የ92 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዝዳንት አስከ 100 ዓመታቸው ለመምራት ምርጫ ሊወዳደሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለማችን በዕድሜ የገፉት መሪ የ92 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ምርጫ በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉ ከሆነ ካሜሩንን ለ43 ዓመታት ያስተዳደሩ መሪ ይሆናሉ።
ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት "ያጋጠሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች በመጋፈጥ ላገለግላችሁ ቁርጠኛ መሆኔን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለስምንተኛ የሥልጣን ዘመን ለመቀጠል የወሰኑት ከተለያዩ የካሜሩን ክፍሎች እና ከውጭ "በርካታ እና ያልተቋረጡ" ጥያቄዎች ስለቀረቡላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፖል ቢያ በአውሮፓውያኑ 2008 አንድ መሪ የሚያገለግልበትን የሥልጣን ዘመን የሚገድበውን ሕግ አስወግደው ነው ያለምን ገደብ በተከታታይ ለመሪነት እየተወዳደሩ ያሉት።
ከዚህ ደቀም በ2018 በተካሄደው ምርጫ ፖል ቢያ የመራጮችን 71 በመቶ ድምጽ አግኝተው ቢያሸንፉም፤ ተቃዋሚዎች ግን መጠነ ሰፊ የተዛቡ የምርጫ አሠራሮች ታይተዋል በማለት ከስሰዋል።
በሥልጣን ላይ ለረጅም ዘመናት የቆዩት የዕድሜ ባለጸጋው የፖል ቢያ አስተዳደር በሙስና፣ በስርቆት፣ በተበላሸ አስተዳደር እና የአገሪቱን የደኅንነት ችግሮችን ለመቅረፍ ባለመቻል ትችት ይቀርብበታል።
በተጨማሪም ለአራት አስርት ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ የቆዩት መሪ ከዕድሜ መግፋት የተነሳ በሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች ምክንያት አገሪቱን በአግባቡ ሊመሩ ይችሉ እንደሆን ጥያቄ ይቀርብባቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ለስድስት ሳምንታት ያህል ከሕዝብ ዕይታ በተሰወሩበት ጊዜ በጤንነታቸው ዙሪያ መላምቶች ከመዘዋወራቸው በተጨማሪ ሞተዋልም ተብሎ ሲወራ ነበር።
የአዛውንቱ መሪ አሁንም በሥልጣን ስለመቀጠላቸው በብዙዎች ዘንድ ግምት የነበረ ቢሆንም፣ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከመግለጻቸው በፊት አልተረጋገጠም ነበር።
ፖል ቢያ በአውሮፓውያኑ 1982 ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በተካሄዱ ምርጫዎች በአንዱም ሳይሸነፉ ነው በመንበራው ላይ የቆዩት። በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ለሰባት ዓመት ለመምራት የሚያሸንፉ ከሆነ እስከ 100 ዓመታቸው ድረስ ካሜሩንን ይመራሉ።
ነገር ግን የፕሬዝዳንቱን በሥልጣን የመቀጠል ፍላጎት በመቃወም አገሪቱን አዲስ አመራር እንዲረከብ ቦታ እንዲለቁ ከአገር ውስጥ እና ከውጪ እየጠነከረ ያለ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንቱ በዕጩነት መቅረባቸውን ያስታወቁት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ካሉ ወሳኝ የፖለቲካ አጋሮቻቸው ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ ሲሆን፣ እነዚህ የፖለቲካ ተጣማሪዎቻቸው ቀደም ባሉት ምርጫዎች ጉልህ ድጋፍን ለፕሬዝዳንቱ ያስገኙ ናቸው።
በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ቁልፍ የሚኒስትርነት ቦታ የነበራቸው የፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ ደጋፊዎች ገዢውን ፓርቲ ለቀው ከወጡ በኋላ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በመጪው ምርጫ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፖል ቢያን ለመፎካከር እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል።















