥማቸዋል።

የወር አበባ ለአስራ ሁለት ወራት ወይም ለአንድ ዓመት ያህል ካልመጣ ማረጥ ተከስቷል ማለት ነው።

በአንዳንዶች ላይ በተፈጥሮ፣ ወይም ለሌላ በሽታ ካደረጉት ህክምና ጋር ተያይዞ ቀደም ብሎ ሊከሰት ይችላል።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የወር አበባ መቋረጥ ከዚያ በፊት ባሉት ቀደምት ዓመታት ሴቶች ላይ በተለያየ መንገድ ተፅእኖ ያሳርፋል።

የኤስትሮጅን መጠን በሰውነት ውስጥ መቀነስም የስሜት መለዋወጥን ጨምሮ በአእምሮ፣ በወር አበባ፣ በቆዳ እና በጡንቻዎች ላይ የተለያዩ ለውጦችን ያስከትላል።

ከዚህም በላይ በርካታ ምልክቶች ያሉ ሲሆን አንዳንዶች ሁሉንም ወይም ምንም ምልክቶች ላያዩ ይችላሉ። እነዚህም ምልክቶች የሚቀያየሩ ሲሆን፣ ለተለያየ የጊዜ ርዝማኔም ይቆያሉ።

ሆኖም በጣም የተለመዱት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦

  • ከባድ ወይም መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ
  • ሙቀት ሙቀት ማለት
  • በሌሊት ማላብ
  • መደበት
  • የሴት ብልት መድረቅ
  • የፊኛ ችግሮች

አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ጭጋግ ተብሎ የሚጠራው ደካማ የማስታወስ ችሎታ እና ትኩረት ማጣት የሚከሰቱ ሲሆን፣ በተጨማሪም የመገጣጠሚያዎች ህመም እና የቆዳ መድረቅም ይገጥማል።

ሁሉም ሴቶች ባይሆኑም 75 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከበድ ያሉ ምልክቶች እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ።

እነዚህ ምልክቶች በአማካይ ለሰባት ዓመታት ሊቆዩ የሚችሉ ሲሆን ከሦስቱ ሴቶች አንዷ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ያጋጥማታል።