የ92 ዓመቱ ፖል ቢያ ለስምንተኛ ጊዜ የካሜሩን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የ92 ዓመቱ ፖል ቢያ ለስምንተኛ ጊዜ የካሜሩን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ። በአፍሪካ ለረዥም ጊዜ በማስተዳደር ሁለተኛው መሪ ሆነዋል።
ፖል ቢያ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከፍተኛ ጫና ሲደረግ ቢቆይም አልተሳካም።
"እስካሁን ካያችሁት የተሻለ ነገር የሚመጣው አሁን ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ለሕዝቡ ቃል ገብተዋል።
የኢኳቶሪያል ጊኒ መሪ ቴዎዶሮ ኦቢያንድ ንጉማ ምባሶጎ ለረዥም ዓመታት በማስተዳደር ከአፍሪካ ግንባር ቀደሙ ናቸው።
ፖል ቢያ እአአ ከ1982 አንስቶ ካሜሩንን መርተዋል። በ2032 100 ዓመት ይሞላቸዋል። ከሰባት ዓመታት በኋላ ካሜሩንን ለ50 ዓመት ያስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
ምርጫው መጭበርበሩን ተቃዋሚዎች ቢናገሩም የፖል ቢያ ፓርቲ ክሱን አስተባብሏል።
ፕሬዝዳንቱ እስከ 2032 ድረስ በሥልጣን ይቆያሉ።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኢሳ ቲቺሮማ ምርጫውን እሳቸው እንዳሸነፉ እና ይፋ የተደገው ውጤት ሐሰተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በተቃዋሚው መኖሪያ አካባቢ ተኩስ ተከፍቶ ንጹኃን መገደላቸውን ተናግረዋል።
"እስካሁን ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። እንዴት ወንድሞቻቸው ላይ እንደሚተኩሱ አይገባኝም። ምንም ቢያደርጉም አገሪቱን ነጻ ከማውጣት ወደኋላ አልልም" ብለዋል።
በካሜሩን ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ባሜዳ ነውጥ ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት ነዋሪዎች ከቤት አልወጡም።
ትናንት በዶአላ ከተማ በነበረ ተቃውሞ ላይ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተነሳው ግጭት አራት ሰዎች ተገድለዋል።
በካሜሩን ተቃውሞ ቢከለከልም ተቃዋሚዎች ገዢው ፓርቲ "ድሉን ሊነጥቀን ነው" በማለት አደባባይ ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ፖል ቢያ በዕድሜ ትልቁ አፍሪካዊ መሪ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ ለረዥም ጊዜ ከዕይታ መሰወራቸው ሞተዋል የሚል ጭምጭምታ አስነስቶ ነበር።
ከአሕመዱ አሕዲጆ ሥልጣን ሲረከቡ አገሪቱን ለመለወጥ ቃል ገብተው ነበር።
እአአ በ1992 ከገጠማቸው ጠንካራ ፉክክር ውጭ በአብዛኞቹ ምርጫዎች በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል።
በካሜሩን የተካሄዱ ምርጫዎች እንደተጭበረበሩ በተደጋጋሚ ክሶች ይሰነዘራሉ። ፖል ቢያ በተቃዋሚዎች መካከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ በማድረግም ተፎካካሪዎቻቸውን እንደረቱ ይነገራል።
ፕሬዝዳንቱ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስቲዎች በማስፋፋት ስማቸው በበጎ ይነሳል።
ከናይጄሪያ ጋር በነበረው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በነዳጅ የበለፀገችው ባካሲ ወደ ካሜሩን እንድትጠቃለል በማድረግም ይታወቃሉ።
ሆኖም እንግሊዘኛ ተናጋሪ በሆነው የካሜሩን ግዛት የታጣቂዎች ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።
ከ35 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች ዘንድ ሥራ አጥነት 40% ደርሷል።
መንገዶች እና ሆስፒታሎች ዕድሳት ሳይደረግላቸው ቆይተዋል። የንግግር ነጻነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገደበ መጥቷል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኢሳ ቲቺሮማ 54.99% ድምጽ አግኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Michel Mvondo/BBC
በካሜሩን የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ለተቃዋሚ መሪው ድጋፍ ተሰጥቷል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎት ተገድቧል። የአገሪቱ ቴሌኮምንኬሽንም "የቴክኒክ ችግር" እንደገጠመው ገልጿል።
የፖል ቢያ ማሸነፍ ይፋ ከተደረገ በኋላ በመዲናዋ ያውንዴ ሱቆች እና ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩም ከቤታቸው አልወጡም።
ካለፉት ጥቂት ቀናት ጅመሮ በተለያዩ ከተሞች የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተዋል።















