ሁለት ዋነኛ ተፎካካሪዎቻቸውን ከምርጫ ያገዱት የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝዳንት ለአራተኛ ጊዜ ተመረጡ

አላሳኔ ኦውታራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሁለት ዋነኛ ተፎካካሪዎቻቸውን ከምርጫ ያገዱት የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝዳንት አላሳኔ ኦውታራ ለአራተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን አብላጫ ድምጽ ማግኘታቸው ተገለጸ።

የ83 ዓመቱ አላሳኔ ኦውታራ 89.8% ድምጽ ማግኘታቸው ይፋ ተደርጓል። በሁለተኛ ደረጃ የቀድሞው የንግድ ሚኒስትር ዣን-ሉዊ ቢሎን 3.09% ድምጽ አግኝተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለአራተኛ ጊዜ ሊያሸንፉ መሆኑ እምብዛም አስገራሚ አልሆነም። ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላውረንት ጋግቦ እና ነጋዴው ቲዳጄ ቲሀም ከምርጫው ከታገዱ በኋላ ሕዝቡ በምርጫው እንዳይሳተፍ ጠይቀዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባለቤት ሲሞን ጋግቦ በምርጫው እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸው 2.42% ድምጽ አግኝተዋል።

የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ እንዳለው ከጠቅላላው ሕዝብ 50.1% የሚሆነው ድምጽ ሰጥቷል።

ትናንት ከተለያዩ ግዛቶች የተገኘ ድምጽ ተቆጥሮ ውጤቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ምርጫ ቦርዱ ቅሬታዎች ላይ ምርመራ ካደረገ በኋላ አጠቃላይ ውጤቱን የሚያሳውቅ ይሆናል።

በምርጫው እንዳይሳተፉ የታገዱት ተቃዋሚዎች ላውረንት ጋግቦ እና ቲዳጄ ቲሀም ያሳለፍነው እሑድ ምርጫውን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

ምርጫውን 'መፈንቅለ መንግሥት' ብለው የጠሩት ተቃዋሚዎቹ፤ አላሳኔ ኦውታራን ፕሬዝዳንት አድርገው እንደማይቀበሉም አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የያዙት እአአ በ2011 ነበር።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላውረንት ጋግቦ በ2010 በምርጫ መሸነፋቸውን እንደማይቀበሉ ካስታወቁ በኋላ ታስረዋል።

የቀድሞውን ፕሬዝዳንት እስራት ተከትሎም ላውረንት ጋግቦ ተሹመዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለሁለት የሥልጣን ዘመን ብቻ እንዲቆዩ ተወስኖ ነበር። ሆኖም በ2016 ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ አድርገው በ2020 በድጋሚ ምርጫ መወዳደር ችለዋል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ውሳኔውን አውግዘዋል።