ከኢትዮ ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የተጣመረው ወጣቱ ድምጻዊ ጀምበሩ ደመቀ

ድምጻዊ ጀምበሩ ደመቀ እና የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ንጉሡ ሙሉቱ አስታጥቄ

የፎቶው ባለመብት, Yonas Tadesse

ጀምበሩ ደመቀ ሙዚቃን እንዴት እንደ ጀመረ ሲያስታውስ ለኮምፒውተር ያለውን ፍቅር ይጠቅሳል።

ይህ የኮምፒውተር ፍቅሩ ታድያ ዩኒቨርስቲ ድረስ ተከትሎት ሄዷል።

"እኛ ቤተሰብ ውስጥ ሙዚቃ ማዳመጥ የተለመደ ነገር አልነበረም" ሲል የሚያስታውሰው የ22 ዓመቱ ጀምበሩ፣ ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር የሠራው 'አይፈራም ጋሜ' የተሰኘው ሙዚቃ በብዙዎች ዘንድ ተወዶለታል።

ጀምበሩ ከሳምንታት በፊት ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ጀምበሩ በራሱ ስም በሰየመው በዚህ የመጀመሪያ አልበሙ ውስጥ የሙላቱ አስታጥቄን የተለያዩ ሙዚቃዎች ሳምፕል አድርጓል።

ከዚህ ባሻገር የጃዝ ሙዚቃው ንጉሥ ሙላቱ አስታጥቄ በአይፈራም ጋሜ ላይ አብሮት ተሳትፏል። ጀምበሩ ደመቀ ከቢቢሲ ጋር በሥራዎቹ ዙሪያ ያደረገውን ቆይታ እነሆ፦

ከሙላቱ ጋር አይፈራም ጋሜን እንዴት ለመስራት ተገናኛችሁ?

ይህንን ሙዚቃ መስራት የጀመርነው የዛሬ ሁለት፣ ሦስት ዓመት ነው። እኔና አቀናባሪው ላዕከምህረት ጋሽ ሙላቱን በስም እና በክብራቸው ብቻ እንጂ በአካል አግኝተናቸው አናውቅም። ያው የተለያዩ ሥራዎችን ሳምፕል እናደርጋለን።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ መካከል ነው አንድ ቀን ላዕከ ይህንን ሙዚቃ ሳምፕል አድርጎ ይዞልኝ መጣ። አይፈራም ጋሜ የሚለው ድምጹ እዚያው ላይ ነበር። ያንን ይዤ ሙዚቃ ለመስራት ሞከርኩ። ነገር ግን ትንሽ ጊዜ ወሰደ። የዛሬ ዓመት ገደማ የሆነ ቦታ ስናደርሰው ያኔ ሚዶ ሪከርድስ ተቀላቀልኩ።

በዚህ መካከል የእኔ ማናጀር ጉታ፣ ጋሽ ሙላቱን የማግኘት ዕድል አለ ሲለን፣ የኮፒራይት ፈቃድ ለማግኘት በተጨማሪም እርሳቸውም የሠራነውን እንዲሰሙልን እንፈልግ ስለነበር የደረስንበትን ይዘን አገኘናቸው።

መጀመሪያ ያገኘናቸው ቀን እኔ በጣም ፈርቼ ነበር። እርሳቸውን የሚያክል ሙዚቀኛ አጠገቤ ተቀምጠው የእኔን ሙዚቃ ሲያዳምጡ አስፈርቶኝ ነበር።

ሙዚቃውን ከሰሙ በኋላ ግን የነበራቸው ምላሽ የበለጠ የሚያስደንቅ ነበር። በጣም ነበር የወደዱት፤ ያከብረናቸውን ያህል ነበር ያከበሩን።

የኮፒ ራይት ፈቃዱን ካገኘን በኋላ አብሮ የመጫወት፣ በቪዲዮ ክሊፑ ላይ የመሳተፍ ቀጣይነት ያለው ወዳጅነት መመስረት ቻልን። ለእኛ የሰጡን ክብር እርሳቸው ለሙዚቃ እንዲሁም ለሰው ያላቸውን ክብር ያሳያል።

ጋሽ ሙላቱ አይፈራም ጋሜን ከ50 ዓመት በፊት ነበር የሰሩት። አሁን ዳግም በአንተ ድምጽ በአዲስ ስልት ሲሰሙት ምን አሉ?

በመጀመሪያ ያሉን "እንዴት አመጣችሁት?" ነው። ምክንያቱም ቅርጹ ትንሽ ወጣ ያለ ነው የሙዚቃው። የላቲን ሙዚቃም ስሜት አለው። ያንን እንዴት ወደ ሂፖ ሆፕ አምጥታችሁት እነዚህን ሞደርን ሳውንዶች ከተታችሁ? የሚል ጥያቄ ነው የፈጠረባቸው። ከምንም በላይ ያደነቀው ሳውንዱን ነው።

ከግጥሙም ከምኑም በላይ እንዴት እንደተዋሃደ እያደመጠ በጣም ነበር የተገረመው። የበለጠ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ውስጥ ሰፊ ዕድል እንዳለ ስላየ ይህንን መንገድ ብትቀጥሉበት በጣም አሪፍ ነው ነው ያሉን።

የድሮ ሥራዎች ውስጥ አሁን ያለውን የዘመን መንፈስ ማሳየት ከቻልን በሁለቱ ትውልዶች መካከል እንደ ድልድይ መሆን እንችላለን።

ስለዚህ ሥራው በሁለቱ ትውልዶች መካከል እንደ ድልድይ መሆን ነበር ያለመው ማለት ነው?

በትክክል።

በቤተሰባችሁ ውስጥ ሙዚቃ ማድመጥ የተለመደ ነገር እንዳልነበር ነግረኸኛል፤ ታድያ እንዴት ሙዚቀኛ ሆንክ?

ሙዚቃን የተዋወቅኩት በ11 ዓመቴ አካባቢ ነው። ታዲያ ያኔ ከሕዝብ ጋር ስተዋወቅ የጀመርኩት በሂፕ ሆፕ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሂፖ ሆፕ ልቤ ውስጥ ቦታ አገኘ።

ታድያ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ኮምፒውተር በጣም ስለምወድ ፕሮዲውስ ማድረግ ጀመርኩ። ኮምፒውተር በጣም ስለምወድ ከኮምፒውተር ጋር ነው ያደግኩት። ያኔ ታድያ የቅንብር ሶፍትዌር ተልኮልኝ፣ ኤፍ ኤም ስቱዲዮ የሚባል፣ በርካታ ቢቶችን ሰራሁ።

ትዝ ይለኛል 11ኛ ክፍል እያለሁ ክረምት ላይ ነበር። ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ ምን እንደማደርጋቸው ግራ ገባኝ። ሙዚቃ የሚጫወቱ አልያም የሚያቀናብሩ ጓደኞች የሉኝም ። ስለዚህ ሂፖ ሆፕ ስለምወድ ለምን ራሴ አልጫወታቸውም ወደሚለው ሃሳብ መጣሁ።

የሙዚቃ አልበምህ ልክ እንደ መግቢያ የተሰኘ ትራክ አለው። መውጫም ስትል የሰየምከው ሥራ አለ። በዚህ መልክ ማደራጀት የፈለግክበት ምክንያት ምንድን ነው?

እኔ አንድ አልበም ራሱን የቻለ ታሪክ መናገር አለበት ብዬ አምናለሁ።

ከሙዚቃው ባሻገር መናገር የምፈልገው መልዕክት በሥራዎቹ ውስጥ መኖር አለበት። መግቢያ እና መውጫ የሚለው ብቻ ሳይሆን በቅደም ተከተል የሚመጡት ሙዚቃዎችም የሆነ ነገር ለመናገር ይሞክራሉ።

በተናጠል ለመስማት የሚፈልግ ደግሞ ቢሰማው ምንም የሚጎድልበት ነገር አይኖርም። መግቢያ እና መውጫ የኖረበትም ምክንያት እኔ ሙዚቃውን መሥራት ስጀምር ካምፓስ ውስጥ ነበርኩ። እና ከዚያ አንጻር በግሌ የማስባቸው ፍልስፍናዊ የሆኑ ነገሮች አሉ።

እነዚያን ነገሮች በሙዚቃ እንዴት ነው የማስቀምጣቸው የሚለውን ሳስብ አንድ ታሪክ ሲጀምር ሲገባድድ፣ ማገባደጃው ደግሞ የሌላ ታሪክ መጀመርያ መሆኑን ለመናገር ነው የፈለግኩት።

ስለዚህ የመግቢያው ሙዚቃው ሊነጋ እንደሆነ ይነግርሃል። . . . ልክ መጨረሻ ላይ ደግሞ ለውጥ የሚለውን ስትሰማው የዚህ ሁሉ ነገር ማገባደጃው ለውጥ ነው የሚለውን ማሳየት ፈልጌያለሁ።

እኔ ይህንን አልበም ሳጠናቅቅ የተገነዘብኩት ነገር ይህንን አልበም በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ መለወጤን ነው። ከዚህ በኋላ ሊመጣ የሚችለው ሥራዬ ደግሞ ከዚህ ለውጥ የተነሳ ነገር ነው የሚል ጥቁምታ ይሰጣል።

በዚህ አልበም ዝግጅት ውስጥ በግሌም ተለውጫለሁ ስላልከኝ. . . ከየት ተነስተህ ወዴት ነው የተለወጥከው?

በዚህ አልበም ውስጥ የተካተቱት ሥራዎቼ የተጻፉት ራስን፣ አካባቢን እና ዙሪያን ከመረዳት አንጻር ነው።

አንድ ሰው በተለይ ታዳጊ ወጣት ብዙ ነገሮችን ሊያይ ይችላል። ብዙ ዓይነት ‘ኢሞሽናል ትራንስፎርሜሽኖች’ [የስሜት ለውጦች] ሊኖሩት ይችላሉ። እነዚህ የግል ልምምዶቼን በማጤን እና በማስተዋል፣ እኔ ራሴ ምን ማድረግ እንደምፈልግ የማወቅ ሂደት ውስጥ ነበርኩ።

ይህንን የመለወጥ ራስን የማወቅ እና ራስን የመሆን ሂደት ማስተዋል የጀመርኩት ሙዚቃውን በምሰራበት ሂደት ውስጥ ሆኜ ነው።

ጀምበሩ ደመቀ

የፎቶው ባለመብት, Yonas Tadesse

በዚህ ሙዚቃ ውስጥ ራስህን መፈለግ፣ ራስን እያገኙ እና ዳናን እየለዩ መሄድ ልንለው እንችላለን?

ልንለው እንችላለን። ግን ራስን ጥንቅቅ አድርጎ ማወቅ ይቻላል ብዬ አላምንም። ነገር ግን በሆነ ደረጃ ራሴን ያገኘሁበት፣ ያወቅኩበት እንደሆነ ይሰማኛል። ከዚያም በኋላም ቢሆን ይህ ይቀጥላል ማለት ነው።

በአልበምህ ላይ የተካተተው እና 'ለውጥ' ስትል የሰየምከው የመጨረሻው ትራክ ቀጣዩ ሥራዬንም ያመለክታል ብለኸኛል።

አዎ። ግጥሙንም በደንብ ሰምተኸው ከሆነ 'ሰው ዘንድሮ ለውጥ ይፈልጋል፤ ቁጭ ተብሎ እንዴት ይመጣል' የሚሉ ስንኞች አሉት። ያለሁበት ሁኔታ ውስጥ ምቾት እንደማይሰማኝም ለማሳየት ነው። ማለትም በዚህ አልበም ውስጥ ከነበሩኝ እሳቤዎች አልፌ እንደምሄድ ለማሳየት የተጠቀምኩበት ነው።

በሚመጡ ሥራዎቼ እኔም ሆንኩ ሙዚቃዬ አድገን እንገኛለን። ሌላ አዲስ ጭብጥ፣ ሃሳብ ይዤ እመጣለሁ። እኔ ሙዚቃ ስሰራ ሁሌም የነበርኩበት ሁኔታ፣ ሃሳቤ፣ ማንነቴ እየተለወጠ ነው የመጣው። የምሰራባቸው መንገዶችም በተወሰነ መልኩ እየተለወጡ መጥተዋል።

ስለዚህ አዲሱ ነገር ከነበረው ሙሉ በሙሉ እንደሚለወጥ እና በግጥሞቹም ላይ ለማለት እንደሞከርኩት፣ ቀጥሎ የምናገረው፣ የምሰራቸው ሥራዎች ሁሉ እውነት እንደሚሆኑ ነው።

ሁሉም ነገር እውነት ይሆናል ስትል አንተ እና የምትኖረውን ሕይወትህን ነው ወይስ ሥራዎችህ ስለሚያሳዩት የሕይወት ልምድ ለማለት ነው?

በሥራዎቼ ነው እውነተኛ የምሆነው። እኔን ሆኜ ነው የምገኘው። ይህንን አልበም ስሰራ የነበርኩበት እና ሳጠናቅቅ የተገኘሁበት የአዕምሮ ደረጃ የተለወጠ ነው። በወደፊቱ ሥራዬም ይህ ይቀጥላል።

በአልበምህ ላይ 'የእቴጌ ጨዋታ' ስትል የሰየምከው ትራክ በጣም አጭር ነው። አንድ ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ያህል ብቻ ነው የሚረዝመው። ለምንድን ነው እንዲህ እንዲያጥር የፈለግከው?

ሙዚቃ ኢሞሽን እና ፈጠራን አቀናጅቶ የያዘ የጥበብ ቅርጽ ነው አይደል? እንደዚያ እንደመሆኑ እኔ የዚያን ሙዚቃ ሃሳብ ስሰራው ብዙ መናገር አልፈለግኩም። ሙዚቃው መናገር የሚችለው ያንን ብቻ ነው። በትንሽ ነገር ብዙ ማለት የሚችል ሙዚቃ ነው የጻፍኩት።

ምንም እንኳ አንድ ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ ብቻ ቢረዝምም ሦስት አራት ትርጉሞችን አምቆ ይዟል። ስለዚህ ኢሞሽን እና ፈጠራ አብረው ሲቀናጁ ምን ያህል ጉልበት እንደሚኖራቸው ያየሁበት ነው።

መጀመሪያ ስሰራው በዚህ መልኩ አስቤው አይደለም የሰራሁት፤ ግን ሙዚቃው ያለቀበት ቦታ ስደርስ ከዚህ በላይ አልጨምርም አልቀንስም ብዬ ያቆምኩበት ነው።

በአልበሜ ውስጥ ከተካተቱ ሥራዎች በተለየም ኢሞሽናሊ የተሳተፍኩበት ሙዚቃ ነው። ግጥሙንም፣ ዜማውንም ቅንብሩንም ስሰራው ሙሉ በሙሉ ኢሞሽናል የነበርኩበት ሥራ ነው።

መናገር የፈለግኩበትን ነገር ሙሉ በሙሉ ተናግሬ ያለፍኩበት ሥራ ነው። ምናልባትም የወደፊት ሰብዕናዬን የሚያሳየው ሥራ ይኼኛው ይመስለኛል።

ጀምበሩ ደመቀ

የፎቶው ባለመብት, Yonas Tadesse

ይህ የአንተ አልበም ሂፕ ሆፕን ከኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ጋር ተጣምሮ ያየንበት ነው ማለት እንችላለን?

በተወሰነ መልኩ አዎ ማለት ይቻላል። ሂፕ ሆፕ አለው። ኤሌትሮኒክስ ሳውንዶችም በጣም ብዙ አሉት። ሞደርን የሆነ ሂፕ ሆፕ በእኛ ሳውንድ ተተርጉሞ ነው በተወሰነ ደረጃ ያየነው።

በሙዚቃ ስልትህ የእነማን የእነማን ተጽዕኖ አለብህ?

ከምዕራባውያን ሙዚቃ ‘ኮንሺየስ ሂፓፕ’ ስልተ ምትን ከሚሰሩ ሙዚቀኞች መካከል ኬንድሪክ ላማር፣ ጀርሚን ኮል፣ ድሬክ አጠቃላይ ሂፕ ሆፕ የምሰራበት ማንነቴ ላይ ተጽዕኖ አላቸው።

ወደ አገር ውስጥ ስንመጣ ደግሞ አዲሱን ትውልድ የሚወክሉ ሙዚቀኞች፣ ዘመናዊ የሆነውን ሳውንድ እና የተለያዩ ስልተ ምትን እያስተዋወቁ ካሉ ሙዚቀኞች መካከል ደግሞ በዋነኛነት የሮፍናን፣ የካስማሰ፣ የዮሃና እና የዲጄ ሚላ ተጽዕኖ አለብኝ።

ይህንን ትውልድ ወክለን እንሰራለን የሚሉ በርካታ ሙዚቀኞች አሉ። ከእኛ ሳውንድ እና መልዕክት ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ መረዳዳት አለ።

አልበምህ ላይ ከጾታዊ ፍቅር መወድስ ይልቅ ነገን ተስፋ ማድረግ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ደፋር መሆንን፣ መናገርን፣ ከፊት መቅደም በመልዕክት ደረጃ ጎልተው ተሰምተውኛል። አንተ በሥራዎችህ አጠቃላይ ልታስተላልፈው የፈለግከው ምንድን ነው?

ከአልበሜ አንጻር ከሆነ የምናወራው፣ በጣም የተለያዩ መልዕክቶች ናቸው ያሉት። አንድ ይህ ነው የምለው መልዕክት የለኝም። የተለያዩ መልዕክቶች ናቸው የታዩት።

አልበሙን በሃሳብ ደረጃ ስሰራው የተለያዩ ሙዚቃዎች በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ስሜቶች ውስጥ ነው የተሰሩት።

በእርግጥ በአጠቃላይ ማስተላለፍ የምፈልገው ኮንሺየስ (የታቀደበት) መልዕክት ቢኖርም አልበሙ ላይ የነበሩኝ የተለያዩ ሙዚቃዎች ከተለያየ ቦታ የተገኙ እና በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ በመሆናቸው የተለያዩ መልዕክቶች ያላቸው ናቸው።

በዚህ አልበሜ ማስተላለፍ የፈለግኩት ጀምበሩ የነበረበትን ሁኔታ፣ በተለያዩ ጊዜያቶች በሰራው ሙዚቃዎች፣ በዚያ ውስጥ የተሰማውን ስሜት ለማሳየት ነው። አሁን ባለሁበት ሰዓት የተሻለ መልዕክት የሚኖረኝ ይመስለኛል። እርሱን ግን ቀስ ብለን የምናየው ይሆናል።