በጎረቤት አገር መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ በኋላ ካሜሮን የጦር አመራሮች ሹም ሽር አካሄደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋቦን የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት ካደረገ በኋላ የጎረቤት አገር ካሜሮን ፕሬዝዳንት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አመራሮች ላይ ሹም ሽር አደረጉ።
27 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ካሜሮንን ከ40 ዓመታት በላይ የመሩት ፕሬዝዳንት ፖል ፒያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በሌሎች የተኩት በጋቦን መፈንቅለ መንግሥት በተደረገበት ተመሳሳይ ቀን ነው።
ፕሬዝዳንቱ በካሜሮን በመከላከያ ሚንስቴር እና በጦር ኃይሎች ውስጥ ይገኙ የነበሩ አመራሮችን ለማሸጋሸጋቸው የተሰጠ ይፋዊ ምክንያት የለም።
የምዕራብ አፍሪካ የደኅንነት ተንታኞች ግን ፕሬዝዳንቱ የጦር አመራሮችን ሹም ሽር ያካሄዱት በቀጠናው ጦር ሠራዊት መኮንኖች የሚካሄዱ መፈንቅለ መንግሥት በመበራከታቸው ነው ይላሉ።
በቅርቡ ብቻ በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበሩት ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒጀር እና ጋቦን መሪዎች በኃይል ከሥልጣን ተነስተዋል።
“ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበሩ አገራት እየተበራከተ ነው . . . ለረዥም ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪዎች በኃይል እየተነሱ ነው። ይህ ደግሞ ለመሪዎች ስጋት ነው” ሲሉ የደኅንነት አማካሪው ዴቪዲ ኦቶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በወጣት ትውልድ የተሞላ ጦር ሠራዊት ለረዥም ዓመታት ሥልጣን ላይ የከረሙ አምባገነኖችን የማገልገል ትዕግስት የለውም” ይላሉ የደኅንነት አማካሪው።
ፕሬዝዳንት ቢያ ወታደራዊ ሹም ሽሩን ያካሄዱት የመፈንቅለ መንግሥት ስጋት አድሮባቸው ነው ይባል እንጂ አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን የሥልጣን ሽግሽግ የማድረጉ ዕቅድ ቀድሞ የነበረ ነው ይላሉ።
በካሜሮን መከላከያ ሚንስቴር ውስጥ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ኮሎኔል ሲሪል ጉኤሞ ለቱርክ የዜና ወኪል ሲናገሩ ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ሽግሽግ ቀድሞ የነበረ ዕቅድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ተንታኞች በካሜሮን በተካሄደው የጦር አመራሮች ሹም ሽር ወደ ሥልጣን የመጡ መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድም ሆነ ለማሴር ይህ ነው የሚባል ሥልጣን እና ዕድል እንዳይሰጥ ተደርጎ ነው ይላሉ።
የ90 ዓመቱ ቢያ ከእአአ 1982 ጀምሮ ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ሲመሩ የቆዩ ሲሆን የመጀመሪያውን ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ባለፉት አራት አሥርት ዓመታት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ለፖል ቢያ ታማኝ ሆኖ ቆይቷል።












